1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቁሩ ጀርመናዊና የአድዋ ድል ኩራታቸዉ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2006

የአንደኛዉ የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት አባታቸዉ የቀድሞዉ የጀርመን የቅኝ ግዛት አፍሪቃ ሃገር ከካሜሩን ወደ ጀርመን ሲገቡ፤ በደስታ ነበር አቀባበል የተደረገላቸዉ። ቆየት ብሎ ግን አፍሪቃዊዉ በቆዳ ቀለም ላይ የተመሰረተ ጥላቻን አዩ፤ እየቆዩም የቅኝ ግዛት ፊልሞችን በተመለከተ በሚሰሩ ፊልሞች ላይ አጫጭር ተዉኔቶችን እንዲተዉኑ ተደርገዋል።

https://p.dw.com/p/1Bfvn
Frankfurter Buchmesse 2013 - Theodor Michael
ምስል picture-alliance/dpa-Zentralbild


በጎርጎረሳዉያኑ 1925 ዓ,ም ከካሜሩናዊዉ አባታቸዉና ከጀርመናዊት እናታቸዉ በርሊን ላይ የተወለዱት ደራሲና ጋዜጠኛ ቴዉዶር ሚሻኤል፤ ወላጆቻቸዉ በጨቅላነታቸዉ ከዚህ ዓለም ተለይተዉባቸዉ የፋሽት ናዚን ዘረኛ አገዛዝ ሥርዓትን የሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት በችግር አሳልፈዋል። ጥቁር በመሆናቸዉም ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን እንዳይከታተሉም ተደርገዉ ነበር። የኋላ ኋላ ቴዉዶር ሚሻኤል የናዚ ስርዓት ተገርስሶ፤ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አብቅቶ ህልማቸዉን እዉን አደረጉ! ታዋቂ ደራሲ ጋዜጠኛ፤ እንዲሁም በአፍሪቃ ጉዳይ የመንግሥት አማካሪ ሆነዋል። የ89 ዓመቱ ጥቁሩ ጀርመናዊ ቴዉዶር ሚሻኤል« ዶች ዛይን ኡንድ ሽቫርዝዳዙ» «ጀርመናዊ መሆን በዝያ ላይ ጥቁር» በተሰኝ የህይወት ተሞክሮአቸዉን ያስቀመጡበትን መፅሐፍ ለአንባብያን አቅርበዉ፤ በጀርመን የመጽሐፍ ሽያጭ መዘርዝር፤ ከፍተኛዉን ቦታ ይዞ በታሪክ ማስታወሻነቱ ተወዳጅ መሆኑ ተጠቅሶአል። በኢትዮጵያዉያኑ የአድዋ ድል የሚኮሩትን ታዋቂዉን ደራሲና ጋዜጠኛ ጥቁሩን ጀርመናዊ በለቱ ዝግጅታችን ይዘን ቀርበናል
በርሊን ላይ በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 15 ,1925 ዓ,ም ከጀርመናዊ እናታቸዉ እና ከካሜሩናዊ አባታቸዉ የተወለዱት ቴዉዶር ሚሻኤል፤ አንድ ታላቅ ወንድም እና ሶስት እቶችም አልዋቸዉ። ለቤተሰቦቻቸዉ የመጨረሻ ልጅ የነበሩት ቴዉዶር ሚሻኤል፤ ገና የአንድ ዓመት ጨቅላ ህጻን ሳሉ ነበር፤ እናታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩባቸዉ። ሚሻኤል በመጽሀፋቸዉ ላይ እንደተረኩት፤ እሳቸዉ ሲወለዱ፤ እናታቸዉ ብርቱ ችግር አጋጥሞአቸዉ ስለነበር በወተወለዱ በአንድ ዓመት ግዜ ዉስጥ፤ በአደረባቸዉ ፅኑ ህመም፤ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት። ከአንድ አነስተኛ የገበሬ ቤተሰብ የሚወለዱት የሚሻኤል እናት፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1910 ዓም፤ ወደ በርሊን መጥተዉ ነዉ፤ ካሜሩን የመጡትን ባለቤታቸዉን የተዋወቁት። በዝያን ግዜ አንዲት ነጭ ጀርመናዊት ጥቁር ፍቅረኛ መያዝዋ በራሱ፤ አንድ ትልቅ አብዮት ሳይሆን እንዳልቀረ ሚሻኤል በመፃሃፋቸዉ ተርከዋል። ይሁንና ስለ አባታቸዉ እና ስለ እናታቸዉ ግንኙነት ከዚህ ሌላ የሚያዉቁት ነገር እንደሉ በግልፅ አስቀምጠዋል። ምክንያቱም ይላሉ ቴዉዶር በዝያን ግዜ ልጅ ስለነበርኩ ታሪኩን ማወቁ አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነበር፤ ግን ነፍስ አዉቄ ታሪኬን አመጣጤን በዝርዝር ማወቅ በፈለኩበት ወቅት ደግሞ፤ በዝርዝር የሚነግሩኝ ወላጆቼ በህይወት አልነበሩም ሲሉ የህይወት ታሪካቸዉን ባስነበቡበትና በጀርመን የመጻሐፍ መድረክ ተወዳጅነትን አግኝቶ እጅግ ብዙ በተሸጠዉ መፃሐፋቸዉ አስቀምጠዉታል።
« አባቴ የካሜሩን ተወላጅ ነዉ። ካሜሩን በጎርጎረሳዎያኑ 1884 ዓ,ም የጀርመን ቅኝ ግዛት እንደሆነች ይታወቃል። አባቴ ፤ ካሜሩን ፤ በጀርመን የቅኝ ግዛት ስር ከመዉደቅዋ በፊት አልያም የቅኝ ግዛት ልትሆን ስትል ነዉ ወደ ጀርመን የመጣዉ። አባቴ ወደ ጀርመን ስለ ገባበት ግዜ፤ ቤተሰቦቼ የሚሉት የተለያየ አመለካከት ነዉ። ያም ሆነ ይህ በአባቴ ወገን ያለዉ አያቴ በዝያን ግዜ ካሜሩን በጀርመን የቅኝ ግዛት ስር አንድትሆን ስምምነትን ከፈረሙ ታላላቅ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ነበር»
ከጎርጎረሳዉያኑ 1984 ዓ,ም እንስ 1919 ዓ,ም ድረስ ካሜሩን በጀርመን ቅኝ ግዛት ስር እንደነበረች የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአባታቸዉ ካሜሩናዊ የሆኑት ጥቁሩ ጀርመናዊ ቴዉዶር ሚሻኤል፤ ነፍስ ካወቁ በኋላ፤ የጀርመናዊ እናታቸዉን እህቶች ማለትም አክስቶቻቸዉን፤ ስለ አባታቸዉ ማንነት የጀርመን ኑሮና የመሳሰሉትን፤ በዝርዝር ለማወቅ ፈልገዉ ቢጠይቁም፤ መልስ አላገኙም። እንደ ሚሻኤል ምክንያቱ ጀርመናዊት እናታቸዉ ጥቁር አፍሪቃዊ በማግባታቸዉ በቤተሰቡ ዉስጥ የእናቴ ተግባር እንደ አንድ አስነዋሪ ጉዳይ በመቆጠሩ፤ ስለአባታቸዉ ጉዳይ ደፍሮ የሚናገር በመጥፋቱ ነበር። ከአንዲት የጀርመን ገጠር ዉስጥ ይኖሩ የነበሩት የቴዉዶር ሚሻኤል እናት፤ ከመጀመርያ እና ከጀርመናዊዉ ባለቤታቸዉ፤ አንድ ልጅ እንደወለዱ በመፋታታቸዉ ነበር፤ የሚኖሩበትን ገጠር ለቀዉ ወተዉ በርሊን መኖር እንደጀመሩት ፤ ከዝያም ነዉ፤ ካሜሩናዊዉን የቴዉዶር አባት የቀዋወቁት፤ ትዳር መስርተዉ መኖር ሲጀምሩ የቴዉዶር እናት ከመጀመርያ ባለቤታቸዉ ይዘ የመጡትን ልጃቸዉን ለእህቶቻቸዉ ሰተዉ ከካሜሩናዊ ባለቤታቸዉ ጋር፤ በትዳር ሲኖሩ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶችን ይወልዳሉ። በዝያን ግዜ አያቴ ከጀርመናዉያኑ ጋር የቅኝ ግዛት ዉሉን ሲፈራረሙ ካሜሩናዉያኑ የሚያዉቁት ነገር አልነበረም የሚሉት ቴዉዶር ሚሻኤል፤ ስለ ቅኝ ግዛቱ ዉል እንዲህ ይገልፃሉ
« ካሜሩናዉያኑ በቅኝ ግዛት ለመዉደቅ በዉል ሲፈራረሙ በርግጥ የሚያዉቁት አንዳችንም ነገር አልነበረም። ትምህርት ቤት እንኳ ምን እንደሆነ አያዉቁም፤ አይፅፉም፤ አያነቡም። ጀርመናዉያኑ ለመፈራረም ያቀረቡት የስምምነት ዉል በቋንቋ ምክንያት በተደጋጋሚ ተተርጉሞ እንዲረዱት በተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎ እንደነበር ከታሪክ ተረድቻለሁ። እዚህ ላይ ለማለት የፈለኩት አባቴ ወደ ጀርመን የመጣዉ ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት ነዉ። ከዝያም እናቴን በርሊን ከተማ ላይ ተዋዉቆ በጎርጎረሳዊዉ 1915 ዓ,ም ትዳር መስርቶ አራት ልጆችን አፍርተዋል፤ እኔ ደግሞ የመጨረሻ ልጅ ነኝ»
የአንደኛዉ ዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኃላ በጎርጎረሳዉያኑ 1925 ዓ,ም የተወለዱት ቴዉዶር ሚሻኤል፤ አንድ ዓመት ሲሆናቸዉ እናታቸዉ በመሞታቸዉ ካሜሩናዊዉ አባታቸዉ አራት ልጆቻቸዉን ይዘዉ ብዙም ሳይቆዩ ሌላ ጀርመናዊትን ያገባሉ። ግን አራት ህጻናት ያለበት ቤት የገቡት አዲስዋ ጀርመናዊት ሚስት፤ ስራ ስለበዛባቸዉ ትዳራቸዉ፤ ለአንድ ዓመት እንኳ ሳይዘይልቅ ይፈርሳል። ቴዉዶር ሚሻኤል የህይወት ታሬካቸዉን ባስቀመጡበት መፅሐፋቸዉ እንደገለፁት፤ አባታቸዉ ሁለተኛ ትዳራቸዉ ከፈረሰ በኃላ በርካታ ሴቶች፤ በአባቴ ጥሩ ፀባይ ተማርከዉ ከአባቴን ጋር ግንኙነት ቢፈልጉም፤ ከአራት ዓመት እስከ አስራ አራት ዓመት የሆኑን አራት ልጆቹን እያዩ፤ በፍርሃት ሚስት ሳያገኝ ቀረ ሲሉ ገልፀዉታል፤ ከዝያም ካሜሩናዊዉ የቴዉዶር አባት በብስጭት መጠጥ ማዘዉተራቸዉን፤ ስራም ማጣታቸዉንም አልሸሸጉም። እንድያም ሆኑ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ፤ ሰብስቦ የያዘን ካሚሩናዊ አባታቸን፤ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ቤተሰባችን ሁሉ ተበታተነ እኛም ልጆች በተለያዩ ቦታዎች አሳዳጊ አግኝተን ተለያየን ሲሉ ይናገራሉ። በልጅነት እድሜያቸዉ ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት ያዩት ቴዉዶር ሚሻኤል፤ እስራ በጎርጎረሳዉያኑ 1943 ዓ,ም 18 ዓመት ሲሞላቸዉ ለዓመታት በግዴታ ለናዚ የስራ ዘመቻ ተልከዋዋል። ቴዉዶር ሚሻኤል በዝያን ወቅት ስለነበረዉ የትምህርት ህይወታቸዉ እንዲህ ይተርካሉ፤
« የሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት አይቻለሁ። በወቅቱ ትምhreት ቤት መሄድ ተፈቅዶልኝ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህቴንም አጠናቅቄያለሁ ግን፤ በዝያንግ ግዜ የኑረንበርገር ህግ ተብሎ በሚጠራዉ የናዚ መንግስት ህግ መሰረት የከፍተና ደረጃ ትምህርቴን መከታተል አልተፈቀደልኝም። ምክንያቱም በህጉ መሰረት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትን መከታተል የሚችሉት ነጭ የቆዳ ቀለም እንዲሁም ሰማያዊ የአይን ቀለም ያላቸዉ የሰሜን አዉሪጳ ተወላጆች ብቻ ነበሩ። እንዲህ አይነቱን ህግ እንደኔ ያለ ጥቁር አፍሪቃዊ ሰዉ ለመረዳት በጣም ይከብደዋል።»
በዝያን ግዜ አብሲንያ በመባል ትጠራ የነበረዉ ኢትዮጵያ በምዕራባዉያን በቅኝ ያልተያዘች ብቸኛዋ አፍሪቃዊ ሃገር መሆንዋን በመፃሃፋቸዉ የጠቀሱት ቴዉዶር ሚሻኤል በተለይ ጣልያን ድል የተደረገበት ከ1896 የአድዋ ድል በኋላ በአዉሮጳ የነበረዉ ፖለቲካ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን አትተዋል። በዚህም አብዛኛዉ የአዉሮጳ ሃገር ወደ ጣልያን አድልቶ፤ ለኢትዮጵያ እንብዛም ፍቅሩን እንዳላሳየም አልሸሸጉም።በጎርጎረሳዉያኑ 1935 ዓ,ም ጣልያን ዳግም ኢትዮጵያን ለመዉረር ቢነሳም እንዳልሆነለትም አትተዋል። ይህንን ቂም በመያዝ ከአዉሮጳ ይልቅ እስካንዲኒቪያን ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት እንደነበራቸዉ ጥቁሩ ጀርመናዊ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ቴዉዶር ሚሻኤል ይናገራሉ። እንደ ቴዉዶር ሚሻኤል በጎርጎረሳዉያኑ 1937 ዓ,ም ከአንድ ወልደ ፃድቅ ከሚባል ኢትዮጵያዊ ጋር፤ በአንድ የጀርመን ሰርከስ ቡድን ዉስጥ ሲሰሩ እንደነበርም በመፃሃፋቸዉ ያስታዉሳሉ። በዝያን ግዜ ጀርመን ስራ አጥተን ወደ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር በአንድ ሰርከስ ቡድን ዉስጥ እንደ ብርቅዬ ጥቁሮች ለማገልገል ወደ ስዊድን መጓዛቸዉንና በዝያን ግዜ ኢትዮጵያዊ በመባል ክብርም እንደነበር ያትታሉ።
« አዎ ስዊድን ነበርኩ። በዝያ ወቅት ስዊድን የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ ሃገር ነበረች። ባጠቃላይ የስካንዲኒቪያን ሃገራት በሙሉ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸዉ። በአንድ የጀርመን ሰርከስ ቡድን ዉስጥ እኔ እና አንድ ወልደፃድቅ የሚባል ኢትዮጵያዊ እንደ ብርቅዬ ጥቁር ህጻናት ለአንድ ዓመት ስዊድን ዉስጥ ቆይተን የተለያዩ ዝግጅቶችን አሳይተናል። ለነገሩ በዝያን ግዜ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መታየቱ እንደ ፖለቲካ ጨዋታ መሆኑ ነበር። እና እኔም ኢትዮጵያዊ ነህ ተብዬ ወደዝያ ስላክ፤ የ12 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከጀርመን አብሮኝ ወደ ስዊድን የተጓዘዉ ወልደ ጻድቅ የተባለዉ ባልደረባዩ ከዝያ ተመልሰን በርሊን ሽፓንዳዉ ይኖር ነበር ። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኃላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። »
በናዚ አስተዳደር ቴዉዶር ሚሻኤል ቀንና ለሊት ግንባታ ስራ ላይ ተገደዉ ይሰሩ አንደነበር፤ በቀን ዉስጥ ለአንድ ግዜ ብቻ እረፍት እንደነበራቸዉ፤ ረሃብ እና የእንቅልፍ እጥረት ይማቅቁ እንደነበር በመፃሃፋቸዉ አስቀምጠዉታል። ቴዉዶር ሚሻኤል የሁለተኛዉ ዓለም ከተጠናቀቀ በኃላ በሃንቡርግ በሚገኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የፖለቲካ ሳይንስና የኤኮኖሚ ትምህርታቸዉን ጀምረዉ ፓሪስ በሚገኘዉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቀዋል። ለብዙ ዘመናት በጋዜጠኝነትና በአፍሪቃ ጉዳይ በአማካሪነትም ሰርተዋል፤
« ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ከዓመታት በኃላ የኤኮኖሚ እና ፤ በማህበራዊ የከፍተኛ ትምህርቴን ተከታትዬ ፤ በጋዜጠኝነት እንዲሁም በጀርመን መንግስት አስተዳደር ዉስጥ በአማካሪነት አገልግያለሁ። በኮለኝ ከተማ ዉስጥ ለረጅም ዓመታት በአፍሪቃ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ዘገባዎችን አቅርቤያለሁ። የዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ እንደተመሰረተ በተለይ በመጀመርያዎቹ ዓመታት፤ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ እና አስተያየቶችን በመስጠት በማማከር ከዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ ጋር ለዓመታት በቅርበት ሰርቻለሁ» ቴዉዶር ሚሻኤል ስለ አፍሪቃ ታሪክ በጥልቀት በማወቃቸዉ በጀርመን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች በአማካሪነት አገልግለዋል። ግን አፍሪቃንስ ጎብኝተዉ ይሆን? « የተለያዩ ሃገራትን ለተደጋጋሚ ግዝያት ጎብኝቻለሁ። እንዲሁ ካሜሩንን ተመላልሼ ጎብኝቻታለሁ። ያዉ እንደሚታወቀዉ ካሜሩን የአባቴ ሃገር ነዉ። አንድ የአፍሪቃዊ ክልስ ከአዉሮጳ ወደ አፍሪቃ ሲመጣ፤ ሃገሪነዉ በሚለዉ በዚያ የአፍሪቃ ሃገርም ቢሆን ባዳ መሆኑ የታወቀ ነዉ። እንዲህ ስል ካሜሩንን ስጎበኝ አቀባበል አልተደረገለኝም ማለቴ አይደለም። ሌላዉ የኢትዮጵያን ታሪክ በተለይ እጅግ የሚያረካኝ የአድዋ ታሪክ ጠንቅቄ ባዉቅም፤ ኢትዮጵያን አልጎበኘኋትም፤ ለምን እንደሆን ግን እኔም ራሴ መልስ ያላገኘሁለት እና የሚቆጨኝ ጉዳይ ነዉ።»
እንድያም ሆኖ ታዋቂዉ የ89 ዓመቱ ደራሲና የአፍሪቃ ጉዳዮች አማካሪ ቴዉዶር ሚሻኤል በሚኖሩበት ኮለኝ ከተማ ከሰላሳ ዓመት በላይ የሆነዉን የኢትዮጵያዉያኑን ሚካኤል ቤተ ክርስትያን በዓመት 3 አልያም 4 ግዜ በakeብር እንግድነት በመቅረብ የኢትዮጵያን ባህላዊ ክብረ ባአላትን ከባለቤታቸዉና ከኢትዮጵያዉያን ጋር እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ። በዚህም በርካታ ኢትዮጵያዉያን ወዳጆችን አፍርተዋል። የኢትዮጵያዉያን ባህል አልባስዋትዋን እና ባህላዊ ምግቦችዋን ይበልጥ ተዋዉቀዋልም።ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ቅር የሚለኝ አንድ ነገር አሉ ደራሲ ቴዉዶር በመቀጠል፤ «በ1960 ዎቹ መጨረሻ የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ አልጀርስ ላይ በተደረገ ግዜ ተገኝቼ ነበር። በዝያ ወቅት አፄ ሃይለ ስላሴን በአይኔ አይቻቸዋለሁ። ታድያ ሁል ግዜ የንጉሰ ነገስት ሃይለ ስላሴ መጨረሻዎቹ የስልጣን ቀናት በጣም ከሚሳዝኑኝ ክስተቶች አንዱ ነዉ»
የደራሲ ቴዉዶር «ጀርመናዊ ዜጋ ሆኖ ጥቁር መሆን» በተሰኘዉ የህይወት ታሪካቸዉን ያስቀመጡበት መፀሃፍ በጀርመን የመፃህፍ ሽያጭ መድረክ ብዙ አንባብያን በመግዛታቸዉ ተወዳጅ መሆኑ ተነግሮለታል፤ ደራሲዉ መፃህፉን ካነበቡ ሰዎች ምን አይነት አስተያየት ደረሶአቸዉ ይሆን፤
« የሚገርመዉ እስካሁን የጀርመንን ታሪክ የሚያሳይ መፃህፍ ነዉ በማለት ሙገሳ እና ማበረታቻ አይነት አስተያየት ብቻ ነዉ የደረሰኝ ፤ ግን እኔ በተቃራኒዉ ማለትም ስለመፅሐፉ ትችት ቢደርሰኝም በጣም ደስ ባለኝ ነበር፤ ግን እስካሁን ገንቢ ሂስ ብቻ ነዉ ያገኘሁት»
የ89 ዓመቱ ጥቁር ጀርመናዊ ቴዉዶር ሚሻኤል፤ በናዚ አገዛዝ ዘመን በረሃብ ተሰቃይተዉ እንደነበር ምግብን ጠግበዉ በልተዉ እንደማያዉቁ በመፃሃፋቸዉ ላይ አትተዋል። ለዓላማቸዉ በፅኑ የታገሉት ቴዎዶር ሚሻኤል የናዚ ዘመን ተገርስሶ በጀርመን የዲሞክራሲ ስርዓት ሰፍኖ ፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ፤ እዉቅ ጋዜጠኛ እና ደራሲ እንዲሁም ለጀርመን መንግስት የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ እስከመሆን ደርሰዋል። በጡረታ ላይ የሚገኙት እኝህ ጥቁር ጀርመናዊ፤ ዛሪም ለአፍሪቃ አምባሳደር በመሆን፤ በጀርመን እርዳታን እና ምክርን ለሚሹ አፍሪቃዉያን ምክርን በመለገስ በአንድ የአፍሪቃዉያን መርጃ ማህበር ዉስጥ ያገለግላሉ። እንደ ቴዎዶር ሚሻኤል፤ የአፍሪቃን ታሪክ ሲጠቅሱ፤ ለሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት የነጻነት ጮራን የፈነጠቀ ብሎም የዓለም ፖለቲካን የቀየረዉን የኢትዮጵያዉያኑን የአድዋን ድል፤ በቀደምትነት በኩራት በመጥቀስ፤ መፅሃፋቸዉ በተለይ ከሃገሩ ርቆ የሚኖር ለዓላማ ፅናትና ጥንካሪዉ ድጋፍ ይሆነዋል የሚል እምነት እንዳላቸዉ በመጥቀስ ቃለ-ምልልሳቸዉን ደምድመዋል። በአባታቸዉ ካሜሩናዊ የሆኑት እዉቁ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ቴዉዶር ሚሻኤል፤ ከጀርመናዊት ባለቤታቸዉ አራት ልጆችን ወልደዉ፤ በልጅ ልጅ፤ ልጅ ልጆቻዉ ፍቅር ተከበዉ አምስተኛዉ የዘር ሃረግ ግንድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅመጫኛዉን በመጫን ይከታተሉ።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ

Theodor MICHAEL
ምስል Imago/Sven Simon
Deutsche Truppen in Brünn - Einmarsch der Wehrmacht in die Tschechoslowakei
ምስል cc/by/sa/Bundesarchiv/Bild 183-2004-0813-500
Buchcover Wonja Michael Deutsch sein und schwarz dazu
ምስል dtv