1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ200 በላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከየመን ተመለሱ

ሐሙስ፣ ኅዳር 20 2011

ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ የመን ገብተዋል የተባሉ ከ200 በላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸዉ መመለሳቸዉን ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM አስታወቀ።ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸዉ የተመለሱት ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ጋር በመተባበር መሆኑ ተመልክቷል።

https://p.dw.com/p/395CY
Migration Jemen Äthiopien
ምስል IOM

«ወደ 600 የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ከየመnን ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ የመን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን መመለስ መጀመሩን አስታዉቆ ነበር። ድርጅቱ ከየመን በቃል አቀባዩ  በሚስተር ሳባ አልሙላሚ በኩል እንደገለፀዉ ፤ኢትዮጵያዉያኑን ስደተኞች በአዉሮፕላን ከሰንዓ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ነበር ያመሩት።በዚህም መሰረት ከ200 በላይ ኢትዮጵያዉያን አዲስ አበባ መግባታቸዉን የIOMኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ሰይፈ ስላሴ ለDW ገልፀዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም ድርጅቱ ተመላሽ ስደተኞቹን ከአዲስ አበባ ወደየ ትዉልድ ቀያቸዉ እንደሚያጓጓዝ ገልፀዋል። ከተመላሽ ስደተኞቹ መካከል ህፃናትና ሴቶች የሚገኙ ሲሆን  ከመካከላቸው የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉና የጤና ዕክል የገጠማቸዉ እንዳሉ አቶ አለማየሁ ገልፀዋል።ከህፃናቱ መካከልም ከቤተሰብ ጋር ተለያይተዉ የሚገኙ በመኖራቸዉ  ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር እስኪገናኙ ድረስ  በድርጅቱ ማቆያ ጣቢያ እንደሚሰነብቱ አስረድተዋል። 

Migration Jemen Äthiopien
ምስል IOM

አብዛኞቹ  ስደተኞች ወደ ሳዉዲ አረቢያ ለመሻገር በህገ ወጥ መንገድ በሱማሌ ላንድ ቦሳሶ እንዲሁም በጅቡቲ በኩል ወደ የመን የገቡ ሲሆን  በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ዝርፊያ በድብደባና መንገላታት የደረሰባቸዉ ናቸዉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬዉ ዕለት ባወጣዉ መግለጫም ከዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር ባደረገዉ ትብብር በጦርነትና በረሀብ በምትታመሰዉ የመንበ ህይወታቸዉ ለአደጋ የተጋለጠ በህግ ከለላ ስር የነበሩ  ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጭምር  ባለፉት ሁለት ቀናት በሰላም ወደ ሀገራቸዉ ገብተዋል።

Migration Jemen Äthiopien
ምስል IOM

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ጋር በመሆንም «ዜጎቻችን በሰላም ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ እንሰራለን »ሲልም በመግለጫዉ አመልክቷል።ለዚህም አስፈላጊዉን ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM እንዳስታወቀው ከትናንት ወዲያ የጀመረዉ ስደተኞቹን በፈቃዳቸዉ የመመለስ ዘመቻ እስከ ጎርጎሮሳዉያኑ ታህሳስ 30/2018  ድረስ ይቀጥላል። በዚህ ዘመቻ ወደ 600 የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ከየመን ወደ ሀገራቸዉ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፀሐይ ጫኔ 

ሂሩት መለሰ