ሃይማኖትና ዓለማዊ ህግ፧ | ዓለም | DW | 19.09.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሃይማኖትና ዓለማዊ ህግ፧

ዓለምን እጅግ የሚያቀራርብ ቴክኖሎጂ በተስፋፋበት በአሁኑ ዘመን፧ ሃይማኖት በተለያዬ ኅብረተሰብ የሚሰጠው ከፍተኛ ግምት እንደ ጥንቱ ነው-አይደለም? የሲቭልና የሃይማኖት ህጋዊ መብት ምን ይመስላል?

default

በዚህ ርእስ ዙሪያ፧ ያተኮረ ዐውደ-ጥናት በርሊን ውስጥ በ Humboldt ዩኒቨርስቲ ተካሂዶ ነበር። የ DW (የጀርመን ድምፅ ራዲዮ)ባልደረባ ሄንሪየተ ቭሬገ፧ ዐወደ-ጥናቱን ተከታትላ ያጠናቀረችውን ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድርጎ አቅርቦታል።
በማንኛውም ኅብረተሰብ ድሮ ፍትኀዊ ብያኔ የሚሰጠው ሃይማኖትን ምርኩዝ በማድረግ እንደነበረ አይታበልም። በአሁኑም ዘመን፧ በዚያው መልክ የሚሠራባቸው አገሮች መኖራቸው የታወቀ ነው።
ክፉ ነገር ማድረግ ወይም ወንጀል መፈጸም፧ በአሉታዊነት እንጂ በሌላ መልኩ የሚታይ አይደለም። በኢንዱስትሪ የገሠገሠው ምዕራቡ ዓለም፧ ለዴሞክራሲ ግንባታ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የተለያዩ እንዲሆኑ ማድረግ ተቀዳሚ ግዴታ አድርጎ የተከተለው መመሪያ መሆኑ ነው የሚነገረው። Maray Ann Case የተባሉት በህገ-መንግሥት ላይ ምርምር ያደረጉት አሜሪካዊት የህግ ባለሙያ፧ በአገራቸው፧ አንዳንድ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ያልተለመዱ የኑሮ ፈሊጦችን በተመለከተ (ለምሳሌ ያህል የተመሳሳይ ጾታዎች ጋብቻን) ካቶሊካውያንና አይሁድ የሚቃወሙት ሲሆን፧ ፕሮቴስታንቶች ለዘብ ባለ አቋም ይከታተሉታል ይላሉ።
ብዙዎች ፕሮቴስታንቶች ጋብቻንም ሆነ ፍቺን በተመለከተ መንግሥታዊውን ደንብ ነው የሚከተሉት። በሌላ በኩል፧ ወግ አጥባቂ ፕሮቴስታንቶች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ድጋፍ በመሻት፧ የጋብቻ ውል የፈጸሙ ባልና ሚስት የፍቺ ህግን በመከተል ሳይሆን፧ በጥንታዊው ሃይማኖታዊ እሴት እንዲመሩና ፧ ፍቺን ችላ እንዲሉ ለማድረግ በመጣር ላይ መሆናቸውን ሜሪ አን ኬዝ አስረድተዋል።
ህጋዊ መብትና ሃይማኖት፧ የሚጋጩባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች ሲጠቅሱም ሲኮች፧ ከሃይማኖታዊ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሰይፍ እንደሚይዙና፧ ይህ ደግሞ በአውሮፓውያን ጦር መሣሪያ ነክ ደንብ፧ ህግን መጣስ መሆኑን አብራርተዋል። አንዳንድ ሃይማኖትን በማክረር የሚከተሉ ወገኖች በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ኃጢአት የተመላበት ትምህርት ይሰጣል በማለት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ባለመላክ፧ ትምህርትን የሚመለከተውን ህግ ይጥሳሉ ማለት ነው።
በ Halle ከተማ፧ በማክስ ፕላንክ ተቋም የሚሠሩት የሥነ ሰብእ ተማራማሪ Kebet von Benda-Beckmann በደቡብ ምሥራቅ እስያ ካካሄዱት ምርምር አኳያ፧ ሃይማኖት የምዕራቡን አመለካከት የማይጻረር መሆኑን ይገልጻሉ።
«ሃይማኖት መንግሥትን መውቀስ የሚያስችልም ነው። ለምሳሌ ያህል፧ ፈላጭ ቆራጭ ገዥዎች በሚገኙባቸው አገሮች መንግሥትን ለመውቀስም ሆነ ለመንቀፍ ብቸኛው ተቋም የሃይማኖት ነው። በኢንዶኔሺያ በሱሃርቶ የአገዛዝ ወቅት ታይቷል፧ በሌሎች የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችም እኒሁ! ሃይማኖት፧ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንም መተቸት የሚያስችል ነበረ«።
የሥነ-ሰብእ ምሁሯ፧ መስከረም 1 ቀን 1994 ዓ ም ዩ ኤስ አሜሪካ ውስጥ አጥፍቶ ጠፊች ዕልቂት ካስከተሉ ወዲህ፧ የከረረ እሥልምና የሚከተሉ ወገኖችን ምዕራቡ ዓለም ለዴሞክራሲ ጠንቅ አድርጎ ይመለከታቸዋል። እስላማዊውን ህግ፧ ሸሪያን በዚያው መልክ የሚያዩ አሉ። በተለይ የቤተሰብን መብት፧ ጋብቻና ፍቺን የባልና ሚስት ግንኙነት ለጋራ ልጅ፧ የማሳደግ መብት የባለርስትነት መብት እንዲሁም የውርስ መብት፧ የ Benda-Deckmann የሚያከራክሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
«መታወቅ ያለበት መጥፎ አድልዎን ለማስቀረት ይጠቅማል ተብሎ ነው ሸሪያ የሚሠራበት። በሰሜን ካሜሩን፧ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች፧ ለደህንነታቸው በሃይማኖት ባለሥልጣናት ነው የሚመኩት። በጎሣ ደንብ፧ የባሎቻቸውን መሬት ለቀው መሄድ ቢገባቸውም፧ በተጠቀሰው አገርና አካባቢ፧ ለሴቶች የሚሠራው ደንብ፧ የውርስ መብትን ያስከብርላቸዋል። ወደ መንግሥት ፍርድ ቤቶች በመሄድም የላቀ የእኩልነት መብትን ማስከበር ይችላሉ። ግን እማስፈጸሙ ላይ ችግር አለ። እስላማውያኑ ባለሥጣናት፧ በገጠሩ ቦታ ላቅ ያለ ሥልጣንና ተሰሰሚነትም አላቸው። ለእነርሱ አቤት! ማለቱ፧ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።«
Kebet von Benda-Beckmann አክለው እንዳስረዱት፧ «ግለሰባዊ ነጻነትና መብት፧ ከማንኛውም አክራሪ ሃይማኖት በኩል አሥጊ ሁኔታ ይደቀንባቸዋል።ዩ ኤስ አሜሪካ ውስጥ አክራሪ ክርስቲያኖች ለምሳሌ ያህል Creationists የሚባሉት የዝግመታዊ ለውጥን ነባቤ-ቃል እንደማይቀበሉ ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን፧ በትምህርት ባለሥጣናትም ላይ ተጽእኖ እያሳረፉ ነው። ይህ አዝማሚያ፧ በአውሮፓ አገሮች፧ በፖላንድም ሆነ በጀርመንም እየታየ ነው« ብለዋል።