“ሃምሳ ሎሚ” ሶፍትዌር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 12.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

“ሃምሳ ሎሚ” ሶፍትዌር

በስድስት ወጣቶች የተሰራ “ሃምሳ ሎሚ”የተሰኘ ሶፍትዌር አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ሶፍትዌሩ የተቋማትን የአስተዳደር ስርዓት የማቅለል እና የማቀላጠፍ ዓላማ አለው፡፡ በጤና ተቋማት ተሞክሮ አጥጋቢ ውጤት ማስመዘገቡንም ተጠቃሚዎቹ መሰክረዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:03

ሶፍትዌሩ የድርጅቶችን የአስተዳደር ስርዓት ያቀላል

ጊዜው የዛሬ ሦስት ዓመት፣ ቦታው አዲስ አበባ፣ የጉዳዩ ባለቤቶች ደግሞ ወጣቶች፡፡ ቁጥራቸው ስድስት፣ ዕድሜያቸው ከ26 እስከ 30 ባለው ክልል ውስጥ ነው፡፡ አራቱ አምስት ኪሎ ከሚገኘው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ተመርቀው እዚህም እዚያም ሥራ እየሞከሩ ነው፡፡ ነገር ግን ልባቸው ጠብ የሚል ነገር ማግኘት አልቻሉም፡፡ የሞከሯቸው ሥራዎች ሁሉ ተመሳሳይ እና የተማሩትን ያህል የሚያሰራ ሆነው አላገኟቸውም፡፡ 

የሙከራ ውጤታቸውን እያነሱ ዓመታት ቀድመዋቸው ሥራ ከጀመሩ ሁለት ጓደኞቻቸው ጋር በየጊዜው ያወጋሉ፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ምሩቃን የሆኑት ሁለቱ ጓደኞቻቸው በሥራዎቻቸው ያጋጠሟቸውን ክፍተቶች እያነሱ ሲጥሉ አንድ ሀሳብ ብልጭ ይልላቸዋል፡፡ ከወጣቶቹ አንዱ ተመስገን ፍስሀ ያንን ጊዜ እንዲህ መለስ ብሎ ያስታውሳል፡፡

“ኢንዱስትሪ ላይ ብዙ ዓመት የሰሩ ባልደረቦቻችን ያዩዋቸው ክፍተቶች ነበሩ፡፡ አቅራቢዎች የሚያቀርቡት ሶፍትዌር እና ተጠቃሚዎች የሚፈልጉጽ ሶፍትዌር የተለያየ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ ሞባይልን ና cloud ከመጠቀም አንጻር በጣም ትልቅ ክፍተት ስላለ እና ስራውን በተሻላ መንገድ ማስኬድ የሚችሉ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ስለሆኑ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች መርጠን፣ በዚያ ላይ ተመስርተን፣ ስራ ጀመርን ማለት ነው፡፡”  

የታያቸውን ክፍተት ለመድፈን የጀመሩት ሥራ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ተቋማት አሰራራቸውን እንዲለውጡ እና እንዲያሻሽሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ማሻሻያው ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ሙያቸውን ለመጠቀም ተስማሙ፡፡ የድርጅቶች እና ተቋማት መሪዎች እና ሠራተኞች በተለይ በመረጃዎች ላይ ተመስርተው ውሳኔ ለመወሰን እንዲችሉ የሚያደርግ ሶፍትዌር ለመስራት መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ትኩረታቸውን ደግሞ በኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባለው የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ አደረጉ፡፡ 

“በብዙ ድርጅቶች የሚያጋጥመው ነገር ምንድነው? ለምሳሌ ምግብ ቤት ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ቅርንጫፍ ከፍተው ይሰራሉ ፡፡ ያኔ አስተዳደሩ ብዙም አይከብድም፡፡ ለምን?  ጥቂት ሰራተኞች ናቸው ያሉት፣ አቅርቦታቸው ትንሽ ነው፣ የሚመገቡት ሰውም አነስተኛ ነው፡፡ ግን ማደግ ሲጀምሩ፣ ሁለት ሶስት ቅርንጫፍ እያሰፉ ሲሄዱ፣ ተለቅ እያሉ ሲመጡ፣ ክልሎችና የተለያየ ቦታዎች ላይ ቅርንጫፎች ሲከፍቱ እነርሱን ማስተዳደር በጣም እየከበደ ይመጣል፡፡ ስለዚህ እዚህ መሀል ላይ ደግሞ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ፡፡ በሰራተኞችም ሆነ በተለያዩ አካሎች ብክነት፣ ስርቆት ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ንግዱ እንዳያድግ አንቀው የሚይዙት ናቸው፡፡ ሰው በተቻለ መጠን ንግዱን ለማሳደግ ይፈልጋል ግን አሁን ያሉት ተለምዶአዊ አሰራር ከባድ ስለሆነ እርሱን ነው ለመፍታት እየሞከረን ያለነው” ይላል ተመስገን፡፡   

በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ተለምዶአዊ አሰራሮችን ለመፍታት የሰሩት ሶፍትዌር ድርጅቶች ያላቸውን ሀብት በአግባቡ ማቀድ እና መቆጣጠር የሚያስቻላቸው በአንግሊዘኛው “Enterprise resource planning” የሚሉት አይነት ነው፡፡ ሶፍትዌሩ በ“cloud” እና ሞባይል ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተመስገን ይናገራል፡፡ የሶፍትዌሩ ተጠቃሚዎች ከየትኛውም ቦታ ሆነው ድርጅቶቻቸውን፣ ንግዶቻቸውን እና ተቋሞቻቸውን እንዲቆጣጠሩ አድርገው እንዳዘጋጁትም ይናገራል፡፡ ተመስገን የሶፍትዌሩን አሰራር ምሳሌ በመጥቀስ ያብራራል፡፡   

“ለምሳሌ ምግብ ቤት ያለው ሰው ወይም የሚያስተዳድረው ጠዋት ወደ ምግብ ቤቱ ላይገባ ይችላል፡፡ ሌሎች ስራዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ዋና መስሪያ ቤት ሆነው ወይም ሌላ ቦታ ሆኖ እዚያ ምግብ ቤት የሚከፈተው ነገር፣ ሁሉንም ነገር ሪፖርቱ በሞባይላቸው ላይ ልክ ፌስ ቡክ እንደሚያዩት ይደርሳቸዋል፡፡ ይሄ ነገር ደግሞ ከሩቅ ሆነው እንዲያስተዳድሩ፣ እንዲመሩ፣ የተሻለ ውሳኔ እንዲወስኑ ይረዳቸዋል ማለት ነው” ሲል ተመስገን የሶፍትዌሩን አሰራር ያብራራል፡፡    

ሶፍትዌሩ እንደ ምግብ ቤት እና ካፌ ከመሳሰሉ አገልግሎት መስጪያዎች ባሻገር ከፍ ባሉት የጤና ተቋማት፣ የዕቃ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች እና ፋብሪካዎች መዋል እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ይህ ደግሞ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈትሿል፡፡ ሶፍትዌሩን በተቋማቸው አስገጥመው መጠቀም ከጀመሩት ውስጥ አንጋፋው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንዱ ነው፡፡ የሆስፒታሉ የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው ጫኔ ሶፍትዌሩን በኦፕራሲዮን ክፍል እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ጠቀሜታውን እና ያመጣውን ለውጥ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

“ለቀዶ ህክምና ቀጠሮ የተሰጣቸው ታካሚዎችን መረጃ ዲጂታል በሆነ መልኩ ይገባል፡፡ አንደኛ ዳታው በስክሪን ላይ ይታያል፡፡ ከዚያ ሁለተኛ የሚያደርገው ታካሚዎቹ ቀዶ ህክምና ክፍል ከሚገቡበት እስከሚወጡበት ድረስ ያሉበትን ሁኔታ ያሳየናል፡፡ ያለቡት ሁኔታ ሁኔታ ማለት ቀዶ ህክምና ተጀመረ ወይ? ስንት ሰዓት ተጀመረ? ከዚያ ቀዶ ህክምናው በሂደት ላይ ከሆነ ምን ያህል ጊዘ ወሰደ? ከዚያ ከቀዶ ህክምና ወጥተው ወደማገገሚያ ሲገቡ የቀለም መለያው ይቀየራል፡፡ ሲወጡ ደግሞ ወደ አልጋ መዛወራቸውን በቀለም ያሳያል፡፡

መጀመሪያ ስንጠቀምበት የነበረው በእጅ የሚሰራ ነው፡፡ ይሄኛው ዲጂታል ነው፡፡ አንዱ እና ትልቁ ልዩነት ይሄ ነው፡፡ የቀድሞው የመረጃ ቋታችን በወረቀት የሚቀመጥ ሲሆን ይቀደዳል፣ ይጠፋል፡፡ በዚህኛው ዲጂታል ስናደርገው ለጥናትም ብትፈልገው ለሌላም ማስረጃ ብትፈልገው መረጃው በአስተማማኝ የሚቀመጥ ነው፡፡ ሶስተኛው በቴክኖሎጂ መሆኑ አሁን ለባለሙያዎች ብቻ ነው በቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ እንዲታይ የምናደርገው ግን ለሌላው ሰራተኛ እና ለታካሚዎች እንዲታይ የምናደርግበት ደረጃ ላይ ብናደርሰው ደግሞ የበለጠ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ በቅርበት መከታተል ያስችላቸዋል፡፡ እና ከፍ ያለ ለውጥ ነው ያለው፡፡” 

በሶፍትዌሩ የሚጠናቀረውን መረጃ በቀዶ ህክምና ክፍል ካሉ ባለሙያዎች ተሻግሮ ለታካሚዎች እና ለቤተሰቦቻቸው እንዲደርስ ለማድረግ ከግል ሚስጥር አጠባበቅ ጋር የተያያዘ የፖሊሲ ውሳኔ እንደሚያስፈልገው ዶ/ር ውለታው ይናገራሉ፡፡ የፖሊሲ መስተካከያ ከተደረገ ግን መረጃውን በሶፍትዌሩ አማካኝነት በቀላሉ ማቅረብ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ በኦፕሬሽን ክፍል ያዩትን የሶፍትዌሩን ጥቅም በሌሎች ክፍሎችም የማስፋፋት ዕቅድም አላቸው፡፡ በቅርቡም በሶፍትዌሩ አማካኝነት ለተመላላሽ ህክምና የሚመጡ ታካሚዎች ወረፋቸውን በቀላሉ የሚከታተሉበትን ስልት ተግባራዊ ለማድረግ አስበዋል፡፡ 

የሶፍትዌሩ አገልግሎት አዲስ አበባ ላይ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በአዲስ አበባ በስተሰሜን 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ሸዋ ሮቢት ከተማም ዘልቋል፡፡ በከተማይቱ በ2007 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይፋት ሆስፒታል ሶፍትዌሩን መጠቀም ጀምሯል፡፡ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ይመር ሶፍትዌሩን በከፊል እየተገለገሉበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

“መድኃኒት ቤት እና  እንግዳ መቀበያ ክፍል፣ ካርድ የሚወጣበት ቦታ እነዚህ ላይ ስርዓቱን እየሰራንበት ነው፡፡ ስርዓቱን የሰሩት ወጣቶች ወደ መክፈያ ማሽኑ ለማያያዝ ከገቢዎች  [መስሪያ ቤት] ጋር ያለውን ጣጣ አልጨረሱልንም፡፡ በዚህ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አልቻልንም እንጂ ስርዓቱ በጣም አዋጪ ነው፡፡ የሰው ኃይል ችግርን ይቀርፋል፡፡ ለምሳሌ ዶክተሩ ታካሚው ላይ ምርመራ ካደረገ በኋላ ያሰበውን የምርመራ አይነት እዚያው ቢሮ ቁጭ ብሎ ወረቀት ሳይባክን ስርዓቱን ተጠቅሞ ብቻ ቤተ ሙከራ (ላብራቶሪ) ልኮ እንዲሰራለት ማዘዝ ይችላል፡፡ በቤተ ሙከራው ያሉት ኮምፒውተር በመጠቀም የታዘዙትን ተቀብለው፣ በቀጥታ ሰርተው መልሰው  ወደ ዶክተሩ መላክ ይችላሉ፡፡ እዚህ ጋር አሁን መሀል ላይ ያለውን የሰው መመላለስ፣ የወረቀት መባከን ያስቀራል፡፡ ጊዜም ይቆጥባል፡፡ እንደገና ደግሞ ለወረቀት እና ለሌሎች ግዢ የሚውለውን  ገንዘብ ይቆጥባል፡፡ ከዚያ በተረፈ ደግሞ የተቀላጠፈ እና ፈጣን አሰራር ለማሰራት ያግዛል፡፡ ስርዓቱ መዘርጋቱ በሽተኛ እንዳይጉላላ ታካሚ መጥቶ በአጭር ጊዜ ተስተናግዶ፣ የሚፈልገውን ነገር አሰርቶ፣ ቶሎ እንዲመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው የሚያደርገው” ይላሉ አቶ መሐመድ ጠቀሜታውን ሲዘረዝሩ፡፡ 

ወጣቶቹ ሶፍትዌራቸውን ከገጠሙላቸው ከጤና ተቋማት እና ድርጅቶች ባሻገር የሆቴል እና መስተንግዶውን ዘርፍም ለመቀላቀል እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቅርንጫፎች ካሉት ለንደን ካፌ ጋር እየሰሩ እንደሚገኙ የአስተዳደር ሥራዎች ሥራ አስኪያጅ አምላክ ንጹህ ሰብስቤ ይናገራል፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደ የሆቴል ኤክስፖ ላይም ተሳትፈው ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እንዳዩ ይገልጻል፡፡ በግንባታ ላይ ያሉ ሆቴሎችን ከያዙ ሰዎች ጋር በቃል ደረጃ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ያስረዳል፡፡ አምላክ ንጹህ የእነሱ ሶፍትዌሮች በተጠቃሚዎች ተመራጭ የሚያደርጋቸው ሁለት ለየት ያሉ ምክንያቶች አሏቸው ይላል፡፡

“ሶፍትዌሩን እኛው ራሳችን እዚሁ ስለሰራነው በሀገሪቷ ካለው ሁኔታ አንጻር፣ የኢንተርኔቱም ከታሪፍም ከፍጥነቱም አንጻር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ ቦታዎች ያሉ መረጃዎችን ወደዋናው መስሪያ ቤት ተቀናጅቶ ሲመጣ በጣም ትልቅ የኢንተርኔት ፍጥነት የማይፈልግ፣ ኢንተርኔት ባገኘ ቁጥር መረጃውን መላክ የሚያስች፣ ወይ በEVDO አሊያም በCDMA ግንኙነት ከቅርንጫፎች ወደዋናው መስሪያ ቤት እንዲሄደው ነው ያደረግነው፡፡ ስለዚህ የሚጠቀመውን የኢንተርኔት bandwidth አነስተኛ እና በመደበኛ መሰረተ ልማት ሊሰራ የሚችል ነው፡፡ የተለየ የመረጃ ማዕከል ወይም እንደዚህ አይነት ትልልቅ ወጪዎች የሚያስወጡ ነገሮች በማይፈልግ መልኩ ነው የሰራነው፡፡ ይሄ ከሌላው ለየት እንልበታለን ብለን ነው ያሰብነው፡፡ ሌላው ደግሞ ተጠቃሚ በሚፈልገው ሀገር ውስጥ ባለ [ቋንቋ] አማርኛም ሊሆን ኦሮምኛ ወይም ትግርኛ የእኛን ስርዓት ማቅረብ መቻላችን ነው” ይላል፡፡

ስድስቱ ወጣቶች የዛሬ ሦስት ዓመት ሥራቸውን “ሀ” ብለው ሲጀምሩ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን የሚያበረታታው “አይስ አዲስ” ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ድርጅቱ ዛሬም ከገንዘብ እና ገበያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ምክር እና እገዛውን እየሰጣቸው ይገኛል፡፡ የኢንጀነሪንግ ባለሙያ ለሆኑት ወጣቶች ቴክኖሎጂውን ማቀላጠፍ እንጂ የሶፍትዌር ሽያጩ ጉዳይ ላይ እምብዛም መሆናቸውን ተመስገን ይናገራል፡፡ ይህንን ጉድለታቸውን ደግሞ “አይስ አዲስ” ሞልቶላቸዋል፡፡

የወጣቶቹ ሶፍትዌር አሁን ታዋቂ ስም አለው፡፡ “ሃምሳ ሎሚ” ከተሰኘው ስያሜው ጀርባ ስላለው ምክንያት ተመስገን አጠር እና ቅልብጭ ያለ ምላሽ አለው፡፡    

“ሃምሳ ሎሚ ያልነው ከአማርኛው አባባሉ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ እንደሚባለው ቴክኖሎጂ ሸክሙን ሲይዝልን እውነትም ስራው ጌጥ ይሆንልናል፣ ይቀላል ለማለት፣ እርሱን ለማሳየት ፈልገን ነው” ሲል ይደመድማል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic