1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፈረንሳይ፣ለፔን ወይስ ማክሮ?

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2009

ማክሮ ለፔንን በ60 በመቶ ድምጽ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተተንብዮአል። ማክሮ ያሸንፋሉ የሚለው ግምት ሊሰነዘር የቻለው ማክሮ የለፔን ፓርቲ ከሚያገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ባይደግፉዋቸውም ከለፔን የተሻሉ ናቸው ብለው ድምጻቸውን ለማክሮ የሚሰጡ ፈረንሳውያንን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

https://p.dw.com/p/2cFRj
Bildkombo Wahlkampfplakate Frankreich

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪዎችና መርሃቸው

ከአሥር ቀናት በፊት በተካሄደው የፈረንሳይ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንታዊዙር ምርጫ  አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ለሁለተኛው ዙር ምርጫ ያለፉት የመሀል አቋም ያላቸው ኢማኑዌል ማክሮ እና ቀኝ አክራሪዋ ማሪ ለፔን በመጪው እሁድ ለሚካሄደው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ከባድ ፉክክር ላይ ናቸው። በተሰናባቹ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ የሥልጣን ዘመን በኤኮኖሚ ሚኒስትርነት ያገለገሉት «ኦን ማርሽ» የተባለው ፓርቲ መሪ ማክሮ ነፃ ገበያን እና የአውሮጳ ህብረት ሲደግፉ ተፎካካሪያቸው የብሔረተኛው የፍሮ ናስዮናል ፓርቲ መሪ ለፔን ደግሞ ፈረንሳይ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ፣ድንበርዋን እንድትዘጋ እና ከዩሮ ተጠቃሚዎች ማህበር እንድትወጣ የሚፈልጉ ፖለቲከኛ ናቸው ። ከዚህ ሌላ ሁለቱ ተፎካካሪዎች በአሁኑ ጊዜ በአውሮጳ ዐብይ መነጋገሪያ በሆነው በስደተኞች ጉዳይ ላይም የሚከተሉት መርህ እጅግ የተለያየ ነው ።

«ማሪን ለፔን ሙሉ በሙሉ ስደትን እና ምንም ዓይነት ቀለም ሆነ ዘር ይኑራቸው ስደተኞችን የሚቃወሙ ፖለቲከኛ ናቸው። የፈረንሳይ ድንበሮች በሙሉ እንዲዘጉ ነው የሚፈልጉት የሚያካሂዱት ዘመቻም የውጭ ዜጎች ጥላቻን መሠረት ያደረገ ነው። በፈረንሳይ ለሚደርሱ የሽብር ጥቃቶችም በሙሉ ተጠያቂ የሚያደርጉት ሙስሊም ስደተኞችስደተኛ ን ነው ። እርሳቸው ስደተኞች የፈረንሳይን ማንነት አበላሽተዋል ነው የሚሉት። እናም ከየትኛውም የአለም ክፍል ስደተኛ እንዲገባ አይፈልጉም። » የዶቼቬለ የእንግሊዘኛው ክፍል የፓሪስ ዘጋቢ ባራባራ ቬስል  ናት ማሪ ለፔን በስደት እና ስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚያራምዱትን  አቋም የገለፀችልን ። የለፔን ተፎካካሪ የማክሮ አቋም ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው ። የፓሪስዋ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ማክሮ የሚከተሉት መርህ አቋም የተለሳለሰ ነው ትላለች ። የሁለቱ ተፎካካሪዎች የውጭ መርህም እንዲሁ የተራራቀ ነው  ።

Francois Hollande und Emmanuel Macron
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Brinon

«አንድ ነገር እርግጠኛ ነው ። ማሪ ለፔን ኔቶን ለቀው መውጣት ይፈልጋሉ ከሩስያም ጋር መቀራረብ ይፈልጋሉ ። ኢማኑኤል ማክሮ ደግሞ እስካሁን ፈረንሳይ ስታደርግ እንደቆየችው ይቀጥላሉ ። በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ይበልጥ ተዋህደው መቀጠል ነው የሚፈልጉት። »እንደባርባራ ቬስል ሁሉ ሃይማኖትም የሁለቱ እጩ ፕሬዝዳንቶች የውጭ መርህ ፍፁም የሚገናኝ አለመሆኑን ነው የምትናገረው ።እጅግ የተራራቀ አቋም ካላቸው ከሁለቱ እጩ ተወዳዳሪዎች ማን ቀጣዩ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሊሆን እንደሚችል አጓጊነቱ ጨምሯል ። ለጊዜው ግን ማክሮ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 23.75በመቶ ድምጽ በማግኘት ለሁለተኛው ዙር ምርጫ በአንደኝነት ማለፋቸው የአውሮጳ ህብረት እና የህብረቱን መጠናከር የሚፈልጉ ወገኖችን አስደስቷል ።

«ምርጫውን በአንደኝነት ያሸነፉት ዕጩ የአውሮፓ ህብረትን የሚደግፉ በመሆናቸው ተደስቻለሁ።ማክሮ ግልጽ የሆነ የአውሮፓ ህብረት አጀንዳ ነው ያላቸው። ይህ ደግሞ እጅግ ጠቃሚ ምልክት ነው።»

Frankreich Wahl - Presse
ምስል DW/T. Rooks

ከአንደኛው ዙር የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ውጤት በኋላ በአውሮፓ ፓርላማ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ቡድን ሊቀመንበር ስካ ኬለር የሰጡት አስተያየት ነበር ። የመጀመሪያው ዙር የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ፍጹም ያልተጠበቀ ነበር። ውጤቱ የፈረንሳይ የምርጫ ታሪክ ቀይሯል ። በተለይ ለሁለተኛው ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከቀኝ መሀሎቹ ከሪፐብሊካኖች ወይንም ከግራዎቹ ሶሻሊስቶች አንዳቸውም አያልፉም የሚል ግምት አልነበረም። የመሀሉ ማክሮም ሆነ ቀኝ አክራሪዋ ለፔን ለመጨረሻው ውድድር ይደርሳሉ ተብሎም አልተጠበቀም።  በመጪው እሁድ በሚካሄደው ሁለተኛው ዙር ምርጫ ማክሮ ያሸንፋሉ ተብሎ በሰፊው ተገምቷል ። ዛሬ በወጣው ግምት ማክሮ ለፔንን በ60 በመቶ ድምጽ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተተንብዮአል። ማክሮ ያሸንፋሉ የሚለው ግምት ሊሰነዘር የቻለው የፓሪስዋ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ እንደምትለው ማክሮ የለፔን ፓርቲ ከሚያገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ባይደግፉዋቸውም ከለፔን የተሻሉ ናቸው ብለው ድምጻቸውን ለማክሮ የሚሰጡ ፈረንሳውያንን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ሃይማኖት እንዳለቸው ከመካከላቸው ፈረንሳይ የተወለዱ የውጭ ዝርያ ያላቸው ዜጎች እና ሙስሊሞች ይገኙበታል ።

Präsidentschaftswahl in Frankreich Emmanuel Macron
ምስል picture alliance/AA/M. Yalcin

በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም እጩ ተወዳዳሪዎች አይወክሉንም የሚሉ በርካታ ፈረንሳውያንም ድምፃቸውን ላይሰጡ ይችላሉ የሚል ግምት አለ ።የ39 ዓመቱ የኤማኑኤል ማክሮ ፓርቲ «ኦን ማርሽ» ገና አንድ ዓመት ያልሞላው ፓርቲ ነው። የማክሮ የፖለቲካ ልምዳቸውም ብዙ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው። በዚህ የተነሳም ማክሮ ሥልጣን ቢይዙ ሀገሪቱን የመምራት ብቃታቸውን የሚጠራጠሩ አልጠፉም። የማሪን ለፔን ፓርቲ ፍሮ ናስዮናልም ከጎርጎሮሳዊው 2002 ዓምቱ ምርጫ ወዲህ ዘንድሮ ነው ለሁለተኛ ጊዜ ለመጨረሻ ዙር ውድድር የቀረበው። የዚህ ፓርቲም የአመራር ብቃት እንዲሁ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም ።ይሁን እና ሁለቱም ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም ከሚያራምዱ ልምድ ካላቸው ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተጣምረው የመስራት እቅድ እንዳላቸው ነው የሚነገረው ። ከዚህ ሌላ ማክሮን በአንደኝነት ማሸነፋቸው ቢያስደስትም በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ፀረ የአውሮጳ ህብረት አቋም ያላቸው ማሪ ለፔን የ7.6ሚሊዮን የፈረንሳይ መራጮችን ማለትም የ21.4 በመቶውን ድምፅ አግኝተው ሁለተኛ ደረጃን መያዛቸው እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ማሻሻያ ካላደረገ ፈረንሳይ ከህብረቱ ትውጣ የሚሉት ግራ አክራሪው ተፎካካሪ ዦን ሉከ ሜሎንሾን 19.6 በመቶ ድምጽ ማሸነፋቸው ስጋት ማሳደሩ አልቀረም። በዚህ ስሌት ምንም እንኳን ማክሮን ተሳክቶላቸው ቢያሸንፉ ለፔን ደግሞ ወደ 40 በመቶ ድምጽ ሊያሸንፉ የመቻላቸው ግምት ማሳሰቡ አልቀረም ። ስጋቱም ማክሮ ጥቂት የማይባል መፍቅሬ አውሮጳ አቋማቸውን የሚቃወም ህዝብ ያለባትን ሀገር መምራት ከባድ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል የሚል ነው። ከዚህ ሌላ ማክሮን በሰኔ በሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ አብዛኛውን መቀመጫ ማግኘታቸው አጠራጣሪ እንደሆነም እየተነገረ ነው ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ