ሃሚልተን ናኪ፦በአፓርታይድ ወቅት ተመራማሪው ባለሙያ | አፍሪቃዊ ሥረ-መሠረት | DW | 30.04.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃዊ ሥረ-መሠረት

ሃሚልተን ናኪ፦በአፓርታይድ ወቅት ተመራማሪው ባለሙያ

ሃሚልተን ናኪ ከአትክልተኛነት እስከ የጤና ቤተ ሙከራ ረዳትነት የበቁ ሰው ናቸው። በአፓርታይድ ዘመን ይኖሩ የነበሩት እኝህ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊ ስማቸው በቀዶ ህክምና ሐኪም ክርስትያን በርናርድ በተከናወነው ከዓለም የመጀመሪያው የሰው ልብ ንቅለ ተከላ ጋር በተያያዘም ይነሳል።

የሃሚልተን ናኪ ልደትና ሞት
ሃሚልተን ናኪ እጎአ 1926 ገደማ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ሴንቴን በተላለችው መንደር (በዛሬው የኬፕ ታውን ምስራቃዊ ክፍል) ተወለዱ።የደሀ ቤተሰብ ልጅ በመሆናቸዉ ገና በለጋ ዕድሜያቸው እራሳቸውን ለማስተዳደር ተገድደዋል። ሃሚልተን ናኪ ባለትዳር፣ የአራት ወንዶች እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ። እ.ጎ.አ. ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ ም በልብ ድካም ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
የሃሚልተን ናኪ የመጀመሪያ ሥራ ምን ነበር?
ናኪ በ14 ዓመታቸዉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ  ስራ ፍለጋ ወደ ኬፕ ታውን ሄዱ። በኬፕ ታውን ዩኒቨርስቲ በአትክልተኛነት ተቀጥረው ይሰሩም ጀመር። በዩኒቨርሲቲውን ግቢ የቴኒስ ሜዳዎችን የመጠበቅ ሃላፊነትም ነበራቸው።

የሃሚልተን ናኪ ሥራ እንዴት ሊያድግ ቻለ?
ናኪ እ.ጎ.አ. በ 1954 በቤተ ሙከራ ውስጥ እንስሳትን ይንከባከቡ ነበር። የልብ ሐኪም እና ሳይንቲስት  ሮበርት ጎትዝ፣ ናኪ ልዩ ችሎታ እንዳላቸው የተገነዘቡትም በዚህ ወቅት ነው። እሳቸውም ናኪ እንስሳቶቹን እንዴት ለቀዶ ህክምና እንደሚያዘጋጁ አስተምረዋቸዋል። ኋላም ናኪ የምርምር ሕክምና ትምህርት ቤቱ ውስጥ የቤተ ሙከራ ቴክኒሽያን ሆነው መስራት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ በቤተ ሙከራ ውስጥ በእንስሳት አካላት ላይ ንቅለ ተከላ እንዴት ማከናወን እንደሚቻል ተማሩ። በሰዎች ላይ የመጀመሪያውን የልብ ንቅለ ተከላ ካከናወኑት የልብ ሐኪም ፕሮፌሰር ክሪስቲያን በርናርድ ጋር አብረው መስራት የጀመሩትም በዚህ አጋጣሚ ነው።  
ሃሚልተን ናኪ በሰዎች ላይ ንቅለ ተከላ አካሂደው ያውቃሉ?
አያውቁም። ናኪ በስራቸው ስኬታማ እየሆኑ የሄዱት ደቡብ አፍሪቃ በአፓርታይድ (የዘር መድሎ ሥርዓት) በምትገዛበት ወቅት ነው። ጥቁር ስለነበሩም ነጮች ቀዶ ህክምና የሚያካሄዱበት ክፍል እንዲሰሩ አይፈቀድላቸውም ነበር። ጥቁር የጤና ባለሙያ ሠራተኞችም ከነጭ ህሙማን ጋር እንዳይገናኙ በሕግ የተከለከለ ነበር። ስለሆነም የናኪ አስተዋፅዎ ለቀዶ ህክምና የሚያስፈልጉ ቴክኒካዊ ነገሮች ላይ ምርምር በማካሄድ የተወሰነ ነበር። 

ሃሚልተን ናኪ በመጀመሪያው የልብ ንቅለ ተከላ ወቅት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምን ነበር?
እ.ጎ.አ. ታህሳስ 3 ቀን 1967 በልብ ሐኪም ክሪስትያን በርናርድ በተመራው የቀዶ ህክምና ቡድን ውስጥ ሃሚልተን ናኪ አልተሳተፉም። የነቅሎ ተከላውም የተከናወነው ዴኒዝ ዳርቫል ከተባሉ ሟች ለጋሽ የተወሰደው ልብ ወደ ተቀባዩ ሉዊስ ዋሽካንስኪ በመትከል ነበር። 
በንቅለ ተከላው ወቅት ትልቅ ሚና የተጫወቱ ሰዎችን ለመዘከር በተቋቋመው የኬፕ ታውን የልብ ቤተ መዘክር መሠረት ናኪ ከክሪስትያን በርናንድ ጋር የነበራቸው ዋና ሚና በእንስሳት ላይ ማደንዘዣ የመስጠት ስራ ነበር። ይኼ ችሎታቸውም በቤተ ሙከራው የቀዶ ህክምና ረዳት ሆነው እንዲያገለግሉ ማዕረግ አሰጥቷቸዋል። እ.ጎ.አ. በ 2014 ቡሌቲን የተባለው የእንግሊዝ የሮያል የቀዶ ህክምና ኮሌጅ አንድ ጽሑፍ  «ናኪ አንድ የልብ ባይፓስ ቀዶ ህክምና የሚደረግለት ውሻን ማደንዘዣ በመስጠት ቤተ ሙከራ ውስጥ ላለው የቀድሞ ሥራ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ፈፅመዋል።» ይላል በዚህ ሚናቸዉም ናኪ ለበርናርድ ስኬት መንገዱን ካመቻቸው ቡድን አባል ነበሩ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:49

ሃሚልተን ናኪ

ሃሚልተን ናኪ በመጀመሪያው የልብ ንቅለ ተከላ የቀዶ ህክምና ወቅት መሳተፋቸውን የተለያዩ ምንጮች ይጠቅሳሉ። ታድያ እንዴት እንደዚህ አይነት ወሬ ሊሰራጭ ቻለ?
የአፓርታይድ ስርዓት በአገሪቱ ጥቁር ሕዝቦች የተገኘ ውጤትን ይሸፋፍን የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እነዚህን ኢፍትሃዊ ድርጊቶች የማጋለጥ ስራ ተሰርቷል። የናኪ ታሪክ ግን የብዙ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ታሪኮች የሚያንፀባርቅ ሲሆን ከአመት አመት ደግሞ ጎልቶ እንዲታይ ሆኗል።
 እ.ጎ.አ ግንቦት 29 ቀን 2005 ሃሚልተን ናኪ ከሞቱ በኋላ በርካታ ታዋቂ የሆኑ ጋዜጦች በህትመታቸው ናኪ በመጀመሪያው የሰው ልብ ነቅሎ ተከላ ጊዜ እንደተሳተፉ ገልጸዋል። ይህንንም ጽሑፋቸውን ኋላ ላይ አርመዉ  ማተም ነበረባቸው። እ.ጎ.አ. በ 2009 “የተሰወረ ልብ” የሚለው ዘጋቢ ፊልም የናኪ ሚና ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል። በቅርብ ዓመታትም የናኪ የቤተሰብ አባላት ንቅለ ተከላውን ያደረጉት ናኪ ነበሩ ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል። የናኪ ልጅ ቴምቢንኮሲ ናኪ “ነገሩ በጣም ነው የጎዳኝ ክሪስትያን በርናንድ ሁሉንም ሽልማት ሲያገኙ አባቴ ግን ምንም አላገኘም” ብለዋል።
ክሪስታና በርናርድ ስለ ሃሚልተን ናኪ አስተዋጽኦ ምን ይሉ ነበር?
ክሪስትያን በርናርድ በመጨረሻዎቹ የህይወት ዘመናቸው ለሃሚልተን ናኪ ከፍተኛ ክብር ሲገልፁ ተደምጠዋል። እ.ጎ.አ. በ 1993 ከአሶሺዬትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ሃሚልተን አጋጣሚውን አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ጥሩ የቀዶ ህክምና ሐኪም ሊወጣው ይችል ነበር” ብለዋል። እ.ጎ.አ በ 2001 ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብሎም ለብሪታኒያው ደይሊ ቴሌግራፍ እንደተናገሩት ናኪ “በልብ ንቅለ ተከላ መስክ በወቅቱ ከነበሩ ታላላቅ ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ነበር… ከእኔ ይልቅ ቴክኒካዊ ችሎታዎችም ነበሩት፣ በተለይም ለመስፋት በጣም ጥሩ እጆች ነበሩት።» ሲሉ ተናግረዋል።
ለመሆኑ ለሃሚልተን ናኪ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል?
እ.ጎ.አ. በ 2002 የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ ልዩ አስተዋፅዎ ላበረከቱ ደቡብ አፍሪቃውያን የሚሰጠውን የማፑንጉቡዌ የመዳብ ሽልማትን ለናኪ ሸልመዋቸዋል።
እ.ጎ.አ. በ 2003 ናኪ ከኬፕ ታውን ዩኒቨርስቲ የህክምና ሳይንስ የክብር ዲግሪም አግኝተዋል።
የሃሚልተን ናኪ ስም ወደፊት እንዴት ይታወሳል?
እ.ጎ.አ. በ 2007 ታዋቂው የሃሚልተን ናኪ ክሊኒካል ስኮላርሽፕ ተመስርቷል። አላማውም የበለጠ ምርምር ለማካሄድ አቅም የሌላቸውን ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎችን የመደግፍ ነው። ከዚህም ሌላ ፈተናዎችን ተቋቁመው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርምሮችን ለሚያካሂዱ ሰዎች በስማቸው የተሰየመ  ሽልማት እንዲሰጥ የምርምር ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም ወስኗል።
እ.ጎ.አ. በ 2017 በኬፕ ታውን የክርስቲያን በርናርድ ሆስፒታል ፊትለፊት የሚገኘው እና የሳላዛር ሜዳ በመባል የሚታወቀው ቦታ «ሀሚልተን ኒኪ» በሚል ስያሜ ተቀይሯል።

ቪድዮውን ይመልከቱ። 01:48

ሃሚልተን ናኪ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።