ሀንጋሪ ወታደሮቿን ቻድ ለመላክ ተዘጋጅታለች
ቅዳሜ፣ መስከረም 4 2017የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ከቻዱ መሪ መሀማት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ጋር ቡዳፔስት ውስጥ ከተነጋገሩ በኋላ ቁጥራቸው ወደ 200 የሚደርስ ወታደሮቻቸውን ቻድ በማስፈር እቅዳቸው ገፍተውበታል። ኦርባን በፌስቡክ ከሳህል ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ፍልሰትን ለማስቆምበሚደረገው ዘመቻ ቻድ ወሳኝ ሚና ትጫወታለች ሲሉ ጽፈዋል። ኦርባን ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ፍልሰት ካለ ሳህል አካባቢ ሀገራት ሊቆም አይችልም ሲሉ ስለጉዳዩ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። እናም አሉ ኦርባን በመግለጫቸው ፣ሀንጋሪ ከቻድ ጋር አጋርነት የምትመሰርትበት ምክንያት ይሄ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይም ዛሬም ነገም ከፕሬዝዳንት ዴቢ ጋር እየሰራን ነው ብለዋል። ሱዳን ሊቢያ ኒዠር እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን የምታዋስነው ቻድ ቁጥሩ 19 ሚሊዮን እንደሚሆን የተገመተ ህዝብ አላት። ሀገሪቱም በሳህል አካባቢ ወሳኝ ይዞታ አላት። የምትገኝበት አካባቢ ስልታዊ ከመሆኑ ጋር የምዕራባውያን ቁልፍ አጋር መሆንዋ በዓለም ጂኦ ፖለቲካዊ የመሬት አቀማመጥ ጠቃሚነትዋን አጉልቶ ያሳያል።
ሀንጋሪ ከሳህል አካባቢ ምንድን ነው የምትፈልገው?
ጋናዊው የፖለቲካ ሳይንስና የፀጥታ ጉዳዮች ተንታኝ አማክዬ ኦዉሱ በቻድ ወታደሮቼን አሰፍራለሁ የሚሉት ኦርባን እንደ ቭላድሚር ፑቲን በአካባቢው የኤኮኖሚ ጥቅም ፈላጊ ናቸው ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ከዚህ ሌላ እንደ ፈረንሳይ ያሉ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በአካባቢው ሞገስ ባጡበትና በሳህልም ተሳትፎአቸው በቀዘቀዘበት በዚህ ወቅት ላይ ኦርባን ፖለቲካዊ ነጥቦችን ለማስመዝገብ እየሞከሩ ነውም ብለዋል። ሀንጋሪን ወደ ቻድ የሳቡ ምክንያቶችንም ተናግረዋል።
ትኩረት በአፍሪቃ፣ የአፍሪቃ የማስጠንቀቂያ ሥልት፤ አዲሱ የቻድ ፕሬዝደንት
«በመጀመሪያ ቡዳፔስትን ወደ ሳህል ወይም ወደ ቻድ ሊስቡዋት የሚችሉ ምክንያቶችን ማየት አለብን። በተለይ በሳህል የሚገኙ መጠነ ሰፊ ሀብቶች፦ ነድጅ ዘይት፣ ዩራንየም ፣ወርቅ፣ እና ወደፊት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ሌሎችም በጣም ብዙ ሀብቶች። እንደ ማንኛውም የአውሮጳ ሀገር ሀንጋሪ ይበልጥ ተጽእኖ ፈጣሪ እየሆነች ነው። ከአፍሪቃ ሀብቶችም ፍትሀዊ ድርሻ ማግኘት ትፈልጋለች።ወርቅ ፣ኮባልት ሊትየም እና ሌሎች ቡዳፔስትን ሊጎትቱዋት የሚችሉ ዋነኛዎቹ ሳቢ ምክንያቶች ናቸው፤እነዚህ ደግሞ ችላ ሊባሉ አይገባም።»
ሀንጋሪ ወታደሮቿን ቻድ የማስፈሯ ፋይዳ
ከክፍለ ዓለሙ ውጭ በሚገኙ ታዛቢዎች እምነት ኦርባን 200 ወታደሮችን በመላክ በምዕራብ አፍሪቃ እያደገ የመጣውን የሩስያ ተጽእኖ እየኮረጁ ነው። አንዳንዶቹ የወታደሮቹ መስፈር በሳህል አካባቢ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ከባድ ተጽእኖ ሊያሳርፍ ይችላል ይላሉ ።ሆኖም ኦዉሱ ይህን ይጠራጠራሉ።
«ቻድ ራስዋ ከሀንጋሪም ሆነ ከብዙ የምዕራብ አውሮጳ ሀገራት በጣም ትልቅ ናት። ስለዚህ 200 ወታደሮች ምንም ዓይነት ተጽእኖ ላያደርጉ ይችላሉ። በውጭ ፖሊሲ ደግሞ ተምሳሌታዊ ገጽታ አለው። ይኽውም አንድ መንግሥት ከድንበሩ ባሻገር ለፀጥታ አንድ ነገር እያደረገ መሆኑን ማሳየት የሚፈልግበት። »
ሲግናል ሪስክ በተባለው የደቡብ አፍሪቃ የጥናት ተቋም የጸጥታ ጉዳዮች ተንታኝ ርያን ከሚንግስ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የሳህል ሀገራት መንግሥታዊ ያልሆኑ ታጣቂዎችን ለመመከት የተጠቀሙባቸው ስልቶች ከወታደራዊ እይታ አንጻር በአካባቢው የደኅንነት ተግዳሮቶችን በተገቢው መንገድ መወጣት አልቻሉም።
«እስካሁን ድረስ የሳህል ሀገራት የአውሮጳ ወይም ምዕራባውያን ኃይላትን አለያም የሩስያን ኃይሎች የተጠቀሙበት ስልት የችግሩ ምልክቶች ላይ እንጂ የሰርጎገብነት መንስኤዎች ላይ ያተኮሩ አይደሉም።ወይም እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች የሚያገኟቸውን ድጋፎች አሁንም ለምን እንደሚያገኙ አይደለም።»
የሦስት የሳህል አገራት አዲስ ኅብረት እጣ ፈንታ
የሀንጋሪ የተጋነነ የአፍሪቃ እቅድ
ባለፈው ዓመት ሀንጋሪ በቻድ የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል እና የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ በመክፈት የግብርናና የትምሕርት ስምምነቶችን በመፈራረም ሀገራቸውከቻድ ጋር በፍጥነት ግንኙነቷን አሳድጋለች። ሀንጋሪ በአፍሪቃ ያላት ቦታ በታሪክም ደካማ ነው። ሆኖም ኦርባን ከቻይና ከሩስያና ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር የቅርብ ግንኙነት ለመፍጠር ወደ ምሥራቅና ደቡብ ሀገራት ጋር የሚያስጠጋት የውጭ ፖሊሲ እያራመዱ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምዕራብ አፍሪቃ ወታደራዊ መሪዎች ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ሁሉም ማለት ይቻላል ወደ ሩስያ እና ቫግነር ወደሚባለው ቅጥር ተዋጊ ቡድን ፊታቸውን አዙረዋል። ሀንጋሪ የሚገኙ ምሁራንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለክሬምሊን ቅርብ የሆነችው ቡዳፔስት በሳህል በሩስያ ስም ልትንቀሳቀስ ትችላለች የሚል ስጋታቸውን እያሰሙ ነው።ሆኖም የሀንጋሪ መንግሥት ስለ ተልዕኮው ሲጠየቅ በሳህል ሩስያን ወይም ወይም ሌላ የውጭ ሀገራትን ጥቅም አልወክልም ሲል አስተባብሏል።
በሳህል ሃገራት የጽንፈኞች ጥቃትና የሩስያ ፍላጎት
ሀንጋሪ በቻድ ወታደሮቿን አሰፍራለሁ ማለቷን የአውሮጳ ኅብረት ተቀብሎታል
የአውሮጳ ኅብረት ከሀንጋሪ ጋር ባይስማማም ሀገሪቱ በቻድ የምታካሂደውን ተነሳሽነት ተቀብሏል። በሀገር ውስጥና በአካባቢው ተግዳሮቶች ቢኖሩም ዓለም አቀፍ አጋሮች ከቻድ ጋር መስራታቸው በጣም አስፈላጊ ነው ብሏል ኅብረቱ። በሀገር ውስጥ ግን በተለይ ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ ወታደሮች የቻድ ተልዕኮን «አደገኛና አባካኝ» ሲሉ ይተቹታል።
የፈረንሳዩ ጋዜጣ ለሞንድና የሀንጋሪው የምርመራ ዘገባ አቅራቢ፣ዲሬክት 36 ምርመራ የኦርባን ብቸኛ ልጅ ጋስፓር ኦርባን ከቻድ ጋር በተካሄደ ይፋዊ ድርድር ላይ በጥንቃቄ መሳተፉን ዘግበዋል። የሀንጋሪ መንግሥት ግን ትችቱን ወደ ጎን በማለት ልጃቸው በቋንቋ ችሎታውና በሀንጋሪ ጦር ሠራዊት ውስጥ በሻለቃነት እንደማገልገሉ እንደ ባለሞያ ነው የተሳተፈው ሲል ትችቱን አጣጥሏል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የኦርባን ልጅ በሀንጋሪ ወታደሮች የቻድ ተልዕኮን ዝግጅት ለማገዝ በአገናኝ መኮንንነት ይሰራል።
አውሱ እንደሚሉት የሀንጋሪ ኃይሎች ወደ ቻድ መምጣት በሳህል የወታደሮቹን ስብጥር ያበዛል።ሆኖም ሀንጋሪ የቻድ ሀብቶች ፍላጎት ካላት ያኔ ምናልባት እነዚህን ጥቅሞችዋን ለማስጠበቅ ምናልባትም ተጨማሪ ኃይሎችን ማዝመት ሊኖርባት ይችላል።
ክርስፒን ምዋኪዱ / ኅሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ