ሁለቱ የ2021 የኖቤል ተሸላሚ ጀርመናውያን ሊቃውንት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 13.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ሁለቱ የ2021 የኖቤል ተሸላሚ ጀርመናውያን ሊቃውንት

ስዊድን ስቶኮልም የሚገኘው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ  ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ዘርፎች የኖቬል ሽልማትን ሰጥቷል። ክላውስ ሀሰልማን እና ቤንጃሚን ሊስት የተባሉ ሁለት የጀርመን ሳይንቲስቶችም በፊዚክስና በኬሚስትሪ ዘርፍ ሽልማት አግኝተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:11

ሁለቱ የጀርመን የ 2021 የኖቤል ተሸላሚ  ሊቃውንት 


ስዊድን ስቶኮልም የሚገኘው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ  ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ዘርፎች የኖቬል ሽልማትን ሰጥቷል።ሁለት የጀርመን ሳይንቲስቶችም ፣ በፊዚክስ እና በኬሚስትሪ መስክ  የኖቤል ሽልማትን ተጋርተዋል። የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በእነዚህ ሳይንቲስቶች  ማንነትና ስራ ላይ ያተኩራል። 
ስዊድን ስቶኮልም የሚገኘው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በተለያዩ ዘርፎች የ2021 የኖቬል ሽልማት አሸናፊዎችን ያለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።ክላውስ ሀሰልማን እና ቤንጃሚን ሊስት የተባሉ ሁለት የጀርመን ሳይንቲስቶችም የሽልማቱ ተቋዳሽ ናቸው።
የጀርመናዊው የክላውስ  ፈርዲናንድ ሃስልማን  የኖቬል ሽልማት  በፊዚክስ ዘርፍ ሲሆን፤  ከአሜሪካዊ ሳዩኩሮ ማናቤ እና ከጣሊያናዊው ጂዮርጂዮ ፓሪሲ ጋር  ነበር ሽልማቱን የተጋሩት።
ሊቃውንቱ ሽልማቱን ያሸነፉት  እንደ ኖቬል ኮሚቴው በምድር ላይ እየተከሰተ ያለውን ውስብስብ  የዓየር ንብረት ለውጥ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ጉልህ አስተዋፅዖ በማበርከታቸው ነው።
«የሮያል ስዊድን የሳይንስ አካዳሚ የ 2021 የፊዚክስ  የኖቤል ሽልማትን የተወሳሰቡ  አካላዊ ስርዓቶችን  ግንዛቤ እንደረዳ  አስተዋፅኦ ላበረከቱት መሰረታዊ  ግኝቶች   ለመስጠት ዛሬ ወስኗል።የሽልማቱ ግማሽ  ለሱኩሮ ማናቤ  እና ለክላውስ ሃስልማን በጋራ ይሰጣል። የምድርን የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት በመለካት እና በተጨባጥ  ምሳሌ   የአለም ሙቀት መጨመርን በአስተማማኝ ሁኔታ በመተንበያቸው። ሌላው ግማሽ ከ«አቶሞች» እስከ  ፕላኔት ድረስ በሚታዩ አካላዊ  ስርዓቶች ምስቅልቅል  እና መለዋወጥ ላይ  ለሰራው ግኝት ለጆርጆ  ፓሪሲ  ይሰጣል።»


ጀርመናዊው የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ ክላውስ  ሀሰልማን በጀርመን  ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር  እና የማክስ ፕላንክ የሜትሮሎጂ ተቋም ዳይሬክተር ናቸው።በጎርጎሮሳዉያኑ 1931 ዓ/ም  ጀርመን ሀምቡርግ የተወለዱት ክላውስ ፈርዲናንድ ሀስልማን  የ2 ዓመት ልጅ እያሉ  ወላጆቻቸው ወደ እንግሊዝ በመሄዳቸው  እዚያው  እንግሊዝ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከካምብሪጅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማጠቃለያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ  በ1949 ዓ/ም ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ጀርመን በመመለስ በፊዚክስና በሂሳብ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን  በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ ተከታትለዋል።የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በፊዚክስ እና በፈሳሽች  የተለዋዋጭነት ባህሪ ላይ በሐምሌ 1957 ዓ/ም ከጎቲገን ዩኒቨርሲቲ የማክስ ፕላንክ ጥናት ተቋም አግኝተዋል። ላለፉት በርካታ ዓመታትም የውቅያኖሶችን እና የመሬትን አየር ንብረት በሳተላይት ቴክኖሎጂ በርቀት መረዳት ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን ይሰራሉ።የ 2021 የፊዚክስ የኖቤል ሽልማት ያስገኘላቸው ግኝትም በዚሁ ከአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያተኩር  መሆኑን የኖቬል ኮሚቴ አባሉ ፕሮፈሰር ጆን ቢትላውፈር  ገልፀዋል።
«ክላውስ ሃስልማን  በፍጥነት በሚለዋወጠው የአየር ሁኔታ እና በቀስታ በሚለዋወጠው የአየር ንብረት መካከል አሳማኝ ትንተና አደረገ። የውሃ ሞለኪውሎች በሚያደርጉት ፈጣን ግጭት የአበባ ዱቄቶች  ቀስ በቀስ  እንዲጠፉ ያደርጋል።ከሚለው የአነስታይን የእንቅስቃሴ ፅንሰ ሀሳብ በመነሳት የአየር ሁኔታ በቀናት የጊዜ ሚዛን በውቅያኖሶችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መተንበይ ችሏል። በእነዚህ ሀሳቦች የበለጠ በመግፋት  ልኬቶችን፣ ምልከታዎች እና ማሳያዎችን በማነፃፀር የአንድን የተለዬ አካላዊ ሂደት አሻራ በአየር ንብረት ሥርዓቱ  ውስጥ ስልታዊና አህዛዊ  በሆነ መንገድ  ገንብቷል።»


 በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን  እያሳሰበ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ በ1960 ዎቹ  ጃፓናዊ አሜሪካዊው ሲዩኩራ ማናቤ በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን መጨመር በምድር  ላይ የሙቀት መጠንን እንዴት እንደሚጨምር አሳይተዋል። የእሳቸው ሥራ ለአሁኑ የአየር ንብረት ምርምር መሠረት ጥሏል። ከማናቤ ግኝት ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ክላውስ ሃሰልማን የአየር ንብረትንና  እና የአየር ሁኔታን አንድ ላይ የሚያገናኝ  ሀሳብ በመፍጠር፤ የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭ እና የተዘበራረቀ ሲሆን የአየር ንብረት  ለምን የማይለዋወጥ ሆነ ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። እንዲሁም የተፈጥሮ ክስተቶች እና የሰዎች እንቅስቃሴ በአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ የሚያሳድረውን  ተፅዕኖ ለመለየት የሚያስችሉ ዘዴዎችን በምርምራቸው አመላክተዋል።ይህ   ምርምር  በከባቢ አየር ውስጥ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን በሰው ልጆች የ«ካርቦንዳይኦክሳይድ» ልቀት ሳቢያ  መሆኑን ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ ውሏል። የስራ ባልደረባቸው ፕሮፌሰር ጆሀን ስቲፍ  እንደሚሉት የሀልስማን ግኝት ለፓሪስ አየር ንብረት ስምምነት አበርክቶቱ ከፍተኛ  ነው።
«ለኔ በጣም ግልፅ ነው። ለምን  የኖቤል ሽልማቱን  እንዳገኘ።ለምን ከዚያም በላይ እንደሚገባው ። ምክንያቱም  እሱ  የስራው  ስራ  በአሁኑ ወቅት  የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች  የተከሰተ  መሆኑን  መናገር እንድንችል አድርጎናል ።እና ግልፅ ነው። ያለ ሃስልማን ስራ የፓሪስ አየር ንብረት ስምምነት በጭራሽ ሊኖር አይችልም ነበር። ለዚያ አስፈላጊ የሆነው ነገር ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች የተከሰተ መሆኑን  በማያሻማ መንገድ  ማቅረቡ ነበር። ያ የሃንስማን  ታላቅ ሳይንሳዊ አስተዋፅኦ ነበር።» 
የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንቲስቱ ክላውስ ሀሰልማን በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማትን ባገኙ ማግስት ቤንጃሚን ሊስት የተባሉ የስነ-ቅመማ ሊቅ  ደግሞ በኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ያገኙ ሁለተኛው የጀርመን ሳይንቲስት ናቸው።
 የ 53 ዓመቱ ኬሚስት እና በጀርመን ሙልሃይም የማክስ ፕላንክ የድንጋይ ከሰል ምርምር ዳይሬክተር ሲሆኑ ፤ ሽልማቱን ያሸነፉት በኬሚስትሪ ዘርፍ ከአሜሪካዊው ዴቪድ ማክሚላን  ጋር በጋራ ነው።


ሣይንቲስቶቹ የተሸለሙት ቤተ-ሙከራ  ውስጥ በሚደረጉ ጥናቶች ለሞለኪውል ግንባታ ሲውል የነበረ “ኦርጋኖ ካታሊሲስ” የተሰኘ አስተማማኝና ውጤቱ  ከፍተኛ የሆነ አዲስ ቁስ በማበልፀጋቸው ነው፡፡የኖቬል ኮሚቴ አባሏ ፓርሚላኒ  ቪቱንግ ስግኝቱ የውህድ ቅመማ ስራን ሥራ ቀላል  ያደረገ  በማለት ይገልፁታል።
« ጉዳዩ የውህዶችን «ሞለኪውሎች» ስለመስራት ነው። እናም ሎሬቶቹ  ያማረ እና አጋዥ  መሣሪያ ነው ያበለፀጉት። ቀላልና አንድ ሰው ሊገነዘበው የሚችል። ዓለማችን በ«ሞሎኪዩሎች» የተሞላች ነች። ከምንተነፍሰው ኦክስጅን ጀምሮ እስከ ለሽታዎች ፈውስ የሚቀመሙ ውስብስብ  መድሃኒቶች ድረስ። ህይወት ያላቸው ነገሮች እና  ሰዎችን የመሳሰሉ በተለዩና በተወሳሰቡ ሞሎኪዩሎች የተገነቡ ፍጥረታትም አሉ። በእርግጥ ሁሉም ዓይነት ቁሳቁሶች ፣ ፕላስቲኮች ፣ ሽቶ ፣ የምግብ ጣዕም ማሳመሪያዎች፣ ባትሪዎች እና መድኃኒቶችም  «ሞለኪውሎች» ናቸው። ሞለኪውሎችን ለመሥራት ግን የተለያዩ «አቶሞች»ን አንድ ላይ ማገናኘት አለብን።» 
ነገር ግን ፓሚላኒ እንደሚሉት ቀደም ሲል ይህ ቀላል ስራ አልነበረም ። ምክንያቱም የአብዛኛዎቹ ውህዶች ምላሽ  በጣም አዝጋሚ ነበርና።ያ በመሆኑ እስከ ጎርጎሪያኑ 2000 ዓ/ም ድረስ  ስለ ሁለት ዓይነት አነቃቂ ውህዶች ወይም «ካታሊስት ኢንዛይም» ብቻ ነበር የሚታወቀው ከዚያ በኃላ ግን የነ ቤያሚን ሊስት ግኝት ሁኔታውን ቀየረ ይላሉ ፓሚላኒ ቤቱንግ ።


«ነገር ግን  በ 2000  ዓ/ም ሁሉም ነገር ተቀየረ ። ከዚያም ቤያሚን ሊስት  እና ዴቪድ ማክሚላን ፣ ልክ እንደ ትልልቅ ውህዶችና እና የብረት አነቃቂዎች ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት  ትንንሽ  ተፈጥሯዊ «ሞለኪውሎችን» መጠቀም እንደሚቻል ይፋ አደረጉ። እነዚህ  ትክክለኛ ፣ ፈጣን እና ለአካባቢ  ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ምላሾች ነበሩ። ግኝቶቹ የውህድ «ሞለኪውሎች»ን እንዴት ማቀናጀት እንደሚቻል ሙሉ በሙሉ አዲስ መነሳሳት ፈጠሩ። ይህ አዲስ ግኝትና አስተሳሰብ  ዛሬ በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላል።  ለምሳሌ ፣ በመድኃኒት ግኝት እና ጥሩ ውህዶችን በማምረት ረገድ  የሰው ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ነው። »
ጀርመናዊው ተመራማሪ ቤንጃሚን  ሊስት በጀርመን  ፍራንክፈርት  በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር ጥር 11 ቀን 1968 ዓ/ም የተወለዱ ሲሆን፤የአንደናኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ያጠናቀቁት በዚሁ በትውልድ አካባቢያቸው ነው።የ53 ዓመቱ ሳይንቲስት  ቤያሚን ሊስት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በኬሚስትሪ  ከበርሊን ዩኒቨርስቲ ሲሆን ፣የዶክትሬት ዲግሪያቸውን  ደግሞ ፍራንክፈርት በሚገኘው  የጎተ ዩኒቨርሲቲ  ነበር። ተመራማሪው  በአሁኑ ጊዜ በኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና በማክስ ፕላንክ የድንጋይ ከሰል ምርምር ተቋም ዳይሬክተር እና ፕሮፌሰር ሆነው ይሠራሉ። 
ተመራማሪው ያለፈው ሳምንት ጥቅምት 6  ቀን 2021 ዓ/ም ከተጋሩት የኬሚስትሪ የኖቬል ሽልማት በጨማሪ ላለፉት በርካታ ዓመታት  በሳይንሱ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅኦ  ከ30 በላይ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ከጎርጎሪያኑ 1901 ጀምሮ  የዘንድሮዎቹን ተሸላሞዎች ጨምሮ  በኬሚስትሪ 34 ፣ በፊዚክስ ዘርፍ ደግሞ 28 ጀርመናዉያን የኖቬል ሽልማት አግኝተዋል ።ከነዚህም  ውስጥ በንድፈ ሀሳብ ፊዚክስ ባደረገው ምርምር  በተለይም ለፎቶ ኤሌክትሪክ ውጤት ሕግ ግኝት  በ1921 ዓ/ም የኖቬል ሽልማት ያገኘው ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን ይገኝበታል። 


ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic