1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጅቡቲ ዳራና ምርጫዋ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2003

ጥንት ቅኝ ገዢዎች ሲሻሙ ሐገር አደረጓት። የሐይለኛ ጎረቤቶችዋ ዉጊያ ድሮ የነፃነትዋ ብስራት ነበር።በቅርቡ የገቢዋ ምንጭ።እንደ ጥንት-ድሮዉ ሁሉ ዘንድሮም ጎረቤቶችዋ ሲዛዛቱ፣ትላልቁ አለም የሊቢያ፣ ኮትዲቯር ገድል-ድሉን ሲያብለስል የድሮ መሪዋን አዲስ መረጠች

https://p.dw.com/p/RH53
ጅቡቲ ወደብ

10 04 11

አረብ-ዓለም የቱኒዚያ፣ የግብፅ፣ እያለ የአረቦችን ሕዝባዊ አብዮት ምክንያት ሒደት፣ዉጤትን ሲያሰለ የኢሳ፣ አፋሮቹ ምድር ግን የአረብ ሊግ አባሊቱ ሐገር የአረብነቱ ወግ ማዕረግ አይለፈኝ ያለች መስላ ነበር።ጅቡቲ።ሕዝባዊ አመፅ።ትልቁ አለም የትንሺቱን ሐገር ትልቅ አመፅ ይዘት ክረትን ሳያስተዉል ገዢዎችዋ ደረገሙት።ጥንት ድሮም እንደያ ነበረች።ጥንት ቅኝ ገዢዎች ሲሻሙ ሐገር አደረጓት። የሐይለኛ ጎረቤቶችዋ ዉጊያ ድሮ የነፃነትዋ ብስራት ነበር።በቅርቡ የገቢዋ ምንጭ።እንደ ጥንት-ድሮዉ ሁሉ ዘንድሮም ጎረቤቶችዋ ሲዛዛቱ፣ትላልቁ አለም የሊቢያ፣ ኮትዲቯር ገድል-ድሉን ሲያብለስል የድሮ መሪዋን አዲስ መረጠች።ጅቡቲ።ያለፈ ታሪኳ ማጣቀሻ ምርጫዋ መነሻችን፣ ዉጤት እንድምታዉ መድረሻችን ነዉ ላፍ አብራችሁን ቆዩ።

ፈረንሳዊዉ የአፍሪቃ ፖለቲካ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት አርብ ጅቡቲ ላይ የሆነዉን፣ ከመሆኑ በፊት ለማወቅ ብዙ ምርምር እና ጥናት አይጠይቅም ነበር።

«ሁለት እጩዎች ናቸዉ ያሉት።ያሁኑ ፕሬዝዳንትና የቅሞዉ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት።ሁለተኛዉ ለመጀመሪያዉ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆናቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።ሥለዚሕ እንዲያዉ ተዓምር ካልጠበቅን በስተቀር-አዎ እስማኤል ዑመር ጉሌሕ የሚቀጥለዉ ፕሬዝዳንት ናቸዉ።»

በርግጥም ሆነ።ፕሬዝዳት ኢስማኤል ኡመር ጉሌሕ ብቻቸዉን ላለመባል ያስከተሏቸዉን መናጆ በረጅም ርቀት ጥለዉ አሸነፉ አስባሉ።ቅዳሜ ይፋ በሆነዉ ዉጤት መሠረት ጉሌሕ ከተሰጠዉ ድምፅ ወደ ሰማንያ አንድ ከመቶ ያሕሉን አግኝተዋል።ጉሌሕን በግል የተፎካከሩት የቀድሞዉ የሐገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳት መሐመድ ወርሰሜ አስራ-ዘጠኝ በመቶ ያሕሉን ድምፅ አገኙ።

የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወክለዉ በምርጫዉ ይሳተፋሉ ተብለዉ የነበሩት እጭዎች ባለፈዉ የካቲት ታስረዉ ነበር።በዚሕም ምክንያት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫዉ አልተወዳደሩም።የፕሬዝዳት ጉሌሕ መንግሥት ተቃዋሚዎችን በሰበብ አስባቡ ከምርጫ ሲገፋቸዉ ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም። ፕሬዝዳት ጉሌሕም ብቻቸዉን ወይም የብቻቸዉን ያክል ተወዳድረዉ አሸነፉ ሲባልላቸዉ ያሁኑ አዲስ አይደለም።

የጅቡቲን የመጀመሪያ ፕሬዝዳት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶንን ለመተካት በ1999 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) በተደረገዉ ምርጫ በኦፕቲዶን ተመርጠዉ የኦፕቲዶንን ፓርቲ ወክለዉ የተወዳደሩት ጉሌሕ ተፎካካሪዎቻቸዉን በከፍተኛ ልዩነት አሸነፈዉ ነበር።በንፅፅር እይታ የያኔዉ ምርጫ የተሻለ ተብሎ ነበር።

Präsident Ismail Omar Guelleh Dschibuti
ጉሌሕምስል picture-alliance/ dpa

በስድስተኛዉ አመት ሚዚያ ሁለት ሺሕ አምስት በተደረገዉ ምርጫ ግን ጉሌሕ ለሁለተኛ ዘመነ ሥልጣን ብቻቸዉን ተወዳድረዉ ነበር ያሸነፉት።በሐገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ያ ምርጫ ለጉሌሕ የመጨረሻቸዉ ዘመነ-ሥልጣን በሆነ ነበር።እሳቸዉም ሕገ-መንግሥቱን ለማክበር ቃል ገብተዉ ነበር።ሁሉም ግን ነበር-ነዉ ዛሬ።ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት እንደ ብዙዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች ሁሉ ጉሌሕ ቃል-ሕገ መንግሥታቸዉን ለማጠፍ አለማነቱም።

«ከዚሕ ቀደም የተደረጉትን ምርጫዎች ብንመለከት አፍሪቃ ዉስጥ እየተለመደ የመጣዉን አሳሳቢ ፖለቲካዊ ልምድን እናያለን።ባለፈዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እስማሬል ዑመር ጉሌሕ ሕገ መንግሥቱን የመለወጥ ፍላጎት እንደሌላቸዉ እና ከሁለተኛዉ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ በሕዋላ እንደሚሰናበቱ አስታዉቀዉ ነበር።ለተረጋጋ ሽግግር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዉ ነበር።ከጥቂት ጊዜ በፊት ግን የራሳቸዉ ፓርቲ እሳቸዉ ብቸኛዉ እጩዉ እንደሆኑ ወሰኑ።በዚሕም መሠረት ፓርቲዉ ሕገ-መንግሥቱ እንዲቀየር ወሰነ።ብልጣ ብልጡ ጉሌሕም ይሕን ዉሳኔ አፀደቁ እና ጅቡቲን ለመግዛት ከሕወታቸዉ ተጨማሪ አምስት አመት መስዋዕት ለማድረግ ወሰንኩ አሉ»

ድሬዳዋ ተወልደዉ፥ ያደጉ፥ ድሬዳዋ የተማሩት የኢሳ ጎሳ አባል ጉሌሕ ዘጠና-ዘጠኝ ነጥብ ላይ ሳይደርሱ መቆማቸዉ ያነጋግር ይሆናል።ከኢትዮጵያ ወይም ከሌሎች የአፍሪቃ ብጤዎቻቸዉ ለመማር ግን በርግጥ አልሰነፉም።ዉጪያዊ አጋጣሚን ፈጥኖ በመጠቀም ደግሞ ከጅቡቲ ታሪክ ብዙ ያወቁ በርግጥም ጁቡቲያን ናቸዉ።

በ1880 ዎቹ አጋማሽ የምስራቅ ትልቅ አካሏ ሶማሊያ ከቅኝ ገዢዎች እጅ የመዉደቋ-ድቀትና የምዕራብ ትልቅ ግማድዋ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢዎችን የመዉጋቷ-ጀግንነት ተቃርኖ፥ ከቅኝ ገዢዎች ሽሚያ ንረት ጋር የመዳመሩ ሐቅ ለዚያች ግዛት ቅኝ የመገዛትዋን መርዶ፥ ሐገር ከመሆንዋ ጥስስ ብስራት ጋር አላጋባት።

በ1884 አፍሪቃን ለመቀራመት ያለመዉ የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች የበርሊን ጉባኤ የዛሬዋን ደቡብ ሶማሊያን ለኢጣሊያ፥ሰሜን ሶማሊያን ለታላቅዋ ብሪታንያ መደልደሉ ከብሪታንያ እና ከቱርክ ጋር ለምትፎካከረዉ ፈረንሳይ ቀይ ባሕር ግርጌ እግር መትከያ የሚያሳጣት ነበር።የብሪታንያ እና የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ለረጅም ዘመን ሶማሊያን የሚገዙትን የአዳልና የአጁራን ሥርወ-መንግሥታት እንደታሰበዉ በቀላሉ መደምሰስ አልቻሉም።

ሡልጣን መሐመድ አብዱላሒ ሐሰን የሚመሩት የሶማሊያ ጦር የብሪታንያ ቅኝ ገዢ ጦርን ደጋግሞ ማሸነፉ ለፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች ትንፋሽ፥ ጊዜ፥ ኦቤክ የተሰኘዉን ትንሽ የባሕር ጠረፍ መሬት ከጎሳ መሪዎች ለመግዢያም ጥሩ አጋጣሚ ነበር።ብሪታንያና ኢጣሊያ የማዕከላዊ ሶማሊያን ገዢዎች ለማስገበር ሲባትሉ፥ርዕሠ-መንበራቸዉ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ብዙ የራቀዉ አፄ ዩሐንስ ደግሞ ሰሜን እና ሰሜን-ምዕራብ ኢትዮጵያን ለመያዝ ከዘመቱት ከኢጣሊያ እና በቱርክ ከሚደገፉት ከሱዳን ገዢዎች ጋር በገጠሙት ጦርነት ተወጥረዉ ነበር።

ለኦቤክ አገረ ገዢነት ተሾሞዉ በ1884 ከፓሪስ ኦቤክ ሊዮንስ ላጋርድ ይሕን አጋጣሚ አለመጠቀም በርግጥ ከጅል የሚያስቆጥራቸዉ ነበር።ላጋርድ በግርግሩ መሐል ከሸዋዉ ንጉስ ከአፄ ሚኒሊክ ጋር በጦር መሳሪ፥ በዲፕሎማሲ ድጋፍም ተወዳጅተዉ፥የኢሳና የአፋር ጎሳ መሪዎችን አባብለዉ ኦቤክ ላይ የታጠረ ግዛታቸዉን መጀመሪያ ወደ ታጁራ አስፋፉ፥ ቀጥለዉ የዛሬዋ የጅቡቲ ከተማን ተቆጣጠሩ።

ጅቡቲ በግር ግር መሐል እንደ ሐገር የተመሠረተችበት አንድመቶ አስረኛ ዓመት ሲዘከር ከግር ግር የማይፀደዉ የአፍሪቃ ቀንድ በሌላ ግር ግር ይታመስ ነበር።ሶማሊያ ቅኝ ገዢዎች ባበጁላት ካርታ መሠረት ዳግም እሁለት ተሰንጥቃ በርስ በርስ ጦርነት ስትተረማመስ፥ ኤርትራም በቅኝ ገዢዎች መስመር መሠረት ከኢትዮጵያ ተነጥላ ነፃ መንግሥት መስርታ ነበር።ሱዳን ቅኝ ገዢዎች የቀበሩላት የዘር ልዩነት ፈንጅ ደቡባዊ ግዛቷ ሲያናጥርባት፥ ከኤርትራ ጋር አታካራ ገጥማ ነበር።

በዚሕ መሐል አዲስ አበባና አሥመራ ላይ ሁለት መንግሥት ያቆሙት ሐይላት ከጦር ሜዳ፥ እስከ መንግሥት መሥረታ የዘለቀ ወዳጅነታቸዉ አብቆቶ የገጠሙት ጦርነት ወትሮም ከትርምስ ያልወጣዉን አካባቢ ይነዉጠዉ ገባ።በትርምስ ነዉጡ መሐል ትንሺቱን ሐገር መግዛት እድሜም ጤናም ለተጫጫናቸዉ ለፕሬዝዳንት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ሲበዛ ከባድ ነበር።አካባቢዉን የሚያደማዉ የድንበር፥ የርስ በርስ ጦርነት፥ ትርምስ፥ የፖለቲካ ምሥቅልቅል ለያኔዉ የጅቡቲ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሳይደግስ አይጣላም ነበር።ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ።

ሽማግሌዉን ፕሬዝዳት ያለብዙ ተቀናቃኝ ተኩ።1999።በግር ግር መሐል የተመሠረተችዉን ሐገር የመሪነት ሥልጣን በግር ግር መሐል የተረከቡት ጉሌሕ ፈረንሳዊዉ የፖለቲካ አዋቂ ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት ፈላጭ ቆራጭ ከመሆናቸዉ እኩል እንደ አዲስ መሪ ብዙ ጠቃሚ አዳዲስ ነገሮችን ከዉነዋልም።

«እስማኤል ዑመር ጉሌሕ ፈላጭ ቆራጭ ግን ሐገርን የሚያሻሽሉ መሪ መሆናቸዉን አሳይተዋል።ከቅድሞዉ ፕሬዝዳት የመጨረሻ ዘመናት ጋር ሲነፃፃር ብዙ ለዉጦች አድርገዋል።የመሠረተ-ልማት መዋቅሮች ገንብተዋል።ጅቡቲን ከዱባይ ጋር አገናኝተዋል።በርካታ ትርጉም ያላቸዉ ምጣኔ ሐብታዊ እርምጃዎችን ወስደዋል።በኤርትራና በኢትዮጵያ ጦርነት የሚታገዘዉ የምጣኔ ሐብት እድገት ብቻ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርስቲዎችንም ገንብተዋል።ሌሎች የማይናቁ ለዉጦችም አሉ»

ሶማሊያ አንድነትዋንም-ነፃነትዋንም ለማወጅ ስትዘጋጅ የያኔዋ የፈረንሳይ ሶማሊ ላንድ ሕዝብ ከሶማሊያ ጋር መቀላቀል-አለመቀላቀሉን ለመወሰን ድምፁን ሰጥቶ ነበር።ፈረንሳይ ባደረገችዉ ከፍተኛ ተፅዕኖና ጫና ሕዝቡ የፈረሳይ ቅኝ ተገዢነቱን መረጠ ተባለ።ከሶማሊያ ጋር ዉሕደትን ደግፈዉ የነበሩት የኢሳ ጎሳ እና መሐመድ ሐርቢን የመሳሰሉ ፖለቲከኞች በአደጋ በሚል ሰበብ ተገደሉ።

በ1970ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ በአብዮታዊ ለዉጥ፥ ነዉጥ ግራ-ቀኝ መላጋቷ፥ ሶማሊያን ኢትዮጵያን ለመዉረር ሲያንጠራራት፥ የሞስኮና የዋሽንግተን መሪዎች አዲስ አበባና የመቃዲሾ ገዢዎችን ከእቅፋቸዉ ለማስገባት መራወጣቸዉ ለትንሺቱ ሥልታዊት ሐገር ለዛሬ እሷነቷ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።የፈረንሳዮች ቅኝ አገዛዝ ሲያበቃ የየራሳቸዉ ለማድረግ የሚመኙት ሁለቱ ትላልቅ ጎረቤቶችዋ በአለም ትላልቅ አጋሮቻቸዉ ደጋፍ ከጦርነት ሲዘፈቁ ነፃ ወጣች።1977።

DJIBOUTI TERROR ENDURING FREEDOM p178
የዓለም ዓቀፉ ጦር-ጅቡቲምስል AP

በሃያኛዉ አመት ኢትዮጵያና ኤርትራ የገጠሙት ጦርነት ወደብ አልባዋን ኢትዮጵያን የጅቡቲ ወደብ ጥገኛ ሲያደርጋት አዲሱን የሐገሪቱን መሪ ገደኛ አሰኝቶ ነበር።በሁለት ሺዎቹ መጀመሪያ የታወጀዉ አለም አቀፍ ፀረ-ሽብር ዘመቻ፥ በተለይ በሁለት ሺሕ ሰወስት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ኢራቅን ማስወረራቸዉ ለገደኛዉ ፕሬዝዳት ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

ከፈረንሳይ ዉጪ ትልቁን የፈረንሳይ ጦር ሠፈር የምታስተናግደዉ ጅቡቲ፥ አፍሪቃ ዉስጥ ትልቁን የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠፈርም አስተናጋጅ ሆነች።ወዲያዉ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የሚዋጋዉ አለም አቀፍ ጦርንም ታስናግድ ገባች።ትንሺቱን ሥልታዊ ሐገር ኢትዮጵያና ዱባይ ለወደብ፥ ትላልቁ አለም ለጦር ሠፈርነት የሚያደርገዉ ሽሚያ በደራበት በ2003 በተደረገዉ የምክር ቤት ምርጫ ብልጣ ብልጡ ፕሬዝዳት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አሽቀንጥረዉ ምክር ቤቱን መቶ በመቶ ተቆጣጠሩት።

«ሌላዉ የጅቡቲ ጎረቤቶችን ጨምሮ ብዙ የአፍሪቃ ሐገራት በመፈፀሙ በጣም የሚያሳስበዉ ጉዳይ ተቃዋሚዎች ለበጎም ሆነ ለመጥፎ ከምርጫ የሚገኝ ነገር የለም የሚል ሥጋት ማሳደራቸዉ ነዉ።በዚህም ምክንያት ከዚሕ ቀደም በተደረጉት ፕሬዝዳንታዊና ምክር ቤታዊ ምርጫዎች አልተካፈሉም።እንዲሕ አይነቱ ዉሳኔ በየትኛዉም ሐገር ቢሆን አሳሳቢ ነዉ።ምክንያቱም በጅቡቲ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ክፍል በምክር ቤቱ አልተወከለም።»

በ2005 መግቢያ የሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አልበሽር እና የያኔዉ የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድን መሪ ጆን ጋራግ ደቡብ ሱዳንን ዛሬ ከነፃ ሐገርነት ጠረፍ ያደረሰዉን ስምምነት ናይሮቢ ዉስጥ መፈረመችዉ እንደ ደመቀ ሚያዚያ ባተ።አፍሪቃ ዓለም፥ ሱዳን፥ ሶማሊያ፥ ኢራቅ ሲል እስማኤል ዑመር ጉሌሕ ብቻቸዉን ተዳድረዉ አሸነፉ።ኢትዮጵያ ዉስጥ ግንቦት የተደረገዉ ምርጫ ዉጤትና ደም አፋሳሽ መዘዙ የጉሌሕ ተቃዋሚዎችን ጩኸት ሰሚ ለማሳጣት በቂ ነበር።

ዘንድሮ የካቲት የአለም ትኩረት ከሰሜን አፍሪቃ መካከለኛዉ ምሥራቅ ሲፈራረቅ ደግሞ ጉሌሕ የትንሺቱን ሐገር ትልቅ የተቃዉሞ ሠልፍ ብዙዎች ብዙ ሳይሰሙ ባፍታ ደፈለቁት።የአለም ዘዋሪዎች ጦር፥ ጡንቻ ሊቢያ ኮትዲቯር ላይ እንተሰነዘረ፥ የዓለም አይን ጆሮ ሰሜን እና ምዕራብ አፍሪቃ፥ የመንና ሶሪያ ላይ እንዳነጣጠረ በግር ግሩ መሐል ጉሌሕ ሕገመንግሥት አጥፈዉ ሕጋዊ መሪ ሆኑ።የግር ግር ዉጤት ሐገር፥ የግር ግር መሐል መሪ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ