“ሁሉም ወገኖች ብሔር ለይተው ጥቃት ከመፈጸም፤ ኹከት ከመቀስቀስ እንዲቆጠቡ ጥሪ እናቀርባለን” በተ.መ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ | ይዘት | DW | 09.07.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ይዘት

“ሁሉም ወገኖች ብሔር ለይተው ጥቃት ከመፈጸም፤ ኹከት ከመቀስቀስ እንዲቆጠቡ ጥሪ እናቀርባለን” በተ.መ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ

“ለግድያው ተጠያቂ የሆኑ ወገኖችን ለፍትኅ ለማቅረብ አስቸኳይ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቹ እውነቱን የማወቅ፤ ፍትኅ እና ካሳ የማግኘት መብት አላቸው” በተ.መ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ

ቪድዮውን ይመልከቱ። 02:34

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በአፋጣኝ፣ በጥንቃቄ እና በገለልተኝነት እንዲጣራ ጠየቀ።  “ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቹ እውነቱን የማወቅ፤ ፍትኅ እና ካሳ የማግኘት መብት አላቸው” ያሉት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሩፐርት ኮልቪል በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ግልጋሎት መቋረጡን ኮንነዋል።

ድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ መገደሉ ከተሰማ በኋላ በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች 239 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 3500 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል። የኢንተርኔት አገልግሎቱም ካለፈው ረቡዕ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ማለዳ ጀምሮ እንደተቋረጠ ነው። 

ግድያው ተቃውሞ ስለመቀስቀሱ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መረጃ መድረሱን ያረጋገጡት ሩፐርት ኮልቪል “የተወሰኑት ተቃውሞዎች ሰላማዊ ቢሆኑም የተወሰኑት ከጅማሮው ኃይል የተቀላቀለባቸው ነበሩ። በደረሱን መረጃዎች መሠረት በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል መንገዶች ተዘግተዋል፤ ሕንፃዎች ተዘርፈው ተቃጥለዋል፤ በአዲስ አበባም የቦምብ ፍንዳታ እና የጥይት ተኩስ ነበር” ብለዋል። 

ቃል አቀባዩ “ከሐጫሉ ግድያ በኋላ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች የብሔር መልክ መያዛቸው እጅግ አሳስቦናል። ሁሉም ወገኖች በተለይ ወጣቶች ብሔር ለይተው ጥቃት ከመፈጸም፤ ኹከት ከመቀስቀስ እንዲቆጠቡ ጥሪ እናቀርባለን። ምክንያቱም እነዚህ ድርጊቶች ቀድሞም የነበሩ ውጥረቶችን  ያባብሳሉ” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። 

“የኢንተርኔት ግልጋሎት መዘጋት መረጃ የመፈለግ፣ የመቀበል እና የማካፈልን ጨምሮ ሐሳብን የመግለጽ መብትን ፍትኃዊ ባልሆነ መንገድ ስለሚገድብና ውጥረትን የበለጠ ሊያባብስ ስለሚችል በተለይ አሳሳቢ ነው” ያሉት ሩፐርት ኮልቪል የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ግልጋሎቱን ወደ ሥራ እንዲመልስ ጥሪ አቅርበዋል። 

“ባለሥልጣናቱ ሐጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ መታሰራቸውን አስታውቀዋል። ለግድያው ተጠያቂ የሆኑ ወገኖችን ለፍትኅ ለማቅረብ አስቸኳይ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።  ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቹ እውነቱን የማወቅ፤ ፍትኅ እና ካሳ የማግኘት መብት አላቸው። እኛም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በእነዚህ ተቃውሞዎች ሊፈጸሙ የሚችሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ሲመረምር እገዛ ለማቅረብ ዝግጁ ነን” ሲሉም ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ
 

በተጨማሪm አንብ