ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ | ጤና እና አካባቢ | DW | 14.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ

የሴቶችና እናቶችን የስነተዋልዶ ጤና ለማሻሻል ከሚረዱ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነፍሰ ጡር እናቶች በሚገላገሉበት ጊዜ በተገቢዉ መንገድ በሰለጠኑ አዋላጆች መረዳት መቻላቸዉ ነዉ። ይህን እድል ያላገኙና የማያገኙ ደግሞ በተራዘመ ምጥ ምክንያት ለፊስቱላ ተጋልጠዉ የከፋ ህይወት ለመግፋት ይዳረጋሉ።

ቀድሞ አዲስ አበባ ፊስቱላ ሃኪም ቤት ይባል የነበረዉ የዛሬዉ ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ፤ የአዉስትራሊያ ተወላጆች በሆኑት ዶክተር ሬጅናልድና ካትሪን ሃምሊን ከተቋቋመ ዘንድሮ 40 ዓመቱን ያዘ። የጽንስና የማሕፀን ባለሙያ ሃኪሞቹ ወደኢትዮጵያ የሄዱትበት ምክንያት ይህ አልነበረም። ቀደም ሲል እንደተገለጸዉ ለጥቂት ዓመታት የሥራ ዉል ቢሆንም በዕለታዊ ሥራቸዉ የተመለከቱት በተለይም በለጋ እድሜያቸዉ ለእናትነት የበቁ ሴቶች ከምጥና ወሊድ ጋ በተገናኘ የሚገጥማቸዉ ፊስቱላ የተሰኘዉ የጤና እክል ቀሪ እድሜያቸዉን እነሱን በመርዳት እንዲያያሳልፉት ጠመዳቸዉ። ዶክተር ሃምሊን ሰሞኑን ኢትዮጵያ ዉስጥ የቆዩበትን 55ኛ ዓመት፤ በተማሩትና በሰለጠኑበት የማዋለድ ህክምና ሙያም ገንዘብ የሚሰበስቡበት ሳይሆን የሌሎች የጨለመ ህይወት የሚያፈኩበትን ይህን ግብረ ሠናይ ማከናወን የጀመሩበትን 40ኛ ዓመት እንዲሁም ወደዚች ምድር ከመጡ 90ኛ ዓመት አክበረዋል። ዶክተር ካትሪን ሃምሊን እና ባለቤታቸዉ ወደኢትጵያ በሄዱበት ጊዜ ልዕት ጸሐይ በመባል በሚታወቀዉ የዛሬዉ ጦር ኃይሎች ሃኪም ቤት ከማዋለድ ጎን ለጎን በምጥና ወሊድ ምክንያት ለፊስቱላ የተዳረጉ እናቶች ጤናቸዉ የሚመለስበት የህክምና እርዳታ ይሰጡ ነበር። አጋጣሚዉም ራሱን የቻለ ማዕከል እንዲቋም ምክንያት ሆነ እንደድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፌቨን ሀዲስ ገለጻ፤ እስካሁንም ከ40 ሺህ በላይ ህክምናዉ ተደርጎላቸዋል።

Äthiopien, Addis Abeba, Fistula Hospital, Dr. Catherine Hamlin

የአዲስ አበባዉ የፊስቱላ ሃኪም ቤት

ይህን የህክምና እርዳታም ዛሬ በዋና መዲና አዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ አይደለም። እንደወ/ሮ ፌቨን ገለጻ አብዛኞቹ የፊስቱላ ተጠቂዎች በተለያዩት የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች መገኘታቸዉን በማሰብም በመቀሌ፣ ባህርዳር፣ ሐረር፣ መቱ እና ይርጋለም ህክምናዉ የሚሰጥባቸዉ ማዕከላት ተስፋፍተዋል።

በወሊድ ፊስቱላ ለችግር የተጋለጡ እናቶችን አክሞ ወደቀድሞዉ ማኅበራዊ ህወታቸዉ እንዲመለሱ በማገዝ ተግባር ዓመታትን ያስቆጠረዉ ሥራ አዋላጅ ነርሶችን በማስተማርና በማሰልጠን በተለያዩ አካባቢዎች ወላዶችን በቅርበት እንዲረዱና የስነተዋልዶ ጤና ችግሮች እንዲቀንሱ እንዲሠሩ ወደማድረግ ተሸጋግሯል።

በአዋላጅ ነርስነት በመጀመሪያ ዲግሪ የሚመረቁትን ተማሪዎች ማሰልጠን ከተጀመረ ወዲህም ከ58 የሚበልጡ ትምህርታቸዉን አጠናቀዋል። በቅርቡም እንዲሁ 24 አዋላጅ ነርሶች ተመርቀዋል። ዛሬ ዘጠና ዓመት የሞላቸዉ ዶክተር ሃምሊን የእድሜያቸዉን አጋማሽ ከአርባ ሺህ የሚልቁ የፊስቱላ ተጠቂ እናቶችና ሴቶችን የጤና ይዞታ ለመለወጥ ማዋላቸዉን ያስተዋሉ የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን ሰጥተዋቸዋል። የዛሬ አምስት ዓመት ዘራይት ላይቭሊ አዋርድ የተሰኘዉ ተቋም እሳቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በፊስቱላ ጤናቸዉ ታዉኮ ማኅበራዊ ህይወታቸዉ እንዳልነበረ ሆኖ የተቸገሩ እናቶችና እህቶችን በህክምና ርዳታቸዉ መለወጣቸዉ ለሌሎች ችግሩ ለተስፋፋባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራትም አርአያነቱን በማዉሳት እንደሸለማቸዉ የድርጅቱ የፕሮግራምና የምርምር ሥራ አስኪያጅ ሻሮን ትሪኒቫስ ያስታዉሳሉ።

«ካትሪን ሃምሊን ሽልማቱን ያገኙት የዛሬu አምስት ዓመት ነዉ። ሽልማቱንም ያገኙት ለ50 ዓመታት አስቸጋሪዉን የፊስቱላ ችግር በማከም ላሳዩት ቁርጠኝነት ነዉ። በዚህ ህክምናም እጅግ ድሃ የሆኑትን የአፍሪቃ ሴቶች የጤና ሁኔታ አሻሽለዉ ክብራቸዉን እንዲያገኙ ለማድረግ ችለዋል። ለእሳቸዉ ሥራ እዉቅና የሰጠነዉ እሳቸዉ ያንን ተግባር በሚጀምሩበት ጊዜ ይህ ችግር ጭራሽ የሚያዉቀዉ እና ሊረዳዉ የሞከረም ስላልነበረ ነዉ። እናም ይህን ሃኪም ቤት በመገንባርና እጅግ በርካታ አዋላጆችንም በማሰልጠን፤ ራሳቸዉም የህክምናዉን ቀዶ ጥገባ በማካሄድ 93 በመቶ ስኬት በማስመዝገብ፤ ያሰለጠኗቸዉ አዋልጅ ነርሶችም ገጠር ዉስጥ ሁሉ ገብተዉ የሚያገለግሉ በመሆናቸዉ ችግሩን እንዳይከሰት ከመርዳት አንስቶ በፊስቱላ ምክንያት ከኅብረተሰቡ መገለል እንዳይኖር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ነዉ። »

ዶክተር ሃምሊን ዛሬ የዘጠና ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ሆነዉም ቁጭ የሚሉ ዓይነት አይደሉም ወ/ሮ ፌቨን እንደገለፁልን አዳዲስ ታማሚዎችን እየተቀበሉ ማነጋገሩ፤ እዚያ ተኝነተዉ የሚታከሙትንም መጎብኘቱ ካልተገቱ ሥራዎቻቸዉ ጥቂቶቹ ናቸዉ። በሙያቸዉ የብዙዎችን ህይወት መለወጥ የተሳካላቸዉ ዶክተር የኖቤል ሽልማት እንዲያገኙ ብዙዎች ይመኛሉ፤ ለእጩነት እንዲቀርቡም ከኢትዮጵያ በኩል ጥረት መደረጉ ተሰምቷል። ዘንድሮ በማኅበራዊ ዘርፎች ላበረከቱት አስተዋፅኦ የተሸለሙት ሌሎች ናቸዉ። ዶክተር ሃምሊን ግን ከሽልማት ሁሉ በሙያቸዉ ያገለገሏት የኢትዮጵያን የክብር ዜግነት ማግኘታቸዉን አልቀዉ ያያሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic