1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ መንግሥትን እርምጃ ኮነኑ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 13 2014

የመንግሥት እርምጃዎች ኢትዮጵያ ልትሸከመው ወደማትችል አለመረጋጋት እንደሚያስገቧት ፓርቲዎች አስጠነቀቁ። የአብን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ እናት ፓርቲና መኢአድ መንግሥት "አፈና" እየፈጸመ ነው ሲሉ ከሰዋል። የመንግሥት ኮምዩንኬንሽ አገልግሎት እንደሚለው ግን የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች "ህግ የማስከበር" ዓላማ ያላቸው ናቸው

https://p.dw.com/p/4Bg6Z
Logo Äthiopien Opposition Partei AEUP

ፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ መንግሥትን እርምጃ ኮነኑ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን መውሰድ የጀመራቸው እርምጃዎች አገሪቱ ልትሸከመው ወደማትችለው አለመረጋጋት እና ብጥብጥ ሊያስገባት ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ። የአብን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት አባላት፣ እናት ፓርቲ እና መኢአድ የኢትዮጵያ መንግሥት አፈና እየፈጸመ ነው የሚል ክስ አቅርበዋል።  የመንግሥት ኮምዩንኬንሽ አገልግሎት እንደሚለው ግን የፌደራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች "ህግ የማስከበር" ዓላማ ያላቸው ናቸው። 

በአማራ ክልል እየተወሰደ ነው ያለው "መጠነ ሰፊ እርምጃ" የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ትላንት አርብ ባወጣው መግለጫ "በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ዝውውር፤ በቡድን ተደራጅቶ ግለሰቦች ያፈሩትን ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ላይ የተሰማሩ፤ በነፍስ ግድያ የሚጠረጠሩ" ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አስታውቋል። እርምጃው በመንግሥት ማብራሪያ መሠረት "አንዱን ህዝብ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክልሉ እንዳይረጋጋ በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ" ጭምር ያነጣጠረ ነው።  

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው አምስት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባላት ትላንት አርብ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያን መንግሥት በአማራ ክልል "እገታ እና ስወራ" ይፈጽማል ሲሉ ከሰዋል። የምክር ቤት አባላቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ የአብን አመራሮች እና አባላት፣ የፋኖ ታጣቂ አባላት፣ ሕጋዊ ያሏቸው ታጣቂዎች፣ ወጣቶች፣ የጦር መኮንኖች እና የጸጥታ አመራሮች ተፈጽሟል ያሉት "መንግስታዊ እገታ እና ስወራ በአስቸኳይ እንዲቆም" ጠይቀዋል። 

እናት ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ግን መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች አገሪቱን ለከፋ አለመረጋጋት ሊዳርግ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው አስጠንቅቀዋል። 
"ከሰሞኑ አፈናዎች እና እገታዎች እዚህም እዚያም" መታየታቸውን የሚናገሩት የእናት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) "ሰዎች በሚያዙበት ጊዜ የአገራችን ሕግ በሚደነግገው መሠረት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊወጣ ይገባል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ደሳለኝ "ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ በመንግሥት ኃይሎች እየታፈኑ ነው" በማለት ከእናት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚስማማ አስተያየት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይፈጽመዋል የሚሉት አፈና "ወንጀለኛው ማነው ንጹህስ ማነው የሚለውን ነገር ያልለየ" እንደሆነ የገለጹት አቶ ስንታየሁ "መንግሥትን ይተቻል፤ መንግሥትን ሊጠላ ይችላል" የተባሉ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ገልጸዋል። "ይኸ አይነት አካሔድ ሕግ ማስከበር ሊባል አይችልም" ሲሉ የነቀፉት የመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ "ሕዝብ በዚህ ልክ በጅምላ ማፈን ወደ ሌላ ብጥብጥ፤ ወደ ሌላ ችግር ውስጥ እንደሚከት ለማንም የተሰወረ ነገር አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል። 

የእናት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰይፈ ስላሴ አያሌው (ዶ/ር) የመንግሥት እርምጃ "በማኅበረሰብ መካከል አለመረጋጋት ሊያስከትል" እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ፕሬዝደንቱ እንደሚሉት "ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ይኸንን አለመረጋጋት ልትሸከም የምትችልበት ላይ አይደለም።"

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ግን "በህገወጥ ተግባር ላይ በመሳተፍ፤ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሆነ ብለው፤ አቅደዉ በሚሰሩ አካላትና ግለሰቦች" ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ትላንት አርብ የወጣው መግለጫ "የሚዲያ እና የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል" ብሏል።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ