1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በ76 ዓመታቸው አረፉ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 19 2011

ኢትዮጵያን ለሰባት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዛሬ ጠዋት በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በ76 ዓመታቸው አረፉ። ዶ/ር ነጋሶ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በአንድ የጀርመን ሆስፒታል ውስጥ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነበር።

https://p.dw.com/p/3HZ9l
Äthiopien Negaso Gidada
ምስል DW/Y.G. Egziabhare

ኢትዮጵያን ለሰባት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዛሬ ጠዋት በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በ76 ዓመታቸው አረፉ። ዶ/ር ነጋሶ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በአንድ የጀርመን ሆስፒታል ውስጥ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነበር። በጀርመን ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ ያረፉት በፍራንክፈርት ከተማ ዛክሰን ሐውስ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ ነው።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሐሙስ ዕለት ወደ ፍራንክፈርት ኡኒቨርስቴት ክሊኒክ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ የጤና ሁኔታቸው በመባባሱ ለድንገተኛ ህክምና ወደ ዛክሰን ሀውስ ሆስፒታል ዛሬ ጠዋት መወሰዳቸውን ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ደምቢዶሎ በተባለ ቦታ ጳጉሜ 3 ቀን፤ 1935 ዓ.ም የተወለዱት ዶ/ር ነጋሶ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ከነበራቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ።

Äthiopien Negaso Gidada
ምስል DW/Y.G. Egziabhare

አምስት አስርት አመታት ገደማ በዘለቀ የፖለቲካ ሕይወታቸው ኢትዮጵያን በፕሬዝዳትነት ከመምራት ባሻገር የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራር ሆነው አገልግለዋል። ዶ/ር ነጋሶ አሁን በተግባር ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽንንም በሊቀ-መንበርነት መርተዋል። በሽግግር መንግሥት ወቅትም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ እና በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።

ከጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ከተቃቃሩ በኋላ ሰኔ 15 ቀን፤ 1993 ዓ.ም. ከኦሕዴድ እና ኢሕአዴግ አባልነታቸው የተሰናበቱት ዶ/ር ነጋሶ በግንቦት 1997 ዓ.ም. በተደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ በትውልድ ቀያቸው ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን አሸንፈዋል። ዶ/ር ነጋሶ ባለትዳር እና የልጆች አባት ነበሩ።

ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ