1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በግብፅ

ሰኞ፣ ግንቦት 20 2004

በግብፅ ለበርካታ ዓመታት በአምባገነንነት የቆዩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሞባረክ በአደባባይ ተቃውሞ ከስልጣን ከተወገዱ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከናውኗል። ይህ ምርጫ ግብፃውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይበጀኛል የሚሉትን ፕሬዚዳንት በነፃነት ለመምረጥ ድምፅ የሰጡበት እንደሆነም ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/153K2
ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪዎች በግብፅ
ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪዎች በግብፅምስል picture-alliance/dpa

በግብፅ ለበርካታ ዓመታት በአምባገነንነት የቆዩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሞባረክ በአደባባይ ተቃውሞ ከስልጣን ከተወገዱ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከናውኗል። ይህ ምርጫ ግብፃውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይበጀኛል የሚሉትን ፕሬዚዳንት በነፃነት ለመምረጥ ድምፅ የሰጡበት እንደሆነም ተዘግቧል።

«ሕዝቡ ስርዓቱን ማስወገድ ይፈልጋል!» ግብፃውያን እንዲያ እያሉ ጉሮሮዋቸው እስኪነቃ በታህሪር አደባባይ ከጮኹ ዓመት ከመንፈቅ ተቆጥሯል። ይህ ጩኸት ግን በመፈክር ተጀምሮ በመፈክር ብቻ አልተቋጨም። በገፍ አካል አስገብሮ፣ ጥቂት የማይባሉ ልሳናትን እስከወዲያኛው ከርችሞም ቢሆን እነሆኝ ለውጥ ማለቱ ግን አልቀረም።

በርግጥም ለሶስት አስርት ዓመት አምባ ገነን ሆነው ግብፅን የመሩትን ሃያል መሪ አምበርክኳል፤ የግብፁ አብዮት። ፕሬዚዳንቱ ሆስኒ ሞባረክን የቀድሞው አሰኝቶ፣ ጋማል እና አላ የተባሉ ወንዶች ልጆቻቸውንም አስከትሎ ከቤተመንግስት ወደ ወህኒ ሸኝቷል ይኸው ሕዝባዊ አብዮት። ታዲያ የግብፃውያኑ የያኔው የቀን ተቀን ጩኸት «አምባገነን አገዛዝ አንገሸገሸን፣ ነጻ ምርጫ ተከናውኖ የፈቀድነውን በድምፃችን ለስልጣን እናብቃበት» የሚል ነበር።

በግብፅ ሴት መራጮች ተራ ሲጠብቁ
በግብፅ ሴት መራጮች ተራ ሲጠብቁምስል AP

ለአብዮተኞቹ የመጀመሪያ ድል። ልክ የዛሬ ስድስት ወር፣ ዕለቱም እንዲሁ ሰኞ ነበር፤ ግብፃውያን በታሪካቸው ከሙባረክ መለስ መሆኑ ነው፤ የመጀመሪያ የሆነውን የምክር ቤት ምርጫ ለማከናወን ተሳካላቸው። በበርካቶች የያኔው ምርጫ ያሳለፍነው ሳምንት ለተከናወነው ሌላኛው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደመንደርደሪያ ቢቆጠርም ሰዉ ግን ተመልሶ ከአደባባይ መታየቱ አልቀረም።

ምንም እንኳን የታሰበው የምክር ቤት ምርጫ እውን ቢሆንም፤ በተለይ የግብፅ ወጣቱ ክፍል ከሞባረክ ወዲህ ሀገሪቱን የተቆጣጠረውን ወታደራዊ ሸንጎ ክፉኛ መንቀፉን አላቋረጠም። የምክር ቤቱንም ምርጫ «ጉልቻ ቢቀያየር» ሲል በመተቸት አብዮታችን ግቡን እስኪመታ በሚል ዳግም ከአደባባይ መከሰቱን ቀጠለ። በዘመነ ሞባረክ ከፍተኛውን የስልጣን እርከን ተቆናጠው የቆዩት አምር ሙሳ ከጊዜው ጋር ተራምደው በወቅቱ ክስተቱን የዲሞክራሲ ሂደት ሲሉ አሞካሹት።

«ይህ ዲሞክራሲ ግብፅ ውስጥ በንድፈ ሀሳብ ሳይሆን በተግባር የሚታይበት የአዲስ ዘመን ብስራት ነው። እንግዲህ ከምርጫው በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የመረጥካቸው ተወካዮች ይኖሩሃል ማለት ነው። ሆኖም ወደ ታህሪር አደባባይ ወጥተህ አመለካከትህን በሌላ አንፃር ማንፀባረቅ ከፈለግክም ትችላለህ። ነፃ ሐገር ነው መሆን ያለበት፤ ግን በስርአት የታነፀ።»

ሞባረክ እንዲያ ቀኑ ሳይጨልምባቸው፣ ያ ሁሉ ግብፃዊ በደቦ ሳያመርባቸው በፊት አምር ሙሳ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነቱንም የአረብ ሊጋው ዋና ፀሀፊነቱንም ደርበው ሰርተዋል። ባሳለፍነው ረቡዕ እና ሐሙስ በተካሄደው ምርጫ ደግሞ ከሌሎች 12 ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ጋር ተቀይጠው ተወዳድረዋል፤ ምንም እንኳን የተጠበቀባቸውን ያህል የመራጭ ድምፅ ባያገኙም ማለት ነው። አንዳንድ ተንታኞች እንደሚገልፁት እንደ አምር ሙሳ ያሉ የቀድሞው ባለስልጣናት ልምድ ያካበቱ ቢሆንም፤ የግብፃውያንን ልብ ለማሸነፍ ግን ተራራ የመውጣት ያህል ሳይከብዳቸው አልቀረም። ለወጣቷ ግብፃዊት ኢንጊ ማድቡሊ ደግሞ የከፋው ነገር ከቀድሞው መንግስት ባለስልጣናት መካከል አንዱ ፕሬዚዳንት ሆኖ ብቅ ያለ ጊዜ ነው።

ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ ሞሐመድ ሙርሲ
ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ ሞሐመድ ሙርሲምስል AP

«በጣም ነበር የሚደንቀኝ። ህዝቡን የጨቆነ የአሮጌው መንግስት ርዝራዥ ሰው አሁን ግብፃውያንን ለማጥፋት እና የፖሊስ አገዛዝን ዳግም ለማስፈን ፕሬዚዳንት ሆኖ ቢመረጥ ያ ለኔ ከምንም በላይ የከፋው ነገር ነው የሚሆነው። »

ግብፃዊቷ ኢንጊ ማድቡሊ እንደበርካታ ወጣት ግብፃውያን አብዮተኞች ሁሉ በምርጫው ባትሳተፍም ምኞቷ ግን የሰመረላት አይመስልም። በእርግጥም የቀድሞው መንግስት ርዝራዥ የምትላቸው አምር ሙሳ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በሙባረክ አገዛዝ በጠቅላይ ሚንስትርነት ማዕረግ ባልደረባቸው ለነበሩት ሌላኛው ዕጩ አህመድ ሻፊቅ ግን መንገዱ ሙሉ በሙሉ የተደላደለ ነው ባይባልም፤ አባጣ ጎርባጣነቱ ከወዲሁ ሳይወገድ አልቀረም። እንደ ኢንጊ ላሉ ወጣት ግብፃውያን አብዮተኞች ነገሩ ባይዋጥላቸውም ሻፊ ግን ከፍተኛ ድምፅ ካገኙት ተርታ ተመድበዋል። ወጣቷ ኢንጊ በምርጫው ያልተሳተፈችበትን ምክንያት እንዲህ ትገልፃለች።

«በወታደራዊ አስተዳደር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ላይ በምንም አይነት ሁኔታ አልሳተፍም። ዓመት ከመንፈቅም አልፎ ቢሆን ስልጣን ላይ ያሉት እኮ እነሱ ናቸው። ከመጀመሪያው አንስቶ በአብዮቱ ውስጥ የነበረ ማንኛውም ሰው አሁን ለመምረጥ ይቸገራል። »

ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ አህመድ ሻፊቅ
ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ አህመድ ሻፊቅምስል picture-alliance/dpa

50 ሚሊዮን መራጮች በተመዘገቡበት የግብፁ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከግማሽ በላዩ መራጭ ድምጽ መስጠቱን የግብፅ የምርጫ ኮሚሽን ገልጿል። ለዘብተኛው የግብፅ ጋዜጣ አል ዋፍድ ሂደቱን «ግብፃውያን ትንፋሻቸውን ገታ ያደረጉበት» በሚለው ርዕሱ በስፋት አትቷል። አንዳንድ ግብፃውያን በሐገሪቱ ገና አዲስ ሐገ-መንግስት ሳይፀድቅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መካሄዱ በራሱ ስልጣኑ ከወታደራዊ ሸንጎው እንዳይወጣ ያደርጋል ሲሉ ይተቻሉ። ራሜዝ ኤል ማስሪ፥

«አዲሱ ፕሬዚዳንት ዞሮ ዞሮ ምንም ያህል ስልጣን አይኖረውም። በዚህም አለ በዚያ ስልጣኑን የሚቆጣጠረው የወታደራዊ ሸንጎው ነው። ያ ችግር ይፈጥራል»

የግራ ብሔርተኞች ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ሐምዲን ሳባሂ በበኩላቸው የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ እና አቤት እንደሚሉ ከወዲሁ አስጠንቅቀዋል። የግራ ብሔርተኛ ፖለቲከኛው ቅሬታቸውን ያሰሙት አንዳንድ ችግሮች በምርጫ ጣቢያዎች ተከስተዋል በሚል ነው። «አብዮቱ ይመለከታችኋል» በሚል መርህ መፈክር የሚንቀሳቀስ አንድ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ውስጥ የሚሰሩት ራሜዝ ኤል ማስሪም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

«የተለያዩ ዕጩዎችን በሚደግፉ ሰዎች መካከል አል ጋሪያ ውስጥ ግጭት ተከስቷል። ባሽቲል ውስጥ በዳኛ ውሳኔ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘግተዋል። በብዙ ቦታዎች መራጮች ስማቸው በስርዓቱ መዝገብ ላይ አልሰፈረም።»

በመጀመሪያው ዙር የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የግራ ብሔርተኛው ሐምዲን ሳባሂ 22 ከመቶ የመራጭ ድምፅ በማግኘት በሶስተኛ ደረጃ ማጠናቀቃቸው ተጠቅሷል። በዚሁ የግብፅ ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ውድድር የሙስሊም ወንድማማቾቹ ዕጩ ሙርሲ 25,3 ከመቶ በማግኘት አንደኛ መውጣታቸው ተዘግቧል። የሙባረክ ዘመን ወታደር እና ፖለቲከኛው ሻፊቅ ደግሞ 24 ከመቶ ድምፅ በመሰብሰብ ሁለተኛ እንደሆኑ መንግስታዊው የግብፅ የዜና አገልግሎት አርብ ዕለት ዘግቧል።

በግብፅ የምርጫ ወረቀት ሲቆጠር
በግብፅ የምርጫ ወረቀት ሲቆጠርምስል dapd

«አል አህራም» የተሰኘው ሌላ ጋዜጣ ደግሞ ሻፊቅን «ወታደራዊ ፋሽስት» ሲላቸው ሙርሲን ደግሞ «እስላማዊ ፋሽስት» ሲል በጋዜጣው ተችቷል። በርካታ ወጣት ግብፃውያን አብዮተኞች በበኩላቸው ያለሙለት እውነተኛ ዲሞክራሲ በግብፅ እውን አለመሆኑ ቅሬታ ሳያሳድርባቸው አልቀረም። ወጣቷ ኢንጊ ማድቡሊም ያንኑ ነው የምትገልፀው።

«አብዮቱ ገና ይፋፋማል፤ አብዛኞቻችንም ልጆቻቸውን በመስዋዕትነት የገበሩትን መቼም አንዘነጋቸውም። ሁሉም ዳቦ በልቶ እስኪያድር፣ ነፃነት እና ማኅበራዊ ፍትህ እስኪሰፍን ድረስ ትግላችን ይቀጥላል።»

በግብፁ የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከተሳተፉት 13 ዕጩዎች መካከል ጎልቶ የወጣ አሸናፊ ባለመኖሩ ሁለተኛ ዙር ምርጫ በቅርቡ ይካሄዳል። ፉክክሩም በሙስሊም ወንድማማቾቹ ዕጩ ሞሐመድ ሙርሲ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አህመድ ሻፊቅ መካከል እንደሚሆን እየተነገረ ነው። ይኸው ምርጫ የሚከናወነው ሰኔ ዘጠኝ እና አስር መሆኑ ታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ ይኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ