ሀይማኖት ነክ ሁከት በናይጀሪያ | ኢትዮጵያ | DW | 01.12.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ሀይማኖት ነክ ሁከት በናይጀሪያ

በናይጀሪያ ፌዴራዊ ክፍለ ሀገር በፕላቶ ርዕሰ ከተማ ጆስ በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደ ደም ያፋሰሰ ግጭት የብዙ ሰዎችን ህይወት ጠፋ፤ በርካቶችም በሁከቱ ሰበብ ቤት ንብረታቸውን ለቀው ሸሽተዋል።

ለተጎዱት የጆስ ነዋሪዎች የውኃ ርዳታ አቅርቦት

ለተጎዱት የጆስ ነዋሪዎች የውኃ ርዳታ አቅርቦት

የናይጀሪያ መንግስት በትናንቱ ዕለት ወዳካባቢው ጦር ከላከ ወዲህ ግን ሁከቱ ቆሞ ባካባቢው ውጥረት የሚታይበት መረጋጋት ሰፍኖዋል። የዶይቸ ቬለ የሀውሳ ክፍል ባልደረባ መሀመድ አዋል እንደዘገበው፡ ያካባቢው ህዝብ የዚህኑ አስከፊ ግጭት መንስዔ ማፈላለግ ይዞዋል።
ለሁከቱ መቀስቀስ ምክንያት የሆነው በክፍለ ሀገሩ ፕላቶ የተካሄደው ያካባቢ ምክር ቤታዊ ምርጫ ነበር። ባለፈው ዓርብ ከምርጫው ሂደት በኋላ የተቃውሞው የጠቅላላ ናይጀሪያ ህዝቦች ፓርቲ በምህጻሩ ANPP በገዢው የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በምህጻሩ በ PDP አንጻር ማሸነፉ ጭምጭምታ ከተሰማ በኋላ፡ በብዛት ወጣት ጋጠ ወጦች በጆስ የግድያና የጸሎት ቤቶችን በእሳት አጋይተዋል። በከተማይቱ ነዋሪዎች ዘገባ መሰረት፡ ብዙ መስጊዶችና አብያተ ክርስትያን ተደምስሰዋል። የቀይ መስቀል ማህበር እንዳስታወቀው፡ ከአስር ሺህ የሚበልጥ ህዝብ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ከተነሳው ውጊያ ለማምለጥ እያለ ቤት ንብረቱን ለቆ ሸስቶዋል፤ ከሶስት መቶ የሚበልጥም በግጭቱ ተገድሎዋል፤ በርካቶችም ቆስለዋል። ይሁንና፡ የፌዴራዊው ክፍለ ሀገር መንግስት በግጭቱ የተገደለው ሰው ሁለት መቶ ብቻ መሆኑን ነው በይፋ ያመለከተው። የፕላቶ ፌዴራዊ ክፍለ ሀገር ማስታወቂያ ሚንስትር ኑሁ ጋጋራ እርግጥ ሁከቱ በፖለቲካ ሰበብ ይነሳ እንጂ፡ ሀቀኛው ምክንያት ሀይማኖት ነክ መሆኑን ነው የሚገምቱት።
« ያካባቢው ምርጫ የግጭቱ መንስዔ ነው ብለን አናምንም፤ ምክንያቱም የምርጫው ይፋ ውጤት እስከቅዳሜ ድረስ አልወጣም ነበር። ውጤቱ ይፋ የሆነው ገና ትናንት ነበር። ግን ጆስ በጣም ሰበበኛ ከተማ ናት። በከተማይቱ ትንሹ ነገር ትልቅ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ይህ ዓይነቱ ሁከት በሚፈጠርበትም ጊዜ መጀመሪያ የሚጠቁት የጸሎት ቤቶች ናቸው። እና ለሁከቱ ሀይማኖታዊ ምክንያቶች ተጠያቂ ናቸው ብለን እናስባለን። »
ሁከቱን ቀስቅሰዋል በሚል የተጠረጠሩ ከአምስት መቶ የሚበልጡ ሰዎች፡ በብዛትም ወጣቶች አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላል። ከነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የወታደርና የፖለሊስ መለያ ለብሰው እንደነበር የማስታወቂያ ሚንስትር ጋጋራ አረጋግጠዋል።
« አዎ፡ እውነት ነው። ምክንያቱም አንዳንዶቹን ትናንት በፖሊስ ጽህፈት ቤት ውስጥ አይተናቸዋል። »
ጆስና ሌሎች የፕላቶ ክፍለ ሀገር ከተሞች ባለፉት ጊዚያት ደም አፋሳሽ ፖለቲካ፡ ሀይማኖትና ጎሳ
ነክ ውዝግቦች ተካሂዶባቸዋል። ይሁንና፡ በሳምንቱ መጨረሻ በጆስ የተካሄደው ግጭት ከአራት ዓመት በፊት በዚሁ አካባቢ ከታየው ግጭት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው አስከፊው ሁከት መሆኑን ያካባቢው ነዋሪዎች አመልክተዋል። እአአ በ 2004 ዓም በሙስሊሞችና በክርስትያኖች መካከል በተካሄደው ግጭት ወደ ሰባት መቶ የሚጠጋ ህዝብ ተገድሎ ከአንድ ሺህ የሚበልጥ መቁሰሉ ይታወሳል። ፕላቶ የሚገኘው በብዛት ሙስሊሞች በሚኖሩበት ሰሜናዊ ናይጀርያና በብዛት ክርስትያኖች በሚገኙበት ደቡብ ናይጀርያ መካከል ነው። እና በጥንታውያኑ ክርስትያኖችና በመጤዎቹ ሙስሊሞች መካከል የኖረው ስር የሰደደው ውእዝግብ በየጊዜው ለሚታየው የኃይል ተግባት ተጠያቂ መሆኑ ይነገራል። ሙስሊሞቹ ምንም እንኳን የሀገሪቱ ዜጎች ቢሆኑም ንዑሱ ፖለቲካዊ መብት እንዳላቸው ነው የሚሰማቸው። እና የጆስ ግጭት በአነጋጋሪው የናይጀሪያ የምርጫ ህግ/አዋርና በሀገሪቱ ህገ መንግስት ላይ ተሀድሶ እንዲደደር ከብዙ ጊዜ ወዲህ መታገል የጀመሩት ወገኖችን አቋም አጠናክሮላቸዋል።
ግጭቱ በሙስሊሞችና በክርስትያኖች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ለተጀመረው ውይይት ትልቅ ምት እንደሆነ የካቶሊካውያን ጳጳስና የሀይማኖቶች ኮሚሽን ሊቀ መንበር ኢግናሲዩስ ካይጋማ ገልጸዋል።
« እኔ ይህ በፍጹም ሊገባኝ አልቻለም። ምክንያቱም እኛ የናይጀሪያ ክርስትያን ማህበር እና የሙስሊሞቹ የጃማ አቱል ኢዝላም ማህበር አባላት ባለፈው ሳምንት ነበር ስለመቻቻል እና ስለ ሰላም ለመወያየት በትልቁ መስጊድ የተገናኘነው። »
ክርስትያኖቹና ሙስሊሞቹ በግጭቱ ሰበብ ተስፋ ሳይቆርጡ የሰላም ውይይታቸውን እንዲቀጥሉ ጳጳሱ ተማጽኖ ከማሰማታቸው ሌላ፡ የናይጀርያ መንግስት ለወጣቶች የተሻለ የወደደፊት ዕድል እንዲያዘጋጅ ሀሳብ አቅርበዋል።