1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን እና ዓለም አቀፍ ባህላዊ ትውውቅ መርሀ ግብርዋ

ረቡዕ፣ የካቲት 18 2001

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ «ዓለም አቀፍ ባህላዊ ትውውቅ» የተሰኘ አዲስ የነጻ አገልግሎት መስጫ መርሀ ግብር በቅርቡ ይጀምራል።

https://p.dw.com/p/H16c
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርምስል picture-alliance / dpa

በዚሁ መርሀ ግብር መሰረት፡ ወጣት ጀርመናውያን በፈቃደኝነት ለስድስት ወር ወይም ለአንድ ዓመት ወደ አፍሪቃ፡ እስያ፡ ላቲን አሜሪካ እንዲሁም ወደ መካከለኛና ወደ ደቡብ ምስራቅ አውሮጳ በመሄድ ሊሰሩና ተሞክሮ ሊሰበስቡ ይችላሉ። ወጣቶቹ በዚሁ አገልግሎታቸው ወቅት፡ የተለያዩ ተግባራትን፡ ለምሳሌ በዩክሬይን መዲና፡ በኪየቭ የሚገኙ የጀርመን ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በቤት ስራቸው ማገዝ እና በሪዮ ደ ዣንየሮ ብራዚል ባለው የጀርመናውያን አካዳሚ ልውውጥ ድርጅት ውስጥ ዓበይት ዝግጅቶችን ማደራጀት የመሳሰሉ ስራዎችን ሊያከናውኑ ይችላሉ። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያነቃቃው አዲሱ «ዓለም አቀፍ ባህላዊ ትውውቅ መርሀ ግብር» ምን ይመስላል?

በአስራ ስምንት እና በሀያ ስድስት ዓመት መካከል የሚገኙ ወጣቶች በፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጡበት ጊዜ ርዝመት ራሱ፡ የሚያከናውኑት ተግባር ከሌሎች የልምምድ ስራዎች የተለየ መሆኑን ይጠቁማል። በባህልና በማሰልጠኑ ስራ ለመሰማራት የሚፈልጉ ወጣቶች፡ የጊዜውን ርዝመት፡ ማለትም፡ ስድስት ወይም አስራ ሁለት ወራት መሆን አለመሆኑን አስቀድመው መምረጥ አለባቸው። በዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ውስጥ ለመሰማራት የሚፈልጉ ሁሉም አንድም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ሰርቲፊኬት ወይም በአንድ የሙያ ስልጠና ትምህርት የተመረቁ መሆን ይኖርባቸዋል። ጥቂቱ የእንግሊዝኛ ወይም የሌላ ቋንቋ ዕውቀት ቢኖራቸውም አይጠላም። ይሁንና፡ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ጌርኖት ኤርለር እንደገለጹት፡ መርሀ ግብሩ የሚካሂድባቸው ሀገሮች ብዙ እንደመሆናቸው መጠን ወጣቶቹ የነዚህን ሀገሮች ሁሉ ቋንቋ የግድ መቻል የለባቸውም።

« መርሀ ግብሩ የሚካሄድባቸውን ሀገሮች ቋንቋዎችን በጠቅላላ ከትምህርት ቤት ወይም ከስልጣና ቦታቸው ተምረው እንዲመጡ አንጠብቅም። ይህ በፍጹም የሚጠበቅ አይደለም። »

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ በዚሁ ስራው ላይ የተመ የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኔስኮ ኮሚሽንን ከመሳሰሉ አጋር ድርጅቶች እና በርሱ ስር ከሚሰሩ ከባህል ድርጅት ገተ፡ ከጀርመናውያን አካዳሚ ልውውጥ ድርጅት፡ ከጀርመናውያኑ የስነ ቅርስ ምርምር ተቋም ትብብር ያገኛል። እነዚህን በመሳሰሉ ልዩ ፕሮዤዎችም ላይ ነጻው አገልግሎት ከሚካሄድባቸው የተለያዩት ሀገሮችና ከህዝቦቻቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚደረግ የመርሀ ግብሩ ፕሬዚደንት ሀንስ ዮአኺም ጌርከ አስታውቀዋል።

« ትኩረታችን ያረፈባቸው ሁለት ጉዳዮች አሉ። ሰዎችን በብዛት በምናገኝበት፡ ትልቅ ስብሰባዎች እና ዝግጅቶች በሚካሄዱባቸው ቤተ መጽሀፍት ውስጥ እንሰራለን። ከህዝብ ጋር የመገናኘቱ ዕድል ከፍተኛ የሆነበትን ቦታ ነው የምንመርጠው። ወይም በሶርያ የስነ ቅርስ ቁፋሮ ስራ በሚካሄድበት ጊዜ ከሶርያውያኑ የስነ ቅርስ ቆፋሪዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ዐረብኛ ቋንቋ ሊሞክሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ነው፡ በጀርመናውያኑ የስነ ቅርስ ምርምር ተቋም ውስጥ መስራትን አማላይ የሚያደረገው። »

ዓለም አቀፍ የባህል ትውውቅ መርሀ ግብርን ባነቃቃው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መርሀ ግብር፡ በየወሩ ለቤትና ለምግብ ሁለት መቶ ዩሮ፡ እንዲሁም፡ አንድ መቶ ሀምሳ ዩሮ የኪስ ገንዘብ በምኘት በተለይ ወደ አዳጊዎቹ፡ እንዲሁም፡ ወደ መካከለኛና ደቡብ ምስራቅ አውሮጳ የሚሰማሩት ወጣቶች ወደዚሁ አገልግሎት ለሚገቡበት ድርጊት የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ጌርኖት ኤርለር እንዳስረዱት፡ የሌሎች ሀገሮችን ባህል የማወቁ ፍላጎት፡ እንዲሁም፡ ርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኖ መገኘትም አስፈላጊው ይሆናል።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በዚሁ አዲስ ባነቃቃው ዓለም አቀፍ የባህል ትውውቅ መርሀ ግብር ለመሳተፍ የሚፈልጉ ማመልከቻ እስከመቼ ማስገባት እንደሚችሉ ሚንስቴሩ በኢንተርኔት ባዘጋጀው « ዓለም አቀፍ የባህል ትውውቅ መርሀ ግብር » በተሰኘው ድረ ገጹ አስቀምጦዋል። በሚንስቴሩ ዘገባ መሰረት፡ የመጀመሪያው የወጣቶች ቡድን የፊታችን መስከረም ወር ይንቀሳቀሳል። ከአንድ ዓመት በፊት የጀርመን የኤኮኖሚ ተራድዖ ሚንስቴር ባነቃቃውና የተሳካ ባለው ተመሳሳይ መርሀ ግብር ለሁለት ሺህ ሶስት መቶ ቦታዎች አስር ሺህ ማመልከቻዎች ቀርበውለት እንደነበር የሚታወስ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን ዓለም አቀፍ የባህል ትውውቅን በመሳሰሉ መርሀ ግብሮች ውስጥ ወጣቶቹ ለአስራ ሁለት ወራት የሚሰሩበት ድርጊት እንደ ሲቭል አገልግሎት ሊቆጠርላቸው የሚችልበት ሁኔታም ወጣቶቹን የሚስብ አማላይ ነጥብ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ዘገባ አስታውቋል።

Nehls, Thomas

aa/hm