ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ | ዓለም | DW | 08.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ

የተቀረዉ በጥፋተኝነት ሥሜት-ይቆዝማል።ሌላዉ ድል አድራጊዎች ይበቀሉኛል በሚል ሥጋት--ይብሰከሰካል።ሥጋት ፍራቱ ያየለበት ልጅ፤ሚስቱን እየገደለ እራሱን ያጠፋል።በርሊን ዉስጥ የዚያ ሰሞን ዉዶቹን እያጠፋ-እራሱን ያጠፋዉ ሰዉ ቁጥር በአምስት እጥፍ ጨምሮ ነበር

እስካሁን በሚታወቀዉ የዓለም ታሪክ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያለቀበት፤ ብዙ ሐብት-ንብረት የወደመበት እና የበርካታ መንግሥታት ጦር የተዋጋበት ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ዛሬ 70ኛ ዓመቱን ደፈነ።የጦርነቱ ፍፃሜ የታወጀዉ የናትሴ ጀርመን ጦር አዛዦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለጠላቶቻቸዉ፤ ለተባባሪዎቹ መንግሥታት እጃቸዉን መስጠታቸዉን ሲያስታዉቁ ነበር። የጦርነቱ ፍፃሜ፤- ሠላም የመስፈኑ ማረጋገጪያ ቢሆንም ብዙዎቹ የጀርመን ዜጎች እዉነታዉን ለመቀበል ጊዜ ወስዶባቸዋል።ዛራሕ ዩዲት ሆፍማን የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ ሰብሰብ አድሮጎ አጠናቅሮታል።

ግንቦት-9 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የትንሺቱ ግላትስ መንደር ነዋሪ ወይዘሮ ሒልደጋርት ታይነርት፤ «ጦርነቱ አበቃ፤ የጠመንጃዉ ላንቃም ተዘጋ» ፃፉ በባለቤታቸዉ ማስታወሻ ደብተር ላይ።ላቲን አስተማሪዉ ባለቤታቸዉ ዮሐንስ ታይነርት ፅሁፉን አነበቡ።ብዕራቸዉን አነሱ---ሊፅፉ።

ዋዜማዉ። በርሊን-ካርልስሆርስት።ግንቦት 8 1945 ከምሽቱ 5፤ ከ45።የጀርመን ጦር ሐይሎች ጠቅላይ ዕዝ ዋና አዛዥ ማርሻል ቪልሔልም ካይተል-የጀርመን ጦር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠቱን የሚያረጋግጠዉን ፅሁፍ ፈረሙ።

ማርሻሉ በትክክለኛዉ ሠነድ ላይ ስም ፊርማቸዉን ያሰፈሩት በርግጥ በማግሥቱ ነበር።ግንቦት 9

ያም ሆኖ-የማርሻሉ ፊርማ፤ ጀርመን እጅ መስጠትዋ በሕጋዊ-ሰነድ እንዲረጋገጥ የሶቬት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን ያደረጉትን ግፊት ከመቀበል ባለፍ ሌላዉ የጀርመን ጦር አዛዥ ጄኔራል አልፍሬድ ዮድል ግንቦት ሥምንት ራይም-ፈረንሳይ ዉስጥ ያወጁትን ከመድገም ዉጪ ትርጉም አልነበረዉም።

«እኛ ከዚሕ በታች የፈርምነዉ የጀርመን ጦር የበላይ አዛዦች፤-የምድር፤የባሕር፤ የአየር ጦራችን እና ባሁኑ ወቅት በዕዝ ጠገጋችን ሥር ከቀዩ ጦር ጋር የሚዋጋዉ ሌላዉ ሐይላችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠቱን እናስታዉቃለን።»

ጀርመን እጅ መስጠትዋትን ከሐገሪቱ መንግሥት ይልቅ የጦሩ አዛዞች እንዲያረጋግጡ፤ ስታሊን ያደረጉትን ግፊት ብሪታንያም ቶሎ ነበር የተቀበለችዉ።በሁለት ምክንያት።

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ወቅት-የጀርመን መንግሥት መሸነፉን አምኖ እጅ ሲሰጥ፤-ጦሩ በፖለቲካዉ እንጂ «በጦር ሜዳዉ አልተሸነፍንም ነበር-ብሎ ማንገራገሩ እንዳይደገም-አንድ። በፊርማዉ ሥነ-ሥርዓት የሶቬት ሕብረት ከፍተኛ የጦር አዛዞች እንዲገኙ እድል ለመስጠት-ሁለት።

የራይሙ-አዋጅም ሆነ የበርሊኑ ፊርማ አዶልፍ ሒትለር ከሞቱ በሕዋላ የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን ከያዙት ከካርል ደኒትስ ጋር በመነጋገር የተደረገ ነበር።ይሕ፤ የታሪክ አጥኚ ዮሐነስ ሆርተር እንደሚሉት የሕግ አተረጋጎም ክፍተት መፍጠሩ አልቀረም።(አዋጁ) ካስነሳዉ ክርክር አንዱ የጀርመን ጦር እንጂ፤ መንግሥት እጅ አልሰጠም-የሚለዉ የሕጋዊነት ጥያቄ ነዉ።»

በዚሕም ምክንያት ጦሩ እጅ መስጠቱ ከታወጀም በኋላ ደኒትስ የሚመሩት መንግሥት እስከ ግንቦት 23 ድረስ ሥልጣን እንደያዘ ነበር።

የጦር፤የፖለቲካ፤የሕጉን ጣጣ ከሩቅ የሚመለከተዉ ወይም ብዙም ያልገባዉ አብዛኛዉ ጀርመናዊ ግን ቀጣዩ ሠላም ይሁን ጦርነት ግራ-እደተጋባ ነበር።የያኔዋ ወጣት ኤሽተር ቤያራኖ ግን ለየት ሳትል አልቀረችም።ከድል አድራጊዎቹ መሐል ገብታ ጭፈራ-ሙዚቃዉን ታስነካዋለች።

«ዙሪያዉን ከበዉ ይደንሳሉ፤ እኔም መሐላቸዉ ሆኜ ሙዚቃ እጫወት ነበር።ነፃነቴ ነበር።ነፃ መዉጣታችንን አዉቀን ነበር።»

ወጣትዋ አይሁድ በመሆኗ ከተጋዘችበት ማጎሪያ ሠፈር በሕይወት ያተረፋትም ሙዚቀኝነቷ ነበር።ዘንድሮ-ዘጠና ዓመታቸዉ።

በየማጎሪያ ጣቢያዉ የነበረዉ፤ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለዉ፤ የጦር ምርኮኛዉ፤ የቀን ሠራተኛዉ፤ ሥደተኛዉ ምን ቅጡ-በተመሰቃቀለችዉ ጀርመን ምግብ፤ መጠጥ፤ መጠለያዉን ከማሰላሰል ባለፍ ነፃ በመዉጣቱ ለመጨፈር አልታደለም።

የተቀረዉ በጥፋተኝነት ሥሜት-ይቆዝማል።ሌላዉ ድል አድራጊዎች ይበቀሉኛል በሚል ሥጋት--ይብሰከሰካል።ሥጋት ፍራቱ ያየለበት ልጅ፤ሚስቱን እየገደለ እራሱን ያጠፋል።በርሊን ዉስጥ የዚያ ሰሞን ዉዶቹን እያጠፋ-እራሱን ያጠፋዉ ሰዉ ቁጥር በአምስት እጥፍ ጨምሮ ነበር።ደሚን በተባለች አንዲት ትንሽ ከተማ ብቻ ከ700 እስከ 1000 የሚገመት ነዋሪ እራሱን አጥፍቷል።

መምሕር ታይነርት አንዱ ናቸዉ።«ጦርነቱ አበቃ፤ የጠመንጃዉ ላንቃም ተዘጋ» ከሚለዉ የባለቤታቸዉ ፅሁፍ ግርጌ፤ «አፍታ ነዉ የቀረዉ።ከዚያ ሁሉም ያበቃል።ለዘላለም» የሚል አረፍተ ነገር አከሉበት።እና ሽጉጣቸዉን መዘዙ፤ መጀመሪያ ሚስታቸዉን ቀጥሎ እራሳቸዉን ገደሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic