ሀማኖታዊ ግጭት በግብፅ | አፍሪቃ | DW | 10.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሀማኖታዊ ግጭት በግብፅ

በግብፅ ጥቂት ወጣቶች በካይሮ በሚገኘው እና በግብጽ ብቻ ሳይሆን በመላ ሙሥሊም ሀገራት ከፍተኛ አመለካከት ባተረፈው ዝነኛው የአዝሀር ዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ላይ ሰሞኑን የመሥቀል ምልክት የሣሉበት ድርጊት በሙሥሊሞች እና በኮፕት ኦርቶዶክሶች መካከል አስከፊ ግጭት አስከትሎዋል።

ባለፈው የሣምንት መጨረሻ ላይ ከካይሮ በስተሰሜን በሚገኘው የካሊዩብያ ግዛት ባለፈው የሣምንት መጨረሻ በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተፈጠረው ሁከት የአራት ክርስትያኖች እና የአንድ ሙሥሊም ሕይወት መጥፋት ነው።
በሀይማኖት ሰበብ በተነሳ የኃይል ተግባር ሕይወታቸው ላለፈች አራት የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ባለፈው እሁድ በካይሮ የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል የሀዘን ሥነ ሥርዓት ይካሄድበት በነበረበት ጊዜ  ፅንፈኛ ሙሥሊሞች ሳይሆኑ አልቀሩም የተባሉ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ሥነ ሥርዓቱን በማወክ፡ በሐዘንተኛው ላይ ድንጋይና ሞሎቶቭ ኮክቴል ወርውረዋል። በዚሁ ድርጊት የተናደዱ ክርስትያኖች በበኩላቸው በገዢው የሙሥሊም ወንድማማቾች ማህበር እና በፕሬዚደንት መሀመድ ሙርሲ አንፃር መፈክሮች ባሰሙ ጊዜ ግጭቱ እንደተባባሰ እና የተኩስ ድምፅም እንደተሰማ ያይን ምስክሮች ገልጸዋል። በዚሁ ግጭት አንድ ሰው ተገድሎዋል።


እርግጥ፡ ሁኔታዎች አሁን ጥቂት ተረጋግተዋል። ሆኖም፡ የሰሞኑ ግጭት በሙሥሊሞች እና በኮፕት ኦርቶዶክሶች፡ ማለትም ቢያንስ በሁለቱ ቡድኖች አክራሪዎች መካከል ውጥረቱ ምን ያህል መካረሩን በግልጽ አሳይቶዋል። የሁለቱ እምነት ተከታዮች ሁሌም በሀይማኖት ሰበብ እንደሚወዛገቡ በካይሮ የሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጋማል ሶልታን ቢያስረዱም፡ በወቅቱ ሁኔታዎች ሌላ መልክ በመያዝ በግብፅ እሥላማዊ መንግሥት እንዲመሠረት በሚፈልጉትና በሚቃወሙት መካከል በወቅቱ ሥር የሰደደ ልዩነት መፈጠሩን ገልጸዋል።
« የኮፕት ኦርቶዶክስ ማህበረሰብ በዚህ ውዝግብ ውስጥ በጣም ገብቶውበታል። ምክንያቱም የመንግሥቱን እና የሀገሪቱን የማንነት ጥያቄ፡ እንዲሁም፡ የሀይማኖት እና የፖለቲካ ሚናን የሚመለከት ነው። ቀደም ባለ ጊዜ ውዝግቡ ሀይማኖታዊ ምክንያቶች ብቻ ነበሩት። አሁን ግን ምክንያቱ የብሔራዊ ማንነት እና የሥልጣን ጥያቄ ነው። ይህ ደግሞ ውዝግቡ ከበፊቱ የተጠናከረ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እንዲይዝ አድርጓል። »
በእሥላማዊ መንግሥት ውስጥ ኅልውናቸው ስጋት ላይ ሊወድቅ ይችላል ብለው የሰጉት ክርስትያኖች ከመንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች ጋ መተባበር የጀመሩበት ርምጃቸው በወቅቱ ከሙሥሊም ወንድማማቾች ማህበር ደጋፊዎች ጋ እንዲጋጩ ሳይገፋፋቸው አልቀረም ነው የሚባለው። የግብፅ የማንነትን ጥያቄ ወይም የምትከተለውን የመንግሥት ሥርዓትን በተመለከተ የቀጠለውን ክርክር አስመልክተው የግብፅ ኮፕት ኦርቶዶክሶች መሪ ፓትርያርክ ቴዎድሮስ ዳግማዊ  በሰጡት አስታያየት በግብፅ የእሥላማዊ መንግሥት ምሥረታ በፍፁም ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸዋል።


ፕሬዚደንት ሙርሲ በካይሮ የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን ላይ ባለፈው የሣምንት መጨረሻ የተሰነዘረውን ጥቃት አውግዘዋል፤ በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስትያን ላይ የተጣለው ጥቃት በራሳቸው ላይ እንደተጣለ ጥቃት መመልከታቸውን አስታውቋል። ይሁንና፡ ሀያስያን ፕሬዚደንት ሙርሲ በሚከተሉት እና እነርሱ ሀይማኖትን ማዕከል ያደረገ ባሉት አመራራቸው በአሁኑ ጊዜ በክርስትያኖች እና በሙሥሊሞች መካከል የሚታየውን ውጥረት ይበልጡን አካረዋል በሚል ይነቅፏቸዋል። በሙሥሊሞችና በኮፕት ኦርቶዶክሶች መካከል የቀጠለው ውዝግብ ግብፃውያን ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞውን ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክን ከሥልጣን ሲያነሱ ያስቀመጡትን ዓላማቸውን ትርጉም አልባ ማድረጉንም ይናገራሉ።  ጋዜጠኛው እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አሽራፍ ካሊል እንዳስረዳውም፡ የፕሬዚደንት ሙርሲ መንግሥትን የሚቃወሙት ኮፕት ኦርቶዶክሶች እና ሙሥሊሞች ብቻ ሳይሆኑ፡ ለሀይማኖት ያልወገኑም ይገኙባቸዋል።
« ስያሜ ሲሰጥ ደረጃው በግልጽ መታወቅ አለበት። ለሀይማኖት ያልወገነ ተቃውሞ ቡድን የሚለው አጠራር ለኔ አይሰራም። ምክንያቱም፡ በየዕለቱ ሀይማኖታዊ ግዴታዎቻቸውን የሚያሟሉ፡ ሙርሲን እና ሙሥሊም ወንድማማችነት ማህበርን በፍፁም የማያምኑ ሙሥሊሞች አሉ። ስለዚህ ሁሉንም ባንድነት ለዘብተኛ ፡ ለሀይማኖት ያልወገኑ ብሎ መጥራቱ ሁኔታዎችን ማቃለል ይሆናል። ይህ በመሆኑም እኔ እሥላማዊ እና ፀረ እሥላማዊ ብየ መጥራቱን እመርጣለሁ። እምነቱን ከልብ የሚቀበል ሙሥሊም ልትሆን ትችላለህ። ለሀይማኖት ያልወገንክ ነህ ማለት ግን አይደለም። ባጭሩ እሥልምናን መርሁ ያደረገ መንግሥት እንዲመሠረት አትፈልግም ማለት ነው። »
በተለያዩት የግብፅ ፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ግልጽ መስመር በወቅቱ የለም። ይህንንም ሁኔታ የሁለቱም ትልቆቹ ሀይማኖች አክራሪዎች ይህን ሁኔታ ለራሳቸው ጥቅም ሲያውሉት ይታያል፤ ምክንያቱም፡ ከተወሳሰበ የፖለቲካ ትንታኔ ይልቅ ሀይማኖታዊው አክራሪነት ብዙ ሕዝብ ሊቀሰቅስላቸው እንደሚችል ተረድተውታል።

ኬርስተን ክኒፕ
አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሰ 

Audios and videos on the topic