1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግሪክ፥ አዲሱ የቁጠባ እቅዷ አወያየ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4 2007

ግሪክ ተጨማሪ ብድር እንድታገኝ ያቀረበችው አዲስ የቁጠባ ዕቅድ ላይ ለመደራደር የዩሮ ቡድን የገንዘብ ሚኒስትሮች እንዲሁም አበዳሪ መንግሥታትና ተቋማት ዛሬ ቤልጄም-ብራስልስ ተሰብስበው መክረዋል። ከድርድሩ በፊት የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ዎልፍጋንግ ሾይብለ ግሪክ ለ3ኛ ዙር ያቀረበችው የቁጠባ እቅድ አጥጋቢ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1FxJA
Griechenland EU Fahne vor dem Parlament in Athen
ምስል picture-alliance/R. Geiss

የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ዛሬ አበዳሪዎቻቸው የሚወያዩነትን የቁጠባ እና የተሐድሶ መርሐ-ግብር ዓርብ ሌሊት የግሪክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቆታል። ከ300 የምክር ቤት አባላቱ 251ዱ አዲሱን መርሐ ግብር ሲደግፉ፤ 32ቱ ደግሞ ተቃውመዋል። 8 ደግሞ ድምፀ- ተአቅቦ አድርገዋል። ተዐቅቦ ካደረጉት መካከል የገዢው የሲፕራስ «ሲሪዛ» ፓርቲ አባላት ይገኙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራስ አዲሱን የቁጠባ እና የተሐድሶ መርሐ-ግብር ፓርላማቸው ገና ሳያፀድቀው ሐሙስ ምሽት ለዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ ሀገሮች ልከው ነበር።

የዩሮ ዞን አባል ሃገራት 19 ሚንስትሮች እና ሌሎች ባለሥልጣናት ዛሬ ባኪያሄዱት ስብሰባ ግሪክ ያቀረበችው አዲስ የቁጠባ ዕቅድ «እጅግ አጣብቂኝ» ውስጥ የሚከት መሆኑን አውስተዋል። ግሪክ ለቀሪዎቹ 18 የዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ ሃገራት አዲስ ያለችው ዕቅድ ብታቀርብም ሚንስትሮቹ ቀላል መፍትኄ ማግኘት እንደማይቻል ጠቁመዋል።

Europäische Union Flaggen Brüssel
ምስል DW/A. Rönsberg

በግሪክ የተካሄደዉ የአበዳሪ ድርጅቶችን ቅድመ ሁኔታ የመቀበል ያለመቀበል ሕዝበ ዉሳኔ ከስልሳ ከመቶ በላይ የሚሆነዉ የግሪክ ሕዝብ ቅድመ ሁኔታዉን መቃወሙ ከታወቀ በኋላ በግሪክ፤ በአበዳሪዎቿና በዩሮ ተጠቃሚ ሃገራት መካከል ያለዉ ግንኙነት አጣብቂኝ ዉስጥ ገብቷል። በአሁኑ ወቅት ግሪክ ዉስጥ ባንኮች ተዘግተዋል። የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዉም ቆሟል። ይህ ችግሯ ባፋጣኝ ካልተፈታም ግሪክ ከዩሮ ልትወጣ ልትገደድ፤ ሕዝቡም ለከፋ ችግር ሊጋለጥ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ግሪክን ከውድቀት ለመታደግ የግሪክ መንግሥት ለውይይት ያቀረበው አዲስ የቁጠባ እና የተሐድሶ መርሐ-ግብር ለተግባራዊነቱ 89 ቢሊዮን ዶላር ግድም ወጪ እንደሚያስፈልገው ተጠቅሷል። ግሪክ አዲስ ያቀረበችው ዕቅድ በቀላሉ ተቀባይነት የሚያገኝ አይመስልም። የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ዎልፍጋንግ ሾይብለ «በአውሮጳ ኅብረት ውል መሰረት የዕዳ ስረዛ ማድረግ አይቻልም።» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ