1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቃት በኬንያ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 23 2006

በኬንያ መዲና፣ ናይሮቢ በተጣሉ ሦስት የቦምብ ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና 25 መቁሰላቸውን የኬንያ ሀገር አስተዳደር ባለሥልጣናት አስታወቁ። ትናንት ማታ የተጣሉት ጥቃቶች ዒላማ ያደረጉት በብዛት

https://p.dw.com/p/1BZnR
Nairobi Eastleigh Bombenexplosion 31.03.2014
ምስል picture-alliance/dpa

ሶማሊያውያን በሚኖሩበት በኢስትሌይ ሰፈር የሚገኙ ሁለት የምግብ ቤቶችን እና አንድ ክሊኒክ እንደነበር ባለሥልጣናቱ አክለው ገልጸዋል። ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን ወይም ሰው ባይኖርም፣ የኬንያ ፖሊስ 657 ተጠርጣሪዎችን በዛሬው ዕለት መያዙን አስታውቋል። የናይሮቢ ፖሊስ ኮማንደር እንዳስታወቁት ግን ፣ ጥቃቱ የአሸባሪዎች ስራ ሳይሆን አልቀረም፣ አንዱ የፈነዳው ቦምብም እቤት ውስጥ የተሰራ ሊሆን ይችላል። በጥቃቱ የእጅ ቦምብ መጣሉንም ባካባቢው የነበሩ ያይን ምስክሮች ገልጸዋል። ካሁን ቀደም በኢስትሌይ ሰፈር ለተጣሉ ጥቃቶች ሁሉ ባለፈው መስከረም በናይሮቢ የዌስጌት የገበያ አዳራሽ ጥቃት ጥሎ 67 ሰዎችን የገደለው የሶማልያ ዓማፂ ቡድን አሸባብ ተጠያቂ ተደርጓል። ኬንያ ከትናንቱ ዓይነት ጥቃት በኋላ አዘውትራ ብዙ ተጠርጣሪዎችን ብታስርም ብዙዎቹን መልሳ መልቀቋ ይታወቃል። የኬንያ ፖሊስ ባለፈው ወር ወደብ ከተማ ሞምባሳ ውስጥ አንድ ፈንጂ የጫነ ተሽከርካሪ ማግኘቱን እና ፈንጂው አንድ የገበያ ማዕከልን ለማንጎድ የታሰበ እንደነበር ገልጾዋል። ይህt ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በአንድ የሞምባሳ ቤተ ክርስትያን ጥቃት ጥለው ስድስት ሰዎች መግደላቸው ይታወሳል። አርያም ተክሌ

Nairobi Explosion Anschlag 30.4.14
ምስል Reuters