1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምን ያሕል ሕዝብ፤ ለስንት ጊዜ ማለቅ አለበት?

ሰኞ፣ ሐምሌ 16 2010

የብዙ ወጣቶች ለጋ ሕይወት፤አካል እና ደም የተገበረለት ሕዝባዊ ጥያቄ ለድል መብቃቱ የአዋሳኝ ድንበሩን ደም አፋሽ ግጭት ለማስቆም የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ቁጭቱ።እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ ጭናቅሰን፤ ሚኤይሶ፤ሞያሌ እና ሌሎችም ከተሞች ዛሬም እንደ ዛሬ ስድስት ወሩ ሕይወት፤ ሐብት ንብረት ይጠፋል።

https://p.dw.com/p/31xcE
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

የዓብዲ መሐመድ ዑመር መዘዝ

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለ ማርም ደሳለኝ በዘመነ ሥልጣናቸዉ ማብቂያ የኢትዮ-ሶማሊያ እና የኦሮሚያ ግጭት እንዲወገድ እንደመከሩ፤ እንዳሳሰቡ፤ እንዳስጠነቀቁ፤ ተሰናበቱ።ግጭት ግድያ፤ስደቱ ቀጠለ።ኃይለ ማርያምን የተኩት ዶክተር ዓብይ አሕመድ እስረኞች ሲፈቱ፤ ለምክር ቤት  ማብራሪያ ሲሰጡ፤ሥለሠላም እና መደመር ሲያወሩ የኢትዮ-ሶማሊያ እና የኦሮሚያ ድንበር አስከሬን ይለቀም፤ተፈናቃይ ይቆጠርበት ነበር።በዶክተር አብይ መርሕ እና የተማረከዉ የአዲስ አበባ ሕዝብ በመሪዉና በኤርትራዊዉ ፕሬዝደንት እንግዳዉ ፊት በሰላም ተስፋ እና ሥለሰላም ሲዘፍን ሲጨፍር ለደቡብ፤ለምዕራብ እና ለምሥራቅ ኢትዮጵያ ፌስታዉ ሐዘን ቅይጥ ነበር።ጂግጂጋ፤ሚኤይሶ፤ ሞያሌ ዛሬም ደም አድርቀዉ ደም ያፈሳሉ።እስከ መቼ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ዓሕመድ የሠላም አንድነት መርሕ የአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ማትረፉ እርግጥ ነዉ።በሒሳብ ስሌት የተሰየመዉ መርሕ-ጥረታቸዉ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማስፈን በመስማማታቸዉ ዉጤት አዲስ አበባ ላይ በተረጋገጠ ማግሥት ግን ሰላም-አንድነት ያለመዉ መርሕ ምስራቅ ኢትዮጵያ ላይ በክፍፍል-ግጭት መርከሱን አልሸሸጉም።

ዛሬ ሳምንቱ።ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሁዩማን ራትስ ዋች በተለይ የኢትዮጵያ ሶማሌ መስተዳድር ባለሥልጣናት በሕዝባቸዉ ላይ ሥለሚፈፅሙት ግፍ በሰፊዉ ይዘግባል።ሶማሌዎችም ይናገራሉ።ያንዱን እናሰማችሁ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሚመሩትን መንግሥት ከሕዝብ የማገናኘት ኃላፊነት ያለባቸዉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ግን የሚፈልጉትን በሚፈልጉበት ጊዜ ለሚያዙት ጋዜጠኛ ከመናገር ሌላ የሚወክሉትን መንግስት መርሕ፤ የመሪያቸዉን መልዕክትም ሆነ የሕዝባቸዉን ጥያቄ ለመገናኛ ዘዴዎች ለመግለፅ አንድም አይፈልጉም፤ ሁለትም አይችሉም፤ ወይም አያዉቁትም።

Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

ባለፉት ሰወስት ወራት በብዙ ጉዳዮች ላይ መልስ እና ማብራሪያ ፍለጋ በተደጋጋሚ ደዉለናል።አንዱ የሶማሌ መስተዳድር  ወይም ጠቅላይ ሚንስትሩ «ሰዉ ይረግፍበታል» ያሉት የሶማሌ መስተዳድርና የኦሮሚያ ድንበር ግጭትን የሚመለከት ነበር።እንደዉላለን አይመልሱም።ከመለሱም የንግግራቸዉ መጀመሪያ እና መጨረሻ «እንትናትን ጠይቅ ነዉ።»ሰወስት ወራቸዉ።ዛሬም ደገሙት።

የኢትዮጵያ የፌደራል እና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚንስቴር ባለሥልጣናት ሥልክ ሥለሚመለከታቸዉ ጉዳይ መረጃ ለመስጠት የሚያገለግል አይመስልም።የኢትዮጵ ሶማሊያ መስተዳድር ቃል አቀባዮች  «ጠላት» የሚሉትን ፌስ ቡክ ላይ ለማጥላላት በርግጥ አልሰነፉም። ለመገናኛ  ዘዴዎች የሚያቀብሉት ቃል ሥለሌለ ግን የሥልክ ጥሪ አይመልሱም።

ጂግጂጋ ግን ዛሬ፤ ያዩ እንዳሉት ሕዝብ ባደባባይ ተሰልፎ ሲጮሕባት፤ በልዩ ፖሊስ ዱላ እና ጥይት ሲደበደብባት፤ ደም ሲያዝባት ሞት ሲያንዣብባት ነዉ የዋለችሁ።ስማቸዉን ደብቀዉ፤ ድምፃቻዉን ቀይረዉ ለመናገር የደፈሩት የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት የርዕሠ መስተዳድር አብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳደርን የሚቃወሙ 38 ሰዎች ታስረዋል።ለተቃዉሞ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ ልዩ ፖሊስ የተባለዉ ታጣቂ ኃይል በከፈተዉ ተኩስ ቢያንስ ሁለት ሰዉ ተገድሏል።

Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

አስተያየታቸዉን በድምፅ ለመስጠት የፈሩ የጂግጂጋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ደግሞ ልዩ ፖሊስ በከፈተዉ ተኩስ የቆሰሉት ሰዎች ከሐምሳ ይበልጣሉ።አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸዉ።ከቁስለኞቹ 12 ወንዶች እና ሰባት ሴቶች ክፉኛ ተጎድተዋል።

በደም አፋሳሽ ግጭት ያሳረገዉ የጂግጂጋ የተቃዉሞ ሠልፍ የተደረገዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ ድንበሮችን የሚያብጠዉ ጎሳን የተላበሰ ግጭት እና ግድያ እልባት ሳያገኝ ነዉ።

ከሶማሌ መስተዳድር ተመርጠዉ  የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ጀማል ድርዬ ኸሊፍ እንደሚሉት የድንበሩም ሆነ የራሱ የሶማሌ መስተዳድር ግጭት ጠንሳሽ እና አራማጅ የኢትዮጵያ ሶማሊያ መስተዳድር መሪ ናቸዉ።መስተዳድሩ፤ በአቶ ጀማል እምነት  የአንድ ግለሠብ «ርሥት» የሆነ መስሏል።

 በዘመዶቻቸዉ ላይ ይፈፀማል ያሉትን ግፍ ለማየት በቅርቡ ከዩናያትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ ጋራድ ዑመር ዱል ግን ርዕሠ-መስተዳድር አብዲ ዑመር መሐመድ ብቻቸዉን አይደሉም ይላሉ።

 ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድር ድንበሮች ላይ የሚደረገዉን ግጭት የሚጋጋሙ ኃይላትን «ከሩቅ ሆነዉ ቤንዚን የሚያቀብሉ» ብለዋቸዋል።የቀድሞዉ የምክር ቤት እንደራሴ ጀማል ድርዬ ኸሊፋ እንደሚሉት ግን  የርዕሠ መስተዳድር አብዲ መሐመድ ዑመር ረዳት፤ደጋፊ እና አዛዥ እዚያዉ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሰፈረዉ የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች ናቸዉ።በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድር ወሰን ላይ አምና ነሐሴ በይፋ የተነሳዉ ግጭት አቶ ጀማል እንደሚያምኑት ያኔ በኦሮሚያ መስተዳድር ተቀጣጥሎ የበረዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ አቅጣጫ ለማሳት ያለመ ነበር።

 ዓላማዉ በርግጥ ዉል ስቷል።ሕዝባዊዉ አመፅ ለድል በቅቷል።ይሁንና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የዋሕ ኢትዮጵያዉያን ሕይወታቸዉን ገብረዋል።በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተባርሯል።የታሰረ፤የተገረፈዉን እስካሁን የቆጠረዉ የለም።የጠፋ እና የተዘረፈዉ ሐብት ንብረት ልክም በትክክል አልተሰላም።

የብዙ ወጣቶች ለጋ ሕይወት፤አካል እና ደም የተገበረለት ሕዝባዊ ጥያቄ ለድል መብቃቱ የአዋሳኝ ድንበሩን ደም አፋሽ ግጭት ለማስቆም የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ቁጭቱ።እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ ጭናቅሰን፤ ሚኤይሶ፤ሞያሌ እና ሌሎችም ከተሞች ዛሬም እንደ ዛሬ ስድስት ወሩ ሕይወት፤ ሐብት ንብረት ይጠፋል።እንደገና አቶ ጀማል።

  ከዩናይትድ ስቴትስ የተመለሱት የኢትዮጵያ ሶማሌ መስተዳድር ተወላጅ ገራድ ዑመር ዱል እንደሚሉት እሳቸዉ እና ብጤዎቻቸዉ ለድንበር አካባቢዉ ግጭት እና እዚያዉ ሶማሌ መስተዳድር ዉስጥ ለሚፈፀመዉ ግፍ ተጠያቂ በሚባሉት ኃይላት ላይ የፈደራሉ መንግሥት እርምጃ እንዲወሰድ በተደጋጋሚ «አቤት» ብለዋል።እስካሁን ያገኙት መልስ ግን የለም።

የቀድሞዉ የምክር ቤት እንደራሴ ጀማል ድርዬ ኸሊፍ እንደሚጠረጥሩት ግን አዲሱ የፌዳራል መንግስት ልክ እንደ ቀዳሚዎቹ ሁሉ ግጭቱንም ሆነ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉን ግፍ እንደ ሁለተኛ ጉዳይ ሳይመለከተዉ አልቀረም።

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

  የፌደራሉን መንግስት ይወክላሉ የሚባሉት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እና የፌደራል እና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚንስቴር መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት ማብራሪያ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ሥልክ ብንደዉልም ቀደም ሲል እንዳልነዉ ሥልካቸዉን ለየተመደቡበት ኃላፊነት ለመጠቀም አልፈቀዱም።

በሶማሌ እና በኦሮሞ ተወላጅ ላይ የሚፈፀም ግፍ፤ ግድያ፤ መፈናቀል እና መሰደድም እንቀጠለ ነዉ።ግን ምን ያሕል ሕዝብ፤ ለምን ያሕል ጊዜ መገደል፤ መሰቃየት አለበት? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ