1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳርፉርና የበጎ ፈቃድ መግለጫ

ቅዳሜ፣ የካቲት 14 2001

1-የሱዳን መንግስትና በዳርፉር የሚንቀሳቀሰው የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ በምህጻሩ ጄም ተወካዮች አጠቃላይ የሰላም ውል ለመድረስ የሚያስችላቸውን መንገድ የሚያመቻች የበጎ ፈቃድ መግለጫ ስምምነት ባለፈው ማክሰኞ ተፈራረሙ። -------------

https://p.dw.com/p/GyJE
ምስል picture alliance/dpa

2- የአልጀሪያ ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ለሶስተኛ ጊዜ ለዚሁ ስልጣን ለመወዳደር አቅደዋል።

------------------------

የሱዳን መንግስትና በዳርፉር ከሚንቀሳቀሱት ያማጽያን ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ በምህጻሩ የጄም ተወካዮች አጠቃላይ የሰላም ውል ለመፈረም የሚያስችላቸውን መንገድ የሚያመቻች የበጎ ፈቃድ መግለጫ ስምምነት ባለፈው ማክሰኞ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። በዳርፉር ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ የቀጠለውንና የሶስት መቶ ሺህ ሲቭል ህዝብን ህይወት ያጠፋውን እና ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ያፈናቀለውን ውዝግብ ለማብቃት የሚረዳ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ለስምንት ቀናት የተካሄደውን ውይይት፡ ከተመድ፡ ከአፍሪቃ ህብረትና ከዐረቡ ሊጋ ጋር ባንድነት የሸመገለችው የቓታር ጠቅላይ ሚንስትር ሼክ ሀማድ ቢን ጃሰም አል ታኒ ገልጸዋል።

« ይህ የተቀደሰ ትልቅ ርምጃ ነው፤ እና ጠቅላላ ህዝቡን የሚያሳትፍ የተሻለ ርምጃ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ይህ የሚቻል ነው። »

የሱዳን መንግስትና በዳርፉር የሚንቀሳቀሰው የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ በምህጻሩ ጄም ተወካዮች ካለፈው 2007 ዓም ወዲህ ተገናኝተው ሲወያዩ ያለፈው ሳምንቱ የመጀመሪያ ነው።

እንደሚታወሰው፡ ጄም እአአ በ 2006 ዓም በአቡጃ ናይጀሪያ በሱዳን መንግስትና በሚኒ ሚናዊ በተመራው በአንዱ የሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄ የኤስ ኤል ኤም ከፊል መካከል የተደረሰውንና ያን ያህል ያልሰመረውን የሰላም ውል ለመፈረም ፈቃደኛ ሳይሆን ነበር የቀረው። በአብደል ዋህድ ኑር የተመራው ሌላው የኤስ ኤል ኤም ከፊል የአቡዣውን ውል በመቃወም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከፓርቲው ተገንጥሎ ከማንኛውም የሰላም ጥረት ርቆዋል። በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶርያ የሚገኙት የዓለም አቀፉ የጸጥታ ጥናት ተቋም በምህጻሩ የ አይ ኤስ ኤስ ተንታኝ ፓውላ ሮክ የሱዳን መንግስትና የጄም ተወካዮች ከጥቂት ጊዜ በፊት የተፈራረሙት የበጎ ፈቃድ መግለጫ ስምምነት በዳርፉር ዘላቂ ሰላም ለሚወርድበት ድርጊት አዎንታዊ አስተዋጽዖ ሊያበረክት መቻሉን ገልጸዋል።

« በቓታር የተደረሰው ስምምነት ትልቅ ትርጓሜ የያዘ ነው። በተለይ በዳርፉር ጄም በዳርፉር ከሚንቀሳቀሱት ያማጽያን ቡድኖች መካከል በሚገባ የተደራጀውና የተዋቀረው፡ እንዲሁም፡ በሚገባ የታጠቀው መሆኑ ሲታሰብ። እና ማንኛውም የሰላም ሂደት ጄምን ማጠቃለሉ በጣም ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ፡ ለዳርፉር የሚደረስ የትኛውም የሰላም ሂደት፡ ውዝግቡ የሚመለከታቸውን ያማጽያን ቡድኖችን ሁሉ ማሳተፍ ይኖርበታል፤ ምንም እንኳን፡ ይህ አሁን የተደረሰው ስምምነት በዳርፉር ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት የሚበጅ የመጀመሪያው ርምጃ ቢሆንም። »

ባለፈው ማክሰኞ ባበቃው ውይይት ላይ ሁለቱ ወገኖች የሰላሙ ድርድር እስከሚጀመርበት ጊዜ ድረስ እስረኞች ለመለዋወጥ በመሰረቱ ፈቃደኝነታቸውን እንዳረጋገጡ በውይይቱ የተሳተፉት የጄም መሪ ኻሊል ኢብራሂም አስታውቀዋል።

« የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ግልጽ ነው። እስረኞችን ለመለዋወጥ ነው። ይህንን ዓላማችንንም በሼኽ ሀማድ ርዳታ ማሳካታችን አይቀርም። »

ይህ ዓይነቱ ርምጃ ተቀናቃኞቹን ወገኖችን ለማቀራረብ እንደሚረዳ በፕሪቶርያ የዓለም አቀፍ ጸጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ፓውላ ሮክ ቢያመለክቱም፡ ጠቅላላ የዳርፉር ዓማጽያን ቡድኖች ካላሳተፈ በስተቀር ትርጓሜ አልባ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

« የሱዳን መንግስትና ጄም እስረኞችን ለመለዋወጥ በመሰረቱ የተስማሙበት ሁኔታ በሁለቱ መካከል መተማመን የሚፈጥር ማዕከላይ ነጥቦ ሆኖ ታይቶዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የሽምግልናውን ሂደት የጀመሩት ወገኖች ሁሉ የተለያዩትን የዳርፉር ዓማጽያን ቡድኖች በጠቅላላ ማዋሀድ በመጣር ላይ ናቸው። በዳርፉርም የተኩስ አቁም ደምብ እንዲደረስ ከተፈለገ ያማጽያኑ ቡድኖች በአንድ ድምጽ መናገር ይኖርባቸዋል። »

ፓውላ ሮክ እንደሚያሳዉት፡ የ ኤስ ፒ ኤል ኤም እና የሱዳን መንግስት እአአ በ 2005 ዓም በናይቫሻ ኬንያ የተፈራረሙት አጠቃላይ የሰላም ውል በሰሜናዊ እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ከፊሎች ይንቀሳቀሱ በነበሩ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ብቻ የተደረሰ በመሆኑ በሌሎቹ የሀገሪቱ ከፊሎች ለቀጠሉት ውዝግቦች መፍትሄ ሳያስገኝ ነበር የቀረው። እና ወደፊት ለዳርፉር ሰላም ለማውረድ በሚደረገው ድርድርም ላይ ተመሳሳይ ስህተት እንደማይፈጸም፡ እንዲሁም፡ በዳርፉር ጠንካራውና በሚገባ የታጠቀው ያማጽያኑ የፍትህና የእኩልነት ንቅናቄ የፈረመው ስምምነት ሌሎች ያካባቢው ህዝብ ከፊሎችን የሚወክሉትን ያማጽያን ቡድኖች ከድርድሩ የማያገል እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።

የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ ልዊ ሞሬኒ ኦካምፖ የጦርና በስብዕና አንጻር ወንጀል ፈጽመዋል ባሉዋቸው በሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን አል ቤሺር ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ባስገቡት ማመልከቻ መሰረት ፍርድ ቤት ማዘዣውን ቢያወጣ ለዳርፉር ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት የሚደረገውን ጥረት እንደሚጎዳ ብዙዎች የሚያሰሙትን ስጋት አይጋሩትም።

« የተመድ፡ የዐረቡ ሊግና የአውሮጳ ህብረት ድርድሩን እንደመደገፋቸውና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ርዳታ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን፡ የሰላሙ ጥረት የሚቀጥልበት ድርጊት አስፈላጊ ነው። ፍርድ ቤቱ በፕሬዚደንት በሺር ላይ የእስሩን ማዘዣ ቢያወጣም፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ሸምጋዮቹ ከሱዳን መንግስት ጋር መደራደራቸውን አያቋርጡም። የሰላሙ ሂደትም በዚሁ መልኩ ይቀጥላል። »

በቓታር ዶሀ ለወደፊቱ ድርድር መመሪያዎችን ባስቀመጠው ስምምነት መሰረት፡ በቅርቡ ይጀመራል የሚባለው የሰላም ውይይት ይመክርባቸዋል ተብለው የሚጠበቁትን ዋነኞቹን ጉዳዮች የፕሪቶርያው ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጥበቃ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ፓውላ ሮክ እንደሚከተለው ዘርዝረዋቸዋል። « የስልጣን መጋራቱ ጥያቄ፡ ያማጽያኑ ቡድኖች በ 2003 ዓም በሱዳን መንግስት አንጻር ትግል የጀመሩበት ምክንያት፡ ማለትም የዳርፉር ህዝብ ይደርስበታል የሚሉት ፖለቲካዊ መገለል፡ ያካባቢ ልማት መጓደል፡ አካራካሪው የልማት ባለቤትነት ጥያቄ፡ ተፈናቃዮችም ወደቀዬአቸው ተመልሰው የሚሰፍሩበት፡ ያካባቢው ሀብት ክፍፍል ጉዳዮች፡ እንዲሁም፡ የተኩስ አቁም ደምብ የሚደረስበትና ላካባቢው ጸጥታ ጥበቃ ወሳኝ የሆነው የተለያዩት ያማጽያን ቡድኖችና በመንግስቱ ይረዳሉ የሚባሉት ኦአባውያኑ የዣንዣዌድ ተዋጊዎች ሁሉም የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የሚፈቱብ ጉዳይ ይመከርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። »

« የስልጣን መጋራቱ ጥያቄ፡ ያማጽያኑ ቡድኖች በ 2003 ዓም በሱዳን መንግስት አንጻር ትግል የጀመሩበት ምክንያት፡ ማለትም የዳርፉር ህዝብ ይደርስበታል የሚሉት ፖለቲካዊ መገለል፡ ያካባቢ ልማት መጓደል፡ አካራካሪው የልማት ባለቤትነት ጥያቄ፡ ተፈናቃዮችም ወደቀዬአቸው ተመልሰው የሚሰፍሩበት፡ ያካባቢው ሀብት ክፍፍል ጉዳዮች፡ እንዲሁም፡ የተኩስ አቁም ደምብ የሚደረስበትና ላካባቢው ጸጥታ ጥበቃ ወሳኝ የሆነው የተለያዩት ያማጽያን ቡድኖችና በመንግስቱ ይረዳሉ የሚባሉት ኦአባውያኑ የዣንዣዌድ ተዋጊዎች ሁሉም የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የሚፈቱብት ጉዳይ ይመከርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። »

ይህ በዚህ እንዳለ በሱዳን መንግስትና በጄም ተወካዮች መካከል የተፈረመው የበጎ ፈቃዱ መግለጫ የዳርፉርን ሲቭል ህዝብ ስቃይ የሚያበቃበትን ተስፋ በፈነጠቀበት ባሁኑ ጊዜ በዚያው በዳርፉር ውጊያው ቀጥሎ የሱዳን መንግስት ያማጽያኑን ሰፈሮች መደብደቡን ያጠናከረበት ድርጊት ባካባቢው ሰላም ለማውረድ ያለውን ፍላጎት አጠያያቂ አድርጎታል።

-----

በሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር አልጀርያ እአአ የፊታችን ሚያዝያ ዘጠኝ 2009 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። በዚሁ ምርጫ ላይ ሀገሪቱን እአአ ከ 1999 ዓም ወዲህ በመምራት ላይ የሚገኙት ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡቴፍሊካ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል። በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር የስልጣን ዘመን በሁለት የአምስት ዓመት ስልጣን የተገደበ ነው። በዚህም የተነሳ የአልጀርያ ምክር ቤት ባለፈው ህዳር ወር ሁለት ሶስተኛውን የተወካይ እንደራሴዎችን ድጋፍ በማግኘት በህገ መንግስቱ ላይ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በፕሬዚደንቱ ስልጣን ላይ አርፎ የነበረውን የሁለት የስልጣን ዘመን ገደብን በማንሳት ርዕሰ ብሄር ቡቴፍሊካ ለሶስተኛ ጊዜ ለዚሁ ከፍተኛ ስልጣን እንዲወዳደሩ መንገዱን አመቻችቶዋል። ይኸው የምክር ቤቱ ርምጃ እና የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ውሳኔ በተቃውሞ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በብዙው የሀገሪቱ ህዝብ ዘንድ ቅሬታ ማስከተሉን ሂደቶችን በቅርብ የተከታተሉት ከብዙ ጊዜ ወዲህ በአልጀርያ የሚኖሩትና ለተለያዩ ጀርመንኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙሀን የሰሩት ተንታኝ ክላውዲያ አልትማን ገልጸዋል።

« የአልጀርያ ህዝብ ፕሬዚደንቱ እንደብዙዎቹ ዐረባውያንና አፍሪቃውያን አምባገነኖች አሁን ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ባለመፈለጋቸው የተደሰተ አይመስለኝም። እንደሚታወሰው እአአ በ 1999 ዓም የብዙሀኑን ድምጽ አግኝተው የተመረጡት ቡቴፍሊካ በተለይ በሀገሪቱ ተስፋፍቶ የነበረውን የሙስሊም አሸባሪዎችን ጥቃት በከፊል መቆጣጠር በመቻላቸው በህዝብ ዘንድ ሰፊ ተወዳጅነት አግኝተው ነበር። »

በጦር ኋይሉ ይደገፍ የነበረው የአልጀርያ መንግስት እአአ በ 1992 ዓም በሀገሪቱ የተካሄደውን እና የሙስሊሞቹ ፓርቲ ሊያሸንፍ የነበረበትን ምክር ቤታዊ ምርጫ ከሰረዘ ወዲህ ለበርካታ ዓመታት የቀጠለውን ደም አፋሳሽ የርስበርስ ጦርነት እንዲያበቃና በሀገሪቱ መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ ለተጫወቱት ሰፊ ሚና በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ ትልቅ አመለካከት ማትረፋቸው አትርፈዋል። በዚሁ አክራሪ ሙስሊሞች በጦር ኃይሉና በሺብሉ ህዝብ ላይ በጣሉዋቸው ጥቃቶች ወደ አንድ መቶ ሀምሳ ሺህ ሰው ነበር የተገደለው።

የሶሻሊስት ኃይላት ግንባርን የመሳሰሉ ትልቆቹ የአልጀርያ መንግስት ተቃውሞ ፓርቲዎች ምክር ቤቱ በፕሬዚደንቱ ስልጣን ዘመን ላይ የነበረውን የሁለት ዘመን ገደብ ያነሳበትን ውሳኔ የተሳሳተ ነው በሚል ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ ለመራቅ ወስነዋል፣ ለዚሁ ከፍተኛ የሀገሪቱ ስልጣን ለመወዳደር ዕቅድ ካላቸው አስራ ስምንት መካከል እስካሁን የአልጀርያ ብሄራዊ ግንባር መሪ የሆኑት ሙሳ ቱዋቲ ብቻ ናቸው በተወዳዳሪት መቅረብ የሚያስችላቸውን የህዝብ ፊርማ ማሰባሰብ የቻሉት። ሌሎች የሁለት አነስተኛ ፓርቲዎች ዕጩዎችም በምርጫው ሊሳተፉ እንደሚችሉ ቢገመትም አንዳቸውም ለፕሬዚደንት ቡቴፍሊካ ጠንካራ ተፎካካሪ አለመሆናቸው ተገምቶዋል። እና ቡቴፍሊካ በአንጻራቸው ጠንካራ ተፎካካሪ በማይሳተፍበት ቀጣዩ ምርጫ ተወዳድረው ማሸነፋቸው እንደማይቀር ጋዜጠኛዋ ክላውዲያ አልትማን ቢያመለክቱም፡ ብዙ መራጮች ላይሳተፉ የሚችሉበትት የምርጫ ውጤት በአልጀርያውያን ዘንድ ያን ያህል ተዓማኒነት ማግኘቱ አጠያይቀዋል።

« ምን ያህል ሰው ይደግፋቸዋል። በምርጫው የሚሳተፈው መራጭ ህዝብ ቁጥር ምን ያህል ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ። እንዲያውም የአልጀርያ አመራር ለምርጫው ብዙ ህዝብ ላይወጣ ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ነው የሚሰማው። መንግስት በመስጊዶች ማንኛውንም ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ቢከለክልም፡ የሀገሪቱ የሀይማኖት ጉዳዮች ተመልካች ሚንስትር፡ በአንድ መስጊድ ተገኝተው ኢማሞቹ ህዝቡን ወደምርጫ ጣቢያዎች እንዲሄድ እንዲገፋፉ እስከመጠየቅ መድረሳቸው ተሰምቶዋል። ይህ የሚያሳየው በምርጫው ብዙ ህዝብ ላይወጣ እንደሚችል ነው። ዴሞክራሲያዊ እና የሙስሊሞቹ ፓርቲዎች በምርጫው እንደማይሳተፉ ገልጸዋል። እርግጥ ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡቴፍሊካ አልጀሪያን ወደ ዴሞክራሲያዊው ጎዳና እንደሚያመሩ ቢናገሩም፡ የተቃውሞው ወገን አሁን የወሰደው ውሳኔ ይህ የርዕሰ ብሄሩ አባባል ተግባራዊ አለመሆኑን ነው ያሳየው። »

በምርጫው ላይ ነጻ ተወዳዳሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ያስታወቁት ፕሬዚደንት ቡቴፍሊካ በጀመሩት የብሄራዊ ዕርቀ ሰላም እንደሚቀጥሉበት እና በሽብርተኝነት አንጻርም አስፈላጊውን ርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይሉ ገልጸዋል። በነዳጅ ዘይት ሀብት የታደለችው አልጀርያ፡ ምንም እንኳን በዓለም አሳሳቢ የፊናንስ ቀውስ ቢከተልም፡ የጀመረችውን የኤኮኖሚ ልማት መርሀ ግብር ወደፊት እንደሚገፉበት ፕሬዚደንቱ አስረድተዋል። ቡቴፍሊካ ከአስር ዓመት በፊት ስልጣን ከያዙ ወዲህ በሀገሪቱ ሶስት ነጥብ አምስት ሚልዮን የስራ ቦታዎችን እንደከፈቱና የስራ አጡን መጠንም ከሰላሳ ወደ አስራ ሁለት ከመቶ ዝቅ እንዳደረጉ፡ እንዲሁም፡ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ለማሳደግ ከአንድ መቶ ሀምሳ ቢልዮን ዶላር እንዳወጡ ሲናገሩ ይሰማል። ይሁንና፡ ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ ክላውዲያ አልትማን እንደሚሉት፡ ምንም እንኳን አልጀርያ በአሁኑ ጊዜ ከአንድ መቶ አርባ ቢልዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ቢኖራትም፡ በሀገርዋ ድህነት እንደተስፋፋ ይገኛል።

« ሂሰኞች ፖለቲካዊውና ኤኮኖሚያዊው አዲስ ጅምር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ሀገሪቱ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ዕድገት አይታይባትም። የአየር ማረፊያ፡ የህንጻ፡ ወዘተ.ን የመሳሰሉ የባዶ ዝና ፕሮዤዎች በአልጀርያውያን ሳይሆን በውጭ ኩባንያዎች ሲሰራ ይታያል። ቡቴፍሊካም የስራ አጥነትን ለመታገል የሚያስችል ፕሮዤ እንዳነቃቁ ይናገራሉ፤ ይሁንና፡ አልጀራያውያን ፕሮዤው የአልጀርያን ስራአጥነት ችግር ሳይሆን የቻይናን ስራአጥነት ለመታገል የተነቃቃ ነው እያሉ ሲያሾፉባቸው ይሰማሉ፤ ምክንያቱም፡ በአልጀርያ የተጀመረውን ብዙ ቻይናውያን ኩባንያዎች ናቸው ብዙውን የህንጻ ግንባታ ስራ የሚያከናውኑት። እና ምን ያህል አልጀርያውያን ወጣቶች ሀገሪቱን ለቀው እንደሚወጡ ማየት ይበቃል። » በቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይህንን ሀገሪቱ የምትገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቀየር የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠርላቸው ይችላል በሚል ተስፋ አድርገው የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን የፕሬዚደንታዊው ስልጣን ገደብ በተነሳበት ውሳኔ ይኸው ተስፋቸው መና ቀርቶባቸዋል።

RTR, DPA, ZPR, DW

AA,NM