1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽ በመንታ መንገድ ላይ

ሐሙስ፣ ሰኔ 27 2005

በግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዝደንት ሞሐመድ ሞርሲ በጦር ኃይሉ ከስልጣናቸዉ ከተነሱ ወዲህ የአገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ ወዴትነት እስካሁን አለየለትም።

https://p.dw.com/p/192Ms
ምስል Reuters

ማምሻዉን በሚሊዮኖች የተገመቱ ዜጎች በትረ ስልጣን ከጨበጡ አንድ ዓመት ብቻ ያስቆጠሩት ሞርሲ የቀድሞዉን ፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባረክን ባስወገደዉ ዓይነት ህዝባዊ አመፅ በመሰናበታቸዉ ደስታቸዉን ሲገልፁ ታይተዋል። የጦር ኃይሉ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ያዘጋጀዉን ረቂቅ ሕገመንግስት በማገድ ጊዜያዊ ሲቪል መንግስት ለማቋቋም መዘጋጀቱን እንዲሁም አዲስ ምርጫም እንደሚካሄድ አስታዉቋል።

ፕሬዝደንት ሞሐመድ ሞርሲ እና ፓርቲያቸዉ ሙስሊም ወንድማማቾች የቀናቸዉ አይመስልም። በሕዝባዊ አመጽና በመንግስት ለዉጥ ሂደት የተዳከመ ኤኮኖሚ፤ ለዘብተኛና ፅንፈኛ እስላማዉያን ሽኩቻ፤ ሥራ አጥነትና የነዳጅ አቅርቦት፣ የኃይልና የልማት ተግባራት ማንቀላፋት በግብጽ ባፋጣኝ እንዲታይ የተጠበቀዉን ለዉጥ እንዲያሳዩ እድል አልሰጧቸዉም። ቀዳሚያቸዉን አስወግዶ ሞርሲን ከስልጣን ያወጣቸዉ ሕዝባዊ አመጽ እሳቸዉን ዳግም ለማሰናበት እንደታዛቢዎች ግምት ከዚያኛዉ እጥፍ ነዉ፤ አራት ቀናት ቢወስድም። ለተቃዋሚዎቻቸዉ ጥያቄና ለጦርኃይሉ ማሳሰቢያ አሻፈረኝ ያሉት ሞርሲ ትናንት ማምሻዉን ተገደዉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠዉ የያዙትን ስልጣን ለቀቁ።

Ägypten Militär stürzt Präsident Mursi Abdulfettah es Sisi
አብዱልፋታህ አል ሲሲምስል picture alliance/AA

ዛሬ ደግሞ ሌሎች 12 ረዳቶቻቸዉን ጨምሮ በፕሬዝደንቱ መኖሪያ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ። ግብጽ ዉስጥ ወታደራዊዉ ኃይል የፈፀመዉን ተግባር ጀርመን ዴሞክራሲን ወደኋላ ይቀለብሳል ስትል ብሪታንያ አዉግዛለች። ቱርክ በኩሏ የተፈፀመዉ መፈንቅለ መንግስት ተቀባይነት እንደሌለዉ ገልጻለች። ቱኒዚያም እንዲሁ እዉቅና ካተረፈዉ ሕዝባዊ አመጽ ማግስት በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ስልጣን የያዘዉን አካል በወታደራዊ ኃይል ማንሳት ታላቅ ኪሳራ ነዉ ስትል ተቃዉማለች። ለተቃዉሞ አደባባይ ለወጣዉ ሕዝብ አጋርነቱን በማሳየት ሞርሲን ያወረደዉ የጦር ኃይል አዛዥ አብዱልፋታህ አል ሲሲ ድርጊቱ የመንግስት ግልበጣ ሳይሆን ፕሬዝደንቱ ለብሄራዊ ዉይይት ፈቃደኛ ባለመሆናቸዉ የተከሰተ መሆኑን ነዉ ያመለከቱት፤

«ካለፈዉ ህዳር አንስቶ ሠራዊቱ ፖለቲከኞች በሙሉ እና ብሄራዊ ኃይሉ በጋራ አጠቃላይ ብሄራዊ ዉይይት እንዲያካሂዱ ሲጋብዝ ቆይቷል። ፕሬዝደንቱ ግን ይህን ንግግር ባለቀ ሰዓት ዉድቅ አደረጉ።»

የጦር ኃይሉ ለሞርሲ የሰጠቁ የጊዜ ገደብ ሲገባደድ ግን የለዉጥ አቀንቃኙ ሞሐመድ ኤል ባራዳይ፤ እስልምና ሃይማኖት መሪ ሼኽ አህመድ አል ጠይብ፤ እንዲሁም የኮፕት ክርስቲያኖች ፓርትሪያርክ ቴዎድሮስ ሁለተኛ፤ የተቃዉሞ ፖለቲከኞችና የሳላፊያ ንቅናቄ አንዳንድ አባላት ከአል ሲሲጋ ተገናኝተዉ ተወያይተዋል። ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በዚህ ለመሳተፍ አልፈቀደም። ሞርሲ ባለቀዉ ሰዓት ሁሉ የጦር ኃይሉን ከተቃዋሚዎቻቸዉ ወግኗል በማለት ያንን እንደማይቀበሉ ሲገልፁ ነዉ የቆዩት። የጦር ኃይሉ በበኩሉ ደም እንዳይፋሰስ የሕዝብን ፍላጎት የማስከበር ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ እያለ ነዉ።

Ägypten Adli Mansour Vereidigung
አዲል ማንሱር ቃለመሃላ ሲፈጽሙምስል Reuters

በዛሬዉ ዕለት ደግሞ የሕገ መንግስታዊዉ ፍርድ ቤት የበላይ ዳኛ አዲል ማንሱር በአገር መሪነት ቃለመሃላ ፈጽመዋል።

«ሕግንና ህገመንግስቱን በማክበር በፍትሃዊነት ለማስተዳደር በፈጣሪ ስም እምላለሁ።»

የ67ዓመቱ ማንሱር የአገሪቱን የሽግግር መንግስት እንደሚመሩ ሞርሲ ከስልጣን ሳይወገዱም ዉስጥ ዉስጡን ሲነገር እንደሰነበተ ነዉ መረጃዎች የሚጠቁሙት። አዲል ማንሱር ግብጽ ቀጣዩን ምርጫ እስክታኪያሂድ በተሰጣቸዉ ኃላፊነት ላይ ይቆያሉ። የምርጫዉን ቀን የማሳወቅም የእሳቸዉ ድርሻ ነዉ። በወቅቱ ላለዉ የኤኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠትም ጊዜዉ መጓተት እንደማይኖርበት ይገመታል። የቀድሞዉ ፕሬዝደንታዊ እጩ ተፎካካሪና የግብጽ የድህነት ግንባር አባል ሃምዲን ሳባሂ አዲሲቷን ግብጽ ለመገንባት በሕዝቡ መካከል እርቀ ሰላም፣ እንዲሁም በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ማኅበራዊ ቡድኖች መካከል መግባባት መስፈን እንደሚኖርበት አመልክተዋል፤

«የወደፊት እጣ ፈንታችን በር ክፍት ነዉ ሆኖም እዚያ ለመድረስ ከፍተኛ ማስተዋልና ጥንቃቄ ይጠይቃል። ያም የሽግግሩ ሂደት በእቅዱ መሰረት ከሄደ ማለት ነዉ። አመፅን ከሚያባብሱት በቀርም ለመቻቻል እና ለብሄራዊ እርቅ የቀረበዉ ጥሪም ከምር መወሰድ ይኖርበታል።»

በዛሬዉ ዕለት የፍትህ ጉዳይ ባለስልጣናት ፕሬዝደንት ሞርሲ እና ሌሎች 15 የፓርቲያቸዉ አባላት የሕግ አስፈጻሚዉ አካል ላይ ሰንዝረዋል ያሉትን ስድብ እየመረመሩ መሆኑ ገልጸዋል። ዳኛ ታርዋት ሃማድ አያይዘዉ እንዳመለከቱትም የጉዞ እግድ ተጥሎባቸዋል። የአፍሪቃ ኅብረት የግብጽ የፖለቲካ ሂደቶች አስመልክቶ እንደሚነጋገር የኅብረቱ ኮሚሽነር ራምታን ላማምራ ገልጸዋል። ኅብረቱ የመንግስት ስልጣን በመፈንቅል የሚወሰድባቸዉ ሃገሮችን ከአባልነት ሲያግድ ቆይቷል። ግብጽ ላይ የሚወስደዉ ርምጃም ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል የኅብረቱ ባለስልጣናት አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ