1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነትና አፍሪቃዉያን

ዓርብ፣ ሚያዝያ 30 2007

አፍሪቃዉያኑ በማያዉቁት ጦርነት ሞተዉ፤ ቆስለዉ፤ተጎሳቁለዉ አዉሮጳን ከፋሽታዊ አገዛዝ ነፃ አዉጥተዋል።ለከፈሉት ዋጋ የተከፈላቸዉ ግን ትንሽ ወይም ምንም ነዉ።የከፋዉ ደግሞ የአፍሪቃዉያን ገድል-መስዋዕትነት ጀርመናዉያንን ጨምሮ ብዙዎቹ አዉሮጳዉያን ከቁብ አለመቁጠራቸዉ ወይም አለማወቃቸዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1FMQ9
ምስል public domain

 

በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አፍሪቃዉያን ከያኔ ቅኝ ገዢዎቻቸዉ ወታደሮች ጋር ሆነዉ የፋሽስት ሐይላትን ተዋግተዋል። በጦርነቱ መሐል የፈንጂና የመድፍ ጥይት ማብረጃ እየሆኑ አልቀዋል።ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ ለሟች ቤተሰቦች ካሳ፤ ለቁስለኞች መታከሚያ ለተረፉት መጦሪያ የሠጣቸዉ የለም።ካሳና ድጎማዉ ቀርቶ፤ የዶቼ ቬለዎቹ ቴሬሳ ክሪኒንገርና ሳሌሕ ምዋናሚሎንጎ እንደሚሉት አፍሪቃዉያን አዉሮጳን ከፋሽስቶች ነፃ ለማዉጣት ሥለከፈሉት መስዋዕትነት የሚተርክ ምዕራፍ በጀርመን መፅሐፍት ዉስጥ መገኘቱ አጠራጣሪ ነዉ።

አልበርት ኩኒዩኩ-ዘጠና ሰወስት ዓመታቸዉ ነዉ።ምርኩዝ ግን አያስፈልጋቸዉም።የኮንጎ የጥንት ተዋጊዎች ማሕበር መሪ ናቸዉ።በወጣትነታቸዉ የብሪታኒያ-እና የቤልጂግ ተጣማሪ ጦር ባልደረባ ሆነዉ ሕንድና ምያንማር ዉስጥ ከጃፓኖች ጋር ተዋግተዋል።

«የተሳፍርንበት አዉሮፕላን ሲነሳ ባርባር አለኝ።ቤተሰቦቼን ዳግም አላያቸዉም።አስከሬኔ እንኳን ካገሬ አፈር ብዙ የራቀ ሥፍራ ነዉ-የሚያርፈዉ---- እያልኩ አሰብኩ።ከናትሴዎች ጋር ግንባር የፈጠሩትን ጃፓኖችን ትወጋላችሁ ነዉ ያሉን።»

Karikatur Erster Weltkrieg Kolonialtruppen
ምስል Ullstein

ያኔ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ከነበረችዉ ከቡርኪና ፋሶ የተወሰዱት ባቢይ ሳይም ሥለ ጦርነቱ አላማ፤ሥለ ወዳጅ ጠላቶቻቸዉ ማንነት የሚያዉቁት አልነበረም።

«ሥለ ፋሽዝም ሲወራ እኛጋ ምን እንደሁ የሚያዉቅ የለም።አዉሮጶች ብቻ ነበሩ የሚያዉቁት። ጀርመኖችን መዉጋት እንዳለብን ይነግሩናል። ዝንጀሮ እንዳልሆናችሁ ማስመስከር አለባችሁ ይሉናል።እንደ ወታደር በመዋጋት ዝንጅሮ አለመሆናችንን እንድናረጋግጥ ይነግሩናል።ከዚሕ ዉጪ ሥለፖለቲካ የሚያስረዳን አልነበረም።»

ብሪታንያና ፈረንሳይ በጀርመን ላይ ጦርነት ካወጁበት ከመስከረም 1939 (እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር) ከየቅኝ ግዛታቸዉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አፍሪቃዊ ተዋጊ መልምለዋል።ከዚሕ ቁጥር የሚበልጥ አገልጋይና ረዳትም አዝምተዋል።

ከሰሜን አፍሪቃ እስከ አዉሮጳ፤ ከእስያ እስከ ፓስፊክ በተደረገዉ ዉጊያ ጀርመንን፤ ኢጣሊያንና ጃፓንን ተዋግተዋል።መልማይ አዝማች፤ አዋጊዎቻቸዉ አፍሪቃዉያኑ «ወዶ ዘማች» መሆናቸዉን ይናገራሉ።

አልበርት ኩኒዩኩ እንደሚሉት ግን እዉነቱ ተቃራኒዉ ነዉ።

« በግድ ነበር የሚመለምሉት።እኔ ለምሳሌ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ዉስጥ ነበር የምሥራዉ።መጡና ወሰዱኝ።ሌላ ቦታም በየመስሪያ ቤቱ እየዞሩ ወጣት ሠራተኞችን ወሰዱ።ሳላሳ ዓመት የሚበልጠዉ አልነበረም።»

አፍሪቃዉያኑ ወጣቶች በግዳጅ መዝመታቸዉ ብቻ ሳይሆን በየጦር አዉዱ ለመድፍ ማብረጃነት ወይም ለፈንጂ ጠራጊነት ተማግደዋል መባሉ እስካሁን ድረስ እያነጋገረ ነዉ።አፍሪቃዉያኑ ወደዉም ሆነ ተገደዉ፤ ቀድመዉም ሆነ ተከትለዉ ከቅኝ ገዢዎቹ ወታደር እኩል መዋጋታቸዉ ሥለ ነጩ ማንነት እንዲያዉቁ፤ ከነጩ እንደማያንሱ እንዲረዱ ጠቅሟቸዋል።

Zweiter Weltkrieg Afrikafeldzug Schlacht von El Alamein 1942
ምስል picture alliance/Heritage Images

ኋላ ደራሲና የፊልም አዘጋጅ የሆነዉ ሴኔጋላዊዉ የያኔ ዘመች እንዳለዉ «በጦርነቱ ወቅት ነጩን ራቁቱን አየነዉ» እንዳለዉ አይነት።ሥለ አፍሪቃዊያኑ ዘመቾች ለ10 ዓመት ያክል ያጠናዉ ጋዜጠኛ ካርል ረሠልም-ይሕንኑ ይመሰክራል።

«አፍሪቃዉያኑ፤ እንደ ልዩ ጌታ ያከብሯቸዉ የነበሩት (የቅኝ ገዢ ወታደሮች)ን በጭቃ፤ ቁሻሻዉ ሲርመጠመጡ፤ ሲሰቃዩና ሲሞቱ በማየታቸዉ በሰዎች መካካል ልዩነት እንደሌለ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።ብዙዎቹ በየሐገሮቻቸዉ የነበሩ የነፃነት ንቅናቄዎችን የረዱትም ይሕን ከተገነዘቡ በኋላ ነዉ።»

አፍሪቃዉያኑ በማያዉቁት ጦርነት ሞተዉ፤ ቆስለዉ፤ተጎሳቁለዉ አዉሮጳን ከፋሽታዊ አገዛዝ ነፃ አዉጥተዋል።ለከፈሉት ዋጋ የተከፈላቸዉ ግን ትንሽ ወይም ምንም ነዉ።የከፋዉ ደግሞ የአፍሪቃዉያን ገድል-መስዋዕትነት ጀርመናዉያንን ጨምሮ ብዙዎቹ አዉሮጳዉያን ከቁብ አለመቁጠራቸዉ ወይም አለማወቃቸዉ ነዉ።

ቴሬሳ ክሪኒንገር/ ሳሌሕ ምዋናሚሎንጎ

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ