1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትንባሆ እና የልብ ሕመም

ሐሙስ፣ ግንቦት 23 2010

በዓለም አቀፍ ደረጃ የትንባሆ አጫሾች ቁጥር የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል። ሆኖም ግን አሁንም ትንባሆ በሚያስከትለው የልብ ሕመም እና ተላላፊ ያልሆኑ በሚባሉ በሽታዎች ምክንያት የሚሞተው ሰው ቁጥር ዛሬም ያን ያህል አለመቀነሱን ድርጅቱ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/2yjRZ
Zigarettenstummel
ምስል Colourbox/A. Armyagov

የአጫሾች ቁጥር የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፤

ትንባሆን በማንኛውም መልኩ መጠቀም እና በተዘዋዋሪ ለጭሱ መጋለጥ ለልብ ሕመም የሚዳርግ ዋና ምክንያት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ WHO ዛሬ ለሚታሰበው ትንባሆ ያለማጨስ ዕለት ባለጣው መግለጫ አመልክቷል።  የልብ ድካም እንዲሁም የደም ዝውውር መታወክ ወይም ስትሮክ በመላው ዓለም በዓመት 3 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ እንደሚፈጅም ዘርዝሯል። ድርጅቱ ዘንድሮ ይህ ዕለት ሲታሰብ ትንባሆ ከልብ ህመም ጋር ያለው ግንኙነት ትኩረት እንዲያገኝ አፅንኦት ሰጥቷል። ትንባሆ በጥቅሉ በየዓመቱ ከ7 ሚሊየን ለሚበልጥ ሕዝብ ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑ ቢገለፅም አሁንም በተለይ ቻይና እና ሕንድ ውስጥ አብዛኞቹ አጫሾች ይህን እንደማያውቁ የWHO የማይጋቡ በሽታዎችን ይዞታ የሚመለከተው ዘርፍ ዳይሬክተር ዳግላስ ቤትቸር አመልክተዋል።

«የWHO የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ዓለም አቀፍ የትንባሆ አጠቃቀም ቅኝት በግልፅ እንዳሳየው ማጨስ የደም ዝውውር መታወክን እንደሚያስከትል የማያምኑ አዋቂዎች ብዛት ለምሳሌ ውስጥ 73 በመቶ ይደርሳል። 61 በመቶዎቹ ደግሞ ማጨስ የልብ ድካም አደጋን እንደሚያባብስ አያውቁም።»

በትንባሆ አጠቃቀም ረገደም በርካታ አጫሾች የሚገኙት በሁለቱ የእስያ ሃገራት ውስጥ መሆኑ ነው የተገለጸው። ቻይና 307 ሚሊየን እንዲሁም ሕንድ ውስድ ደግሞ 106 ሚሊየን ሕዝብ ያጨሳል። ሌላዋ በርካታ ትንባሆ አጫሽ ያለባት ሃገር ኢንዶኔዢያ ናት፤ 74 ሚሊየን። የዓለም የጤና ድርጅት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2025ዓ,ም የትንባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር በ30 በመቶ እንዲቀነስ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የተለያዩ ሃገራት ይህን እውን ለማድረግ በጀመሩት እንቅስቃሴ የአጫሾች ቁጥር በተለይም የሴት አጫሾች ማለት ነው በመጠኑ እየቀነ መሄዱን ድርጅቱ ጠቁሟል። ያም ሆኖ ግን ካሰበው ግብ ለመድረስ በዩናይትድ ስቴትስ የወንድ አጫሾች በከፊል የምዕራብ አውሮጳ ሃገራት ደግሞ የሴት አጫሾች ቁጥር የተጠበቀውን ያህል አልቀነሰም። ትንባሆ በየዓመቱ ከሚቀጥፈው ሰዉ ቁጥር መካከል 890 ሺህ የሚሆነው በተዘዋዋሪ ለጭሱ ተጋላጭ የሆነው ወገን ነው። ዳግላስ ቤትቸርም ትንባሆ የሚያስከትለው የጤና እክል እየታወቀ ሃገራት የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረጉት ጥረት እምብዛም እንዳልሆነ ነው የገለጹት።

Welt- Nichtrauchertag am 31. Mai
ምስል dpa

«ትንባሆ መጠቀምም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጭሱ መጋለጥ በዓለም ከልብ ሕመም ጋር በተገናኘ ለሚከተለው ሞት ለ17 በመቶ ዋና ምክንያት ነው። ትንባሆን በመጠቀም በዓመት 3 ሚሊየን ሕዝብ በልብ በሽታ ይሞታል። እንዲያም ሆኖ ግን ዘገባዎች እንደሚያስረዱት፤ በፈቃደኝነት የትንባሆ አጠቃቀምን ለመቀነስ የታቀደውን ግብ ለመምታት የሚሞክር ከስምንት ሃገራት አንዱ ብቻ ነው። »  

እንደየዓለም የጤና ድርጅት መግለጫ በአሁኑ ሰዓት በመላው ዓለም 1,1 ቢሊየን አጫሾች ይገኛሉ። 367 ሚሊየን ደግሞ ጭስ አልባ በሆነ መልኩ ትንባሆን ይጠቀማሉ። ይህ የአዋቂዎቹ ቁጥር ሲሆን በልጆች ደረጃ ደግሞ ከ13 እስከ 15 ዕድሜ ክልል የሚገኙ 24 ሚሊየን አጫሾች መኖራቸው ተመዝግቧል። የትንባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ጥረቱ ከተጀመረ ወዲህ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም 27 በመቶ የነበረው በ2016 ወደ 20 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተመልክቷል።

China Raucher Rauchen Gesundheit Weltnichtrauchertag
ምስል picture-alliance/epa/R. de la Pena

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ3 ሚሊየን በላይ አጫሽ መኖሩን በቅርብ የተደረገ ጥናት አመልክቷል። ካንሰር እና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትኩረት እንዲያገኙ የበኩል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው በኢትዮጵያ የማትያስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ በቀለ በሀገሪቱ የወጣት አጫሾች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ እንደሚያሳስብ ይናገራሉ።

«የስልጣኔ ምልክት ተደርጎ ነው የሚታየው  በወጣቶቹ  ላይ አሁንም ትምህርት ቤት ሄደን ስናስገነዝባቸው ይሄን ያህል የጤና ጠንቅ መሆኑን አይገነዘቡትም። እነሱ የሚያዩት ለጊዜው በቃ የማደግ ምልክት የመሻሻል የስልጣኔ ምልክት አድርገው ነው የሚወስዱት። አንዱ ከገቡበት በኋላ ለማቆም በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። አሁን ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ አንድ ሚሊየን ፈረንሳዮች ናቸው ሲጋራ ማጨስ ያቆሙት እና ባደጉ ሃገራት ውስጥ ትንባሆ ማጨስ የዘመናዊነት ምልክት መሆኑ ቀርቶ ትምባሆ ማጨስ እየቀነሰ በእኛ ሀገር ላይ እየተስፋፋ ነው ያለው።»

ከአቶ ወንዱ ለመረዳት እንደቻልነው ሰዎች በሚሰበሰቡበት ስፍራ እንዳይጨስ የተደነገገውን በማክበር በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አራት ሆቴሎች ማለትም ሰሜን ሆቴል፣ ተገን ሆቴል፣ ማግኖሊያ ሆቴል እና አራራት ሆቴል እውቅና አግኝተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ