1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳርፉር፣ የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔና የሱዳን ተቃዉሞ

ዓርብ፣ ነሐሴ 26 1998

ወትሮም ሐሳቡን የቅኝ ገዢዎች ሴራ በማለት ያጣጣለዉ የሱዳን መግሥት ዉሳኔዉን «ሕገ-ወጥ» ብሎታል።ሱዳን እስካልፈቀደች ድረስ ደግሞ ሠራዊት ማዝመት-ማስፈር አይቻልም።

https://p.dw.com/p/E0iD
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትምስል AP



የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ምዕራባዊ ሱዳን ግዛት ዳርፉር እንዲዘምት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያሳለፈዉን ዉሳኔ ሱዳን ዉድቅ አደረገችዉ።ምክር ቤቱ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ያረቀቁትን የዉሳኔ ሐሳብ ትናንት ያፀደቀዉ በአስራ-ሁለት የድጋፍ በሰወስት ድምፀ-ተአቅቦ ነዉ።ድምፃቸዉን ያቀቡት የምክር ቤቱ አባላት ሩሲያ፣ ቻይናና ቀጠር የሱዳን መንግሥት እስኪቀበለዉ ድረስ ሐሳቡ መፅደቁን አልፈቀዱትም።አለም አቀፍ ሠራዊት ዳርፉር ይሠፈር የሚለዉን ሐሳብ ስትቃወም የነበረችዉ ሱዳን የምክር ቤቱን ዉሳኔ ሕገ-ወጥ ብላዋለች። ማርቲና በትለር ከኒዮርክ ያስተላለፈችዉን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አሰባስቦታል።


የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ትናንት ባፀደቀዉ ዉሳኔ መሠረት ወደፊት ዳርፉር የሚዘምተዉ ሠራዊት እስካሁን እዚያ የሠፈረዉን የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ይተካል።ወይም እዝ-አስተዳደሩን ከአፍሪቃ ሕብረት ተረክቦ ይመራል።የዉሳኔ ሐሳቡ-አርቃቂ አፅዳቂዎች እንደሚሉት ሰባት ሺሕ አባላት ያሉት የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት የግዛቲቱን ሠላም ማስከበር፣ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት መከላከል አልቻለም።ይሕን የማድረግ ሥልጣኑም፣ አቅሙም፣ መሳሪያ-ገንዘቡም የለዉም።

ከእንግዲሕ የሚዘምተዉ ሠራዊት በቁጥር ከአፍሪቃ ሕብረቱ ሠራዊት በአስር-ሺሕ በልጦ አስራ-አራት ሺሕ ወታደር፣ ሰወስት-ሺሕ ሰወስት መቶ ፖሊሶች በጥቅሉ አስራ-ሰባት ሺሕ ሰወስት መቶ አባላት ይኖሩታል።ሱዳን ከአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ሌላ የዉጪ ሰራዊት ይስፈር የሚለዉን ሐሳብ ገና ከጅምሩ ሉአላዊነቷን እንደመዳፈር አድርጋ ነዉ-ያየችዉ።ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አል-በሽር ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታኒያ ያረቀቁት ሐሳብ ትናንት ለዉሳኔ ከመቅረቡ በፊት በዋዜማዉ ሮብ ረቂቁን በመቃወም የካርቱም አደባባይን ላጨናነቀ ሕዝባቸዉ እንደነገሩት ዳርፉርን አንድም የዉጪ ወታደር አይረግጣትም።

የአልበሽር ዛቻ፣ የሕዝባቸዉ ተቃዉሞ፣የሌሎች ቅሬታም ረቂቁን ከመፅደቅ አላገደዉም።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትሱ አምባሳደር ጆን ቦልተን እንዳሉት ደግሞ የረቂቁ በመፅደቅ አለም ሠላም ጠቃሚ ነዉ።

«እንደሚታወቀዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በጣም ጠቃሚ የሆነዉን ዉሳኔ በማፅደቁ እጅግ ነዉ-ደስ ያለን።ምክንያቱም የረቂቁ መፅደቅ ዳርፉር ግዛት ባለዉ ሁኔታ የአለም ሠላምና ፀጥታ የተጋረጠበትን ሥጋት የሚያቃልል በመሆኑ።ከእንግዲሕ ወቅቱ ዉሳኔዉን ገቢር የማድረጊያ ነዉ።የምናተኩረዉም በዚሕ ላይ ነዉ።»


የዳርፉር አማፂያንና በሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት ይደገፋሉ የሚባሉት የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎች እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በሁለት ሺሕ ሰወስት ዉጊያ ከጀመሩ ወዲሕ ሁለት መቶ ሺሕ ያሕል የግዛቲቱ ነዋሪ አንድም በቀጥታ በጦርነቱ፣ አለያም ጦርነቱ ባስከተለዉ በሽታና ረሐብ ሞቷል።ሁለት ሚሊዮን ደግሞ ተሰዷል።ወይም ተፈናቅሏል።ግጭት ጦርነቱን ማስቆም በግዛቱ ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉን መከራ መግታት መሆኑን ቢያንስ በይፋ የማይቀበል ወገን የለም።

የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ትናንት ያሳለፈዉ ዉሳኔም ሁሉም የሚያምንበትን ሐሳብ ገቢር ለማድረግ ያለመ መሆኑ አላነጋገረም።ዉሳኔዉ የተረቀቀና የፀደቀዉ ግን ሁሉንም ወገን በሚያግባባ መልኩ አለመሆኑ ነዉ-ክፋቱ።ቻይና፣ ሩሲያና ቀጠር ድምፃቸዉን ያቀቡት የቻይናዉ አምባሳደር ዋንግ ጉዋንግያ እንዳሉት ልዩነቱ እስኪወገድ ጊዜ ያስፈልጋል በሚል ምክንያትም ነዉ።


«በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት መካካል ልዩነት አለ።ከሱዳን መንግሥት ጋርም ልዩነት እንዳለ ይገባኛል።እና ጊዜ ያስፈልገናል።ሥለዚሕ እንደማምነዉ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሐይል ሐላፊነቱን መረከብ አለበን በሚለዉ ሐሳብ ቻይና እንደሁሉም ሐገራት ትስማማለች።በጊዜዉ፣ ጉዳዩ በተያዘበት ሁኔታ ላይ ግን-አዎ የተለየ አመለካከት ነዉ-ያለን።»

ዳርፉር የሚዘምተዉ ሠራዊት ሠላም ማስከበር ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ ሰባት መሰረት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት የመካለል ሥልጣንና ሐላፊነትም ይኖረዋል።ገቢር ይሆናል ወይ ነዉ-ጥያቄዉ።ወትሮም ሐሳቡን የቅኝ ገዢዎች ሴራ በማለት ያጣጣለዉ የሱዳን መግሥት ዉሳኔዉን «ሕገ-ወጥ» ብሎታል።ሱዳን እስካልፈቀደች ድረስ ደግሞ ሠራዊት ማዝመት-ማስፈር አይቻልም።

የወቅቱን የፀጥታዉ ምክር ቤት ተዘዋዋሪ የፕሬዝዳትነት ሥልጣን የያዙት የጋናዉ አምባሳደር ናና ኤፋሕ-አፔንታግ ቀጣዩ ወደፊት «ይታሰብበታል» ከማለት ሌላ መልስ አልነበራቸዉም።