1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድርን አቋረጡ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 29 2012

ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር ማቋረጣቸውን አስታወቁ። ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ከሚደረገው ድርድር ያፈነገጡት ኢትዮጵያ ትናንት በተደረገው ድርድር የግድቡን ውኃ አሞላል የተመለከተ ረቂቅ ደንብ ካቀረበች በኋላ ነው።

https://p.dw.com/p/3gTZL
Äthiopien Addis Abeba | Diskussion Blue Nile & Renaissance-Damm | Flaggen
ምስል DW/G. Tedla

ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር ማቋረጣቸውን አስታወቁ። ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ከሚደረገው ድርድር ያፈነገጡት ኢትዮጵያ ትናንት በተደረገው ድርድር የግድቡን ውኃ አሞላል የተመለከተ ረቂቅ ደንብ ካቀረበች በኋላ ነው። የሱዳኑ የመስኖ ምኒስትር ያሲር አባስ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ረቂቅ ሙሉ ድርድሩን የሚያሰጋ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አባስ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሰነድ የግድቡን የወደፊት አስተዳደር በአባይ ውኃ ላይ ለሚደረስ አጠቃላይ ስምምነት የሚተው ነው። ግብጽም እንደ ሱዳን ሁሉ ኢትዮጵያ ለድርድር ያቀረበችው ሰነድ የግድቡን የወደ ፊት የሥራ ክንውን እና ሕጋዊ የቅራኔ አፈታትን ያላካተተ ነው ብላለች። ኢትዮጵያ ያቀረበችው የግድቡን ውኃ አሞላል የተመለከተ የሥምምነት ረቂቅ "የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጽህፈት ቤት ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መሠረት" መሆኑን የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትሩ ስለሺ በቀለ "የመጀመሪያውን የውኃ አሞላል ሥምምነት በፍጥነት ለመፈረም እና በቀጣይ ጊዜያት አጠቃላይ ሥምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር ለመቀጠል" ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

 

እሸቴ በቀለ 

አዜብ ታደሰ