ሁለተኛ ቀኑን የያዘዉ የነቀምት ከተማ ተቃዉሞ  | ኢትዮጵያ | DW | 27.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ሁለተኛ ቀኑን የያዘዉ የነቀምት ከተማ ተቃዉሞ 

በኦሮሚያ ክልል በነቀምት ከተማ በትናንትናዉ እለት በተቀሰቀሰዉ ግጭት አንድ ሰዉ መገደሉና 11 ሰዎች መቁሰላቸዉ ተገለፀ።  በዛሬዉ እለትም በከተማዋ ዉጥረት መንገሱንና መደበኛ አገልግሎቶች መቋረጣቸዉን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:10

«በተቃዉሞዉ 11 ሰወች ቆስለዋል አንድ ሰዉ ተገድሏል»አቶ ሙላቱ ገመቹ


የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ከእስር የተፈቱ የፓርቲዉ አመራሮች ከነቀምት ከተማ ህዝብ በተደረገላቸዉ «የእንኳን ደስ ያላችሁ» ጥሪ መሰረት ባለፈዉ እሁድ ወደ ቦታዉ አምርተዉ ነበር።  ይሁን እንጅ ከቦታዉ ሊደርሱ ጥቂት ኪሎሜትሮች ሲቀራቸዉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ወደ ከተማዉ እንዳይገቡ  በጸጥታ ሀይሎች መከልከላቸዉን የፓርቲዉ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ይህንን ተከትሎም  ለመቀበል በዝግጅት ላይ የነበረዉ የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ በትናትናዉ እለት ከጸጥታ ሀይሎች ጋር ወደ ግጭት መግባቱን ገልጸዋል።አቶ ሙላቱ ዛሬ ደረሰኝ ባሉት መረጃ መሰረትም በርካታ ሰወች መጎዳታቸዉንና በዚህ የተነሳም ህዝቡ መንገዶች ዘግቶ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
«እኔም አብሬ ሄጀ ነበር እዚያዉ አድረን ነዉ አብረን የተመለስነዉ።እሁድ ዕለት ከትናናት ወዲያ ማታ እዚያዉ ታግተን ነዉ ያደርነዉ።ከትናንት ጀምሮ በነቀምት በኩል

ጊምቢ፣ደምቢደሎ፣አሶሳ የሚወስዱ የየብስ መንገድ የለም።አዉቶብስም አይደርስም ህዝብ አግዶታል።መንገድ ተዘግቷል።ዛሬ ደግሞ ወደ 11 ሰወች በጥይት እንደተመቱ ነዉ።አሁን ሆስፒታል ገብተዋል። አንድ ሰዉ እንደሞተ ነዉ የተነገረኝ።ዛሬ የደረሰኝ ሪፖርት ይህ ነዉ።»
ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የነቀምት ከተማ ነዋሪ በበኩላቸዉ በዛሬዉ እለት በከተማዋ  ከፍተኛ ዉጥረት መንገሱንና መደበኛ አገልግሎቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከትናንት ጀምሮ መዘጋታቸዉንም ገልጸዋል።  በተቃዉሞ ሳቢያ የተዘጉ መንገዶችን  ለማስከፈትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ የፀጥታ ሀይሎች በአካባቢዉ  እየተዘዋወሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በከተማዋ የሚገኘዉ የወለጋ ዩንቨርሲቲ በትናንትናዉ እለት የተማሪወች ምዝገባ እያከሄደ ነበረ ያሉት ነዋሪዉ ፤በዛሬዉ ዕለት ግን በዩንቨርሲቲዉ ዉጥረት መንገሱንና  በርከት ያሉ የመከላከያ

ሰራዊት አባላት በአካባቢዉ ሰፍረዉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ድምፅ የደረሰዉ ጉዳት እንዳሳዘናቸዉ የሚናገሩት  የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ፤ ሁኔታዉን አቤት ለማለት እንኳ መደበኛ አስተዳደር ባለመኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሁኔታዉን የበለጠ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ከታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ወዲህ በዉልቂጤ፣በጎንደር፣በባህርዳር ከትናንትናዉ ዕለት  ጀምሮ ደግሞ በነቀምትና በደሚቢዶሎ ከተሞች ተቃዉሞዎች ተካሂደዋል።ይህንን በተመለከተም  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቋቋመዉ የኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት በዛሬዉ እለት መግለጫ አዉጥቷል። በኦሮሚያ ክልል በተለይም በነቀምትና በደምቢዶሎ አካባቢወች በእነዚህ ሁለትና ሶስት ቀናት፤ ፅሕፈት ቤቱ፤ «ህገ ወጥ አካላት» ያላቸዉ ወገኖች  የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት እያወኩ መሆናቸዉን  አመልክቶ  እነዚህ አካላት ከድርጊታቸዉ የማይቆጠቡ ከሆነ  የፀጥታ ሀይሎች አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸዉን ፅ/ቤቱ  ገልጿል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

Audios and videos on the topic