ሁለተኛዉ ዙር የሶርያ የሰላም ድርድር | ዓለም | DW | 11.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሁለተኛዉ ዙር የሶርያ የሰላም ድርድር

ሁለተኛዉ ዙር የሶርያ መንግሥትና የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች ህብረት ድርድር ዛሬ በጄኔቭ ስዊትዘርላንድ ተጀመረ። ሁለቱ ተፋላሚ ሃይላት ባለፈው ወር መጨረሻ ያደረጉት የመጀመርያዉ ዙር ድርድር ያለምንም ዉጤት ነበር የተጠናቀቀው። በሳምንቱ መጨረሻ የተመድ ለሶርያውያኑ የሆምስ ከተማ አስፈላጊውን የሰብዓዊ ርዳታ ማድረስ አልቻለም።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የሶርያ ውዝግብ እጅግ የተወሳሰበ መሆኑን ቢገልጹም፤ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ አያገኝም ብሎ መናገር እንደማይቻል አስረድተዋል።
የሶርያ ሰላም ድርድር የሚካሄድባት ሰላማም የሰፈነባት የስዊትዘርላንዷ ጄኔቭና፤ የሶርያ ተቃዋሚ ኃይላት ዋና መቀመጫ የሆነችዉ እና የመንግስት ወታደሮች በቀጠሉት ዘመቻ ሲቪል ነዋሪዎችዋ በመኖር አለመኖር መካከል የሚገኙባት የሆምስ ከተማ፤ እጅግ የተለያየ ገፅታ አላቸው። እንድያም ሆኖ የሶርያ ተቃዋሚ ኃይላት ተወካዮችና የሶርያ መንግሥት ተስፋ በመሰነቅ ጄኔቭ ላይ የሚደራደሩባት ሁኔታ ሁለቱን ከተሞች አስተሳስሮአቸዋል። የሶርያዋ ሆምስ፤ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች፤ የፖለቲካ መፍትሄ ለማግኘት ፈቃደኛ መሆን አለመሆናቸው የሚፈትንባት ከተማ ትሆናለች። ይሁንና፣ በሳምንቱ መጨረሻ በከተማይቱ በተካሄደው ውጊያ ሳብያ የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ ማከፋፈል ያልቻለበት ድርጊት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ጉዳይ ላይ እንኳን መስማማት አለመቻላቸዉን አሳይቷል። ባለፈው የጥር ወር መጠናቀቅያ ላይ በሶርያ ተፋላሚ ኃይሎች ተወካዮች መካከል የተደረገዉ ድርድር ያለምንም ዉጤት አብቅቷል።

እንዲያም ሆኖ የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳይ የፖለቲካ ተንተኝ ሞሃመድ ማህሙድ ኦልድ ሞሃሜዱ እንደሚሉት ፤ በጄኔብ በሚገኘዉ የፀጥታ ፖለቲካ ተቋም፤ ሁለቱም ወገኖች በጠረጴዛ ዙርያ ለድርድር መቅረባቸዉ በራሱ እንደ አንድ ንዑስ ዉጤት ይቆጠራል፤ ይህን ባያደርጉ ኖር ምናልባትም በሃገሪቱ ያለዉ ሁኔታ የከፋ ሊሆን ይችል ነበር፤ « የሁለቱ ተፋላሚ ሃይላት ልዩነት እጅግ ሰፊ መሆኑ ሲታሰብ የጄኔቫዉ ድርድር መጀመሩ ንዑሱ አግባቢ ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል አቋሙን ለማጠናከር ወደ ጄኔቭ የመጣውን መንግስት ለማስወገድ እንደሚፈልግ የሚናገር የሚፈልግ ቡድን ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ጨርሶ መደራደር የማይፈልገው የሶርያ መንግስት ይገኛል። »
ይህ ፣ ይላሉ የመካከለኛ ምስራቅ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኙና በጄኔቭ በሚገኘዉ ዓለማቀፍ የጥናት ተቋም እንግዳ ፕሮፊስር ሞሃመዱ፤ በሶርያ የሰላም ድርድር፤ ፈጣን የሆነ አመርቂ መልስ ይገኛል የሚል አመለካከት አለመኖሩን ነዉ የሚያሳየዉ። የሶርያዉን የመጀመርያ ዙር የሰላም ድርድር የታዘቡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ የሶርያ ተፋላሚ ወገኖች በጎርጎረሳዊዉ 2012 ዓ,ምቱ የተደረገዉን ዉይይት

በመመርኮዝ ነዉ ለድርድሩ የቀረቡት። በዝያን ግዜዉ ድርድር ፤ በሶርያ የሚታየዉን ዉጥረት ማብቃትና የተኩስ አቁም ማድረግ፤ የሽግግር መንግስት መመስረት የሚሉ ነጥቦች ተነስተዋል። በጄኔቩ የሶርያ የሰላም ድርድር ላይ፤ የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች ህብረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሽግግር መንግስት ወደሚመሠረትበት ጉዳያ ላይ እንዲገባ ነው የሚሞክረው፤ የሶርያ መንግስት ተወካዮች ግን ድርድሩ በማጠቃላያ መግለጫ ላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ነጥብ በነጥብ፣ በመጀመሪያም፣ የኃይሉን ተግባር በሚመለከተው ነጥብ ላይ እንዲመክር ነው ሀሳብ ያቀረቡት።የአሳድ መንግስት ተወካዮች ልክ ባለፈዉ ጄኔቭ የሰላም ድርድር ላይ እንዳደረገው የመንግስቱን ተቃዋሚዎች ህብረት ተወካዮችን አሸባሪዎች አድርጎ ለማቅረብ እና ከዉጭ የሚመጡ ጀሃዲስቶች የደቀኑትን ስጋት ለማጉላት ነው የሚሞክረው። በዚህም የሽግግር መንግስት የሚለዉ ርዕስ የሚነሳበት ግዜዉ አሁን እንዳልሆነም ተናግሮዋል። የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳይ የፖለቲካ ተንተኝ ሞሃመድ ማህሙድ ኦልድ ሞሃሜዱም፤ መንግስት ይህን ርዕስ ፤ ማጓተት እንጂ ማንሳት እንደማይፈልግ ያምናሉ፤
«በድርድሩ ላይ መንግስት ይህንን ርዕስ ማጓተት ፣ማጓተት ነዉ የሚፈልገዉ። እንደ እኔ እምነት በድርድሩ ላይ እስከምን ድረስ መሄድ እንደሚችሉና የድርድሩን አካሄድ እስከምን ድረስ ሊቀይሩ እንደሚችሉ እየተመለከቱ ያሉ ይመስለኛል። በድርድሩ የተለያየ አርዕስት እያነሱ ፤ የሽግግር መንግስት የሚለዉ ርዕስ እንዳይነሳ እየሞከሩ ነዉ። ቢሆንም ግን በዚሁ ርዕስ ላይ ውሎ አድሮ ውይይት መደረጉ የማይቀር ነው»የሶርያዉ የሰላም ድርድር ባለፉት አስር ዓመታት ዉስጥ በዓለማችን ከተደረጉት ፖለቲካዊ ዉይይቶች፤ እጅግ አዳጋቹ እና የሰላም ዉይይቱ ከሳምንት ወደ ወራቶች ሁሉ ሊጓተት እንደሚችል ሞሃሜዱ ሳይገልፁ አላላፉም። በሳምንቱ መጨረሻ በሆምስ የተቋረጠዉ የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ ሂደት፤ በጄኔቭ ውይይት ለመጀመር የተደረሰው ትንሽ የሰላም ግኝት ምን ያህል ንዑስ መሆኑን አሳይቶአል ሲሉ የንስ ሌርከ በተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ቢሮ ቃል አቀባይ ይገልጻሉ ፤


«ወደ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሶርያዉያን ፤ ተፋላሚ ወገኖች በተፋላሚዎቹ ወገኖች በተከበቡ ሠፈሮች ይኖራሉ፤ ያ ማለት ደግሞ አስፈላጊዉ የሰብዓዊ ጉዳይ ቁሳቁስ ፈፅሞ አያገኙም። እኛም ወደነሱን መድረስ አንችልም፤ እነሱም ያንን ቦታ ለቀዉ መዉጣት አይችሉም»
እንደ ዓለማቀፉ ህግ ከሆነ የሶርያ መንግስት ለሶቪል ማህበረሰቦች የሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል። እንደ ተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ቢሮ ቃል አቀባይ ያንስ ላርከ ገለፃ፤ በሶርያ ለሚገኙ ወደ 9,3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶርያዉያን የሰብዓዊ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በሶርያ በሚታየዉ የርስ በርስ ጦርነት ሳብያ ድርጅቱ እስካሁን የርዳታ እጁን ለመዘርጋት የቻለዉ ለጥቂቶቹ ብቻ ሲሆን፣ በቀላሉ ሊደረስባቸው በማይችሉ አካባቢዎች ያሉ ሶርያውያን ቁጥር በግምት ሦስት ሚሊዮን እንደሆነ ገልፀዋል።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic