1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጦርነት በሰሜን፤ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት

ዓርብ፣ ጥቅምት 27 2013

በዚህ ሳምንት ፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መንግሥት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ  ጋር ጦርነት  መጀመሩን ይፋ አድርጓል። በሁለቱ አካላት መካከል ለወራት የዘለቀው ንትርክ በውይይት እንዲፈታ ብዙዎች ሲያስቡ ቢቆይም የተፈራው ጦርነት መቀስቀሱ የተደባለቀ ስሜትን መፍጠሩን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚነበቡ አስተያየቶች ያመላክታሉ።

https://p.dw.com/p/3kyW3
Symbolbild Social Media
ምስል DW/S. Leidel

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት *ጥቅምት 27 2013)

በዚህ ሳምንት መባቻ ፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መንግሥት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ  ጋር ጦርነት  መጀመሩን ይፋ አድርጓል። በሁለቱ አካላት መካከል ለወራት የዘለቀው ንትርክ በውይይት እንዲፈታ ብዙዎች ሲያስቡ ቢቆይም የተፈራው ጦርነት መቀስቀሱ የተደባለቀ ስሜትን መፍጠሩን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚነበቡ አስተያየቶች ያመላክታሉ። የተወሰኑትን አሰባስበናል፤ ፍፁም ጥላሁን በትዊተር፤ «ወንድምና ወንድም ሲጣሉ የሚያባብስ እሱ ቤተሰብ አይደለም። ድምጻችሁን አሰሙ፤  እምቢ ለጦርነት በይ ኢትዮጵያ! ለጎሳ ግጭት እምቢ በይ!» ሲሉ፤ «ይህ ጦርነት የመዛመት ዕድል ያለው መሆኑን ለመገንዘብ ጠንቋይ መሆን አያሻውም። ኢትዮጵያ አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች።» ብለዋል አንዷለም ቦልተና በዚሁ በትዊተር። መቲ ሰራፊናም እንዲሁ፤ «ጦርነት መቅረት ያለበት ሌላኛው ምክንያት፤ ሽማግሌ ወንዶች ጦርነትን ያውጃሉ ወጣቶች በህይወታቸው ዋጋ ይከፍላሉ፤ ለትግራይ ጸልዩ፤ ጦርነትን እምቢ በይ ኢትዮጵያ።» ነው ያሉት በትዊተር። ሌላው በትዊተር አስተያየት የሰጡት ህብር ኢትዮጵያ የተባሉት ደግሞ ሃሳብ ደግሞ እንዲህ ይላል፣ «ይህ ውጊያ የእርስ በርስ ጦርነት አይደለም። ህዝቦች አልተጋጩም። ቲፒኤልኤፍ የሚባል የሚሊየነሮች ስብስብ የቡድን ፍላጎቱን ለማርካት ጭሮ ያስነሳው እሳት ነው። ከትግራይ ህዝብ ጀርባ ላይ ነቅሎ ይሄዳል። መቶ ሺህዎችን ያሰደደው በተራው ይሰደዳል።» ትዝታ ደግሞ፤ «ጦርነት ወደህ የምትገባበት ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አይደለም። ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የምንጋጋጥበት ሰዓትም አይደለም። ከሁሉም በፊት ሀገራዊ አንድነት ግድ ይላል። ከዚያ ሌላው ያለው አማራጭ የጠላቶቻችን መጫወቻ መሆን ነው። ኢትዮጵያ ትቅደም።» ይላሉ።

ዮሐንስ ደግሞ የትዊተር ፤ «መጀመሪያ ቤትህን አጽዳ! መጀመሪያ አራዊቶችህን ቅጣ! መጀመሪያ ሰው በላ አሸባሪህን ተቆጣ! ብዙ መጀመሪያዎችን አልፈህ ወደ ጦርነት የሄድከው ሌላ አይደለም፤ «ሊበሏት ያሰቧትን ጅግራ,,,,,» እንጂ ኢትዮጵያ የምትናጠው በኦነግ ነው! ሌላው ወሬ ነው!» አዲሱ ዘመድ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ጠ/ሚሩ ህወሓትን እደመስሳለሁ ካሉ መጀመሪያ ህወሓት አጽድቆ የሰጣቸውና በሁለት እጃቸው ተሸክመው ይመራኛል ያሉትን ዘረኛ ከፋፋይ የሆነውን አውሬውን ሕገ-መንግሥት ይደምስሱት በፊርማቸው ያግዱት!!! በዚህ አውሬ ሕገ-መንግሥት ብዙ ንጹሐን ተገድለዋል ታርደዋል ተፈናቅለዋል አሁንም ድረስ እየሆነ ነው!!!» ሲሉ ሳሙኤል ነጋም የእሳቸውን ሃሳብ የሚጋሩ ይመስላል፤ «አንቀጽ 39ና የጎሳ ፖለቲካን አስወግዱ፤ ይህ ነው መፍትሄው።» ብለዋል።
ከሁለቱም አቅጣጫ ለጦርነቱ ግፋ የሚሉ ወገኖችን ያስተያየት በማስተዋል፤ «የሶሻል ሚዲያ አርበኞች እሳት ማላኮሱን ትተውት?»  ያሉት ደግሞ ሚሲ ናቸው፤ «የትም የኢትዮጵያ ክፍል ኑር ጦርነት ከጀመረ አንተም አትተርፍም፤ የትም የዓለም ክፍል ኑር ኢትዮጵያ ያሉ ወገኖችህ አይተርፉም። ማላኮሱን ትተን ለሀገራችን እንጸልይ።» ሲሉም መክረዋል።
ይርጋለም አበበ ኃይሌ ደግሞ፤ «ሀገር ራሱን ለማጥፋት በወሰነ የፖለቲካ ቡድን ላይ ዘምቷል፤ ይህ አሳዛኝ ቢሆንም አማራጭ አልተገኘም። ከዚህ በኋላም እርቀ ሰላም ይመጣል።» ባይ ናቸው። ብዙአሁ ሙላት በፌስቡክ፤ «ከጦርነት የሚገኝ ትርፍም ጥቅምም የለም ህወቶች እጅ ይስጡ በሰላማዊና በዲሞክራሳዊ አካሄድ የተጀመረውን ጉዟችንን እናስቀጥል እኛ ለገዥው መደብ ሳይሆን ለሀገራችን ሰላም ነው የምንመኘው።» ሲሉ አበበ ገደፋው ደግሞ፤ «በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ተኩስ የከፈተ አሸባሪ ቡድን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።» ነው ያሉት።  

Karte Äthiopien englisch

 ሙሀሺም ሱልዳን ደግሞ ሚዛናዊ መረጃ ፈላጊ ይመስላሉ፤ «ከመንግሥት የምንሰማው ሁሉ ህወሀት የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሰነዘረ የሚል ነው። ከመንግሥት ውጪ ገለልተኛ የተጣራ መረጃ ማግኘት እንችል ይሆን?» በማለት ጠይቀዋል። ሻሎም ክብረት በፋንታቸው፤ «የሀገሬ ህዝብ የውሸት ኖሮ የእውነት ይሞታል፤ የኢትዮጵያ እናቶች ያሳዝኑኛም በጣም! ከቻላችሁ ስለሰላም ጸልዩ።» ነው ያሉት። ጥቁር አዝሙድ የተባሉት የትዊተር ተጠቃሚ፤ «ከኢትዮጵያ ጎን እንቁም! ለኢትዮጵያ እንጸልይ!» ሲሉ ተመሳሳይ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ጉዳዩም የሀገሬውን ብቻ ሳይሆን የመላ ዓለምን ትኩረት ነው የሳበው። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት በጦር መሣሪያ ላንቃ መነጋገሩ ቆሞ ፖለቲከኞቹ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ ለመፈለግ እንዲነጋገሩ እየወተወቱ ነው።
ሳምንቱ ብዙም መልካም ዜና የተወራበት አልነበረም። ያለፈው ሳምንት የተሰናበተው በምዕራብ ወለጋ  ዞን ጉሊሲ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ መርዶ አድርሶ ነው።  በአማራ ተወላጆች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የተደጋገመው መሰል ግድያና ጥቃት ስሜታቸውን እንደነካው የሚያመለክቱት የማኅበራዊ መገናኛው ተጠቃሚዎች ለሌሎች አጋርተዋል፤  ሙሉዓለም ምስጋናው በፌስቡክ፤ «የአማራ መሪዎች ከተቀመጡበት ሳይነሱ በኦነግ ሸኔ የአማራ ህዝብ  የዘር ጭፍጨፋ ዘመቻ ሁለት ዓመት ሞላው። ዛሬም በምዕራብ ወለጋ ከ200 በላይ አማራዎች በኦነግ ሸኔ መጨፍጨፋቸው ተሰማ።» ሲሉ ሚኒልክ ሦስት በበኩላቸው፤ ቡራዩ: ለገጣፎ: ሻሸመኔ: አሰላ: አዳባ: ዶዶላ: ዝዋይ: አሳሳ: ሮቤ: ጊምቢ: ጉሊሶ: ነቀምት: አሩሲ: ባሌ: ሀረርጌ: ወለጋ: ላለፉት ሁለት አመታት በሰበብ አስባቡ ኦሮሞ ክልል አማራ እና ክርስቲያን ላይ የተፈፀሙት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች በዝርዝር አልተመዘገቡም::» ብለዋል። ምትኩ ጌታቸው በፋንታቸው፤ «ንፁሐን ኢትዮጵያውያን የተገደሉት አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው፤ ባለፈው እሁድ ምሽት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ የተፈፀመውን ጥቃት ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘው ይገባል። ለጠፋው የሰው ሕይወት መንግሥት በአፋጣኝ ፍርድ ይስጥ።» ይላሉ።

ባምላክ ላይ ደግሞ ፤ «ለአማራ እንታገላለን የምትሉ ፓርቲዎች በአማራ ላይ በሚደረሰውን በደልና ሲቃይ ለማስቁም እናተ አንድ ሁኑ፤ ለምርጫም ለህዝብ ያመች ዘንድ አንድ ስንሆን ያምርብናል ስንለያይ እጣ ፈንታችን ሞት ነው።» በማለት ይመክራሉ። የአብሳለም ፍቅሩ ሃሳብ ደግሞ ከእሳቸው ይለያል፤ «ብአዴን ግን መቼ ነው የህዝቤን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻልኩም ፤ ህዝቤ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንኳን በይፋ ማውገዝ አይሆንልኝምና አቅምና እውቀቱ ያለው ተከብሮ የሚያስከብር አማራ ሥልጣኔን ይረከበኝ የሚለው?» በማለት ነው የሚጠይቁት። ባሐር አሊ ደግሞ፤ «መንግሥት በሽተኞችን በወቅቱ ለመፈወስ የሚያደርገው ጥረት አናሳ በመሆኑ በሽታው ተንሰራፍቶ ለመንግሥቱ ህልውና አደጋ ከመጋረጡ ባሻገር ለዜጎች ሰቆቃ ምክያት ሆኗል።» ይላሉ።

Symbolbild Twitter
ምስል imago/xim.gs

ኑሩ አህመድ ሌላም ጥቃት እንዳይደርስ የሚል  ስጋት አላቸው፤  «አሁንም በሌላ በኩታቅዷል በዛዉ በምእራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ እምታባል ቀበሌላይ ዛሬከጠዋቱ 3:00 ሳአትላይ ጥቃትሊያደርሱ ሲሉበመሀበረሰቡ እርብብ ተመልሰዋል ይሁንእጂ አሁንም ህዝቡበጣም እቺግርላይነዉ ያለዉ የጉሊሶዉ በኛላይ እዳይደገም ለሚመለከተዉ አካልአድርሱልኝ»

ዳዊት መአረግ ደግሞ « ሰው ክቡር ነው! ሰው በግፍ ሲገደል ዝም አትበሉ! ነገ የእናንተንም በር ማንኳኳቱ አይቀርምና ተቃወሙት።» ይላሉ። ጥቃቱን የፈጸመው ኦነግ ሸኔ ነው ለሚለው የመንግሥት መግለጫ አሰፋ ጌታብቻ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ማንም ይሁን ማንም መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ማስከበር ህገ-መንግሥታዊ ግዴታ አለበት።» የሚል ማሳሰቢያቸውን አጋርተዋል። ሙሴ ሙሳ ደግሞ ጠያቂ ናቸው፤ « ሲኖሩ ነፍጠኛ ተብለው የጥላቻ መርዝ ሲዘራ ዝም ብላችሁ ሲሞቱ ንፁሃን

ትላላችሁ ። ደግም ብሔራዊ የሀዘን ቀን ብሔር ይመርጣል እንዴ?» ዑስማን አህመድም ይጠይቃሉ፤ «መከላከያ በወጣ በሰአታት ልዩነት ነው ስብሰባ ብለው ሰብስበው የረሸኗቸው፤ ሸኔ ከሆነ ልዩ ኃይሉ ምን ይሠራል?» ብሩክ ካሳ ስጋታቸውን በማስቀደም የተመ ድርጅትን ጣልቃ ገብነት ይጠይቃሉ፤ «ነፍስ ይማር! አማራ ከምን ግዜውም በላይ አደጋ ላይ ነው። አሚሶም የተመድ ድረሱልን።» ነው የሚሉት።

የናፍቆት ጥሪ ለጥቃቱ ሰለባዎች እንዴት እንድረስ የሚል ነው፤ «ቤተተሰቦቻቸውን አጥተው፣ ቤት አልባ ሆነው ሜዳ ላይ ላሉት ዜጎች ምን አይነት ድጋፍ ተደርጎላቸው ይሆን? እኛስ እንዴት ልንደርስላቸው እንችላለን? በዚህ ግርግር ፆታዊ ጥቃት ሴቶች እና ህፃናት ላይም ተደርጎ ሌላ ሀዘን እንዳናተርፍ ምን እናድርግ?» ኢባን አሊ ፍትህ ላይ አተኩረዋል፤ «አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጉሊሶ የተካሄደው ግድያ በገለልተኛ አካል ይጣራ ብሏል። ትክክለኛ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ሀሳብ ነው። መቼም ወንጀሉን ከፈጸመው አካል ውጪ ይሄንን የሚቃወም ይኖራል ብለን አናስብም። ይሄንን የሚቃወም ካለም የወንጀሉ ፈጻሚ እሱ ስለመሆኑን አትጠራጠሩ።» 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ