1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ዲጂታሉ ሕብረተሰብ»

ረቡዕ፣ የካቲት 12 2006

የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስቴር ፣ እ ጎ አ ከ እንደ ጎርጎሪዮሳዊው ዘመን አቆጣጠር ከ 2000 ዓ ም አንስቶ፣ ዐበይት የሳይንስ አርእስት እየመረጠ፤ ሕብረተሰቡ በያመቱ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ እንዲወያይ ፤ እንዲከራከር፤ በቀጥታ በተግባር

https://p.dw.com/p/1BBjt

መተርጎም ያለበት ጠቃሚ ጉዳይ እስከሆነ ድረስም ተፈጻሚ እንዲያደርገው ሲመክር ቆይቷል። የሳይንስ ዓመት ተብሎ ዓመት ሙሉ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሕብረተሰቡ እንዲያተኩር ሲደረግ፤ ከውይይቶችና ክርክሮች ሌላ ፤ ትርዒቶችና ውድድሮችም ይካሄዳሉ። የዚህ ፣ አንድን ዓመት የሳይንስ ርእስ አስጨብጦ የማሰቡ ዋና ዓላማ ፣ በአንድ ሀገር ዕድገት ላይ ፣ ሳይንስና ምርምር ያላቸው ድርሻ በሕብረተሰቡ ዘንድ ፣ በግልጽ እንዲታወቅ ፣እንዲታይ ማድረግም ነው።

እናም ዘንድሮ የተመረጠው ርእስ ፣ «ዲጂታሉ ሕብረተሰብ» የሚል ነው።

እ ጎ አ በ 2000 ዓ ም ሲጀመር ዓመቱ «የፊዚክስ ዓመት» ነበረ የተባለው።

2001 የሥነ ሕይወት ዓመት

2002 የመልክዓ ምድር ሳይንስ ዓመት

2003 የሥነ ቅመማ ዘመን

2004 የሥነ ቴክኒክ ዓመት፤

Bundesinstitut Geowissenschaften
ምስል picture-alliance/dpa

2005 የአልበርት አይንሽታይን መታሰቢያ ዓመት፣ የፊዚክስ ዓመትም ተብሎ ነበር ፤ ይህ የሆነው፤ እ ጎ አ (ከ 1879-1955 )የኖረውን ያለፈውን ምዕተ ዓመት እጅግ ታላቅ ሳይንቲስት ለማዘከር ታስቦ ነው።

2006 የሥነ ቴክኒክ መረጃ ዓመት

2007 የሥነ ልቡና ሥነ ምግባር ሃይማኖት ፤ ፍልሥፍና ፣ቋንቋና የመሳሰለው 40 ያህል የትምህርት ዘርፎች የሚታሰቡበት ዘመን

2008 የሒሳብ ዓመት

2009 የምርምር አሳሽነት መታሰቢያ ዓመት(በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥነ ፈለክ መታሰቢያ ዓመት ነበረ)

2010 የኃይል ምንጭ መጻዔ-ዕድል

2011 የጤና ምርምር መታሰቢያ ዓመት

2012 ምድርና መጻዔ-ዕድሏ የተተኮረበት ዓመት

2013 የህዝብ መጠንና የዜጎች ዕድል፣

ዘንድሮ ደግሞ ፤ በይፋ እንሆ ከዛሬዋ ዕለት አንስቶ እስከ መጪው ዓመት ታኅሣሥ ወር 3ኛ ሳምንት ማለቂያ ድረስ ፤ ቀደም ሲል እንዳልነው ፣ «ዲጂታሉ ሕብረተሰብ» በሚል ርእስ ነው ዘመኑ የሚታሰበው።

እናም የጀርመን ፌደራል መንግሥት የትምሕርትና ምርምር ጉዳይ ሚንስትር ወ/ሮ ዮኻና ቫንካ ዛሬ ፤ እ ጎ አ የ 2014 አዲሱን የሳይንስ ርእሰ-ጉዳይ በይፋ ከማብሠራቸው በፊት ትናናት በዋዜማው እንዳስገዘቡት፤ የዲጂታል ሥነ ቴክኒክ ቀልጣፋ ዕድገት እያሳየ በመሆኑ፤ ስላላው ጠቀሜታና ጉዳት ህዝቡ በጥሞና ሊወያይበት ይገባል ብለዋል። ሚንስትሯ ለዜና አገልግሎት በሰጡት ቃል፤ «በአጠቃላይ በአካባቢያችን ዲጂታል አሠራርና አጠቃቀም በመሥፋፋቱ ፍርሃት ያደረባቸው፣ ጥርጣሬ ያልተለያቸው የሕብረተሰቡ አካላት አሉ» ነው ያሉት። ይሁንና ፤ «ዲጂታል ማሕበረሰብ »

Die digitale Gesellschaft mit Computermaus
ምስል DW

ምርምርና ሳይንስ፤ በኢንተርኔት ፤ የግልሰቦችን የግል የመረጃ ሰነዶች መጠበቅ እንዲቻል ጠንክሮ እንዲገኝ ምክክሩን የሚያጠናክር በመሆኑ፤ የተመረጠው ርእሰ ጉዳይ እጅግ ጠቀሚ መሆኑ ነው የተነገረለት።

ሰዎች፤ ባለፉት 20 ዓመታት ለራሳቸው የሚጠቅማቸውንም ሆነ የማይጠቅማቸውን መረጃ እንዴት እንደሚያገኙ እንዴት እንደሚኖሩ፤ እንዴት ከሰዎች ጋር መልእክት እንደሚለዋወጡ ሲታሰብ ፤ አንድ አዲስ አብዮት እንደተካሄደ መቁጠር ይቻላል።

ዓለም ከመጽሐፍ ሕትመት ጋር ከተዋወቀች ወዲህ ፤ «ዲጂታል ሥነ ቴክኒክ » እንደ ተከታይ አብዮት ሊታይ ይቻላል የሚሉ አሉ። ሳይንስና ምርምር በአርግጥ፤ ለዲጂታል ለውጥ አንቀሳቃሽ ሞተሮችና የለውጥ አጃቢዎች በመሆን ጠቀሚ ድርሻ ማበርከታቸው አልቀረም። አዲስ ሥነ ቴክኒክ ከማስተዋወቅና በዚህ ረገድ ውጤት ከማስገኘት ባሻገር፤ የኤኮኖሚ፤ ማሕበራዊና ሥነ ልቡናዊ አመለካከቶችም ቀስ በቀስ ፣ ከበስተጀርባ አዳዲስ ምልክቶች ማሳየታቸው አልቀረም።

ይህን በመሳሰሉ የማሕበራዊ ኑሮ እንቅሥቃሴዎች በመሳተፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደግፉ ጀርመናውያን 6,600,000 ናቸው። ይህም በጀርመን ሀገር ኢንተርኔት ከሚጠቀመው ኑዋሪ ከየ 8 ቱ አንዱ መሆኑ ነው። ከዛሬ ጀምሮ ፤ በጀርመን ሀገር 2014 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት እስኪያከትም፤ በአገር አቀፍ ደረጃ፤ ስለዲጂታል ህዝቡና ተመራማሪዎች መርኀ ግብር እየወጣ ይወያያሉ ፣ ከርእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ትርዒቶች ይመለከታሉ ፊልሞችን ያያሉ። ስለምርምር ይዞታም ይመከራል፤ ውይይት ይደረጋል ፤ ክርክርም ይካሄዳል። ህዝቡን ከሚያሳስበው አንዱ ፣ የኢንተርኔት አስተማማኝ አለመሆን ነው።

Protest gegen Überwachung in Berlin 29.07.2013
ምስል picture-alliance/dpa

ይኸው አስደናቂ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ውጤት በዚህ ዘርፍ የመጠቀ እውቀት ባላቸው «ሃከርስ» በተባሉ ወገኖች ሊሠረሠር ፤ በውስጡ የሚገኙ የግል ሰነዶች፣ መረጃዎች ሊመዘበሩ ፣ ሊሠረሠሩ ይችላሉ። ስለእነዚህ የኢንተርኔት ሰነድ ሠርሳሪዎች ጉዳይ ከተነሳ፤ ባለፈው ሳምንት በኮሎኝ ከተማ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ጠበብት በመሰብሰብ የተመክሮ ልውውጥ ማድረጋቸው ተመልክቷል። በኢንተርኔት አገልግሎት በኢ-ሜይል አጠቃቀም ያሉት የማያስተማምኑ ክፍት ቦታዎች የትኞቹ ናቸው? ያንተን አገልግሎት ሰጪ የመረጃ ማጠራቀሚያና ማከፋፈያ ማዕከል ፣ ሌቦች በቀላሉ መቆጣጠር የሚችሉት ምን ሲሆን ነው? ያን እንዴት መከላከል ይቻላል? ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ ነበረ። በማንቸስተር ፣ ኢንግላንድ ፣«ናሽናል ኮምፒዩቲንግ ሴንተር» የተሰኘው ድርጅት የመረጃ ሥነ ቴክኒክ የሰነድ ጥበቃ ነክ አማካሪ ፣ ቤን ዊልያምስ፣ ሶፍትዌር ወደሚሠሩ ታዋቂ ኩባንያዎች መረጃ እንደሚሠርቅ ለፍተሻ ወደ ኢ-ሜይል አገልግሎት ሰጪ ማዕከል የሚልኩት የስለላ ተግባር አብዛኛውን ጊዜ መሳካቱን ነው የገለጡት።

«ማወቅ የሚገባህ፤ የትኛው የሥነ ቴክኒክ ውጤት ሥራ ላይ እንደዋለና አድራሻውን ነው። መረጃ ማግኘት የሚቻለው፤ እንግዲህ፤ ተጠቃሚ ላላሆኑ ሰዎች ኢ-ሜይል በመላክ ነው። መልእክቱ ወደ ኩባንያው ነው የሚተላለፈው። የ ኢ-ሜይል ማጣሪያ ሥርዓቶችን ሁሉ ጥሶ!የምልከው ኢ- ሜይል የማያሠጋ ሆኖ ከታሰበ ወደ ዋናው የ ኢ ሜይል አገልግሎት ሰጪና ማከፋፈያ ፣ ዘልቆ ይገባል ማለት ነው።»

Besucher der Internetkonferenz Re:publica
ምስል picture-alliance/dpa

በርሊን ውስጥ ዛሬ ማታ፣ በመኻል አውሮፓ ሰዓት አቆጣጠር ፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት፣ (በኢትዮጵያ ከምሽቱ 3 ሰዓት ማለት ነው )የጀርመን የትምህርትና ምርምር ሚንስትር ወ/ሮ ዮኻና ቫንካ፣ «ዲጂታል ሕብረተሰብ» የሚል ርእስ የተሰጠውን ሕዝቡ የተለየ ትኩረት እንዲያደርግበት የተመደበውን ዓመታዊውን የሳይንስ ዘመን በልዩ ሥነ ሥርዓት ይከፍታሉ። ይህን ርእሰ ጉዳይ መንስዔ በማድረግ በአለንስባህ ከተማ የሚገኝ አንድ ተቋም ሕብረተሰቡን ይወክላሉ ብሎ ለመደባቸው 1515 ሰዎች የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ መጠይቅ አቅርቦ ነበር።

ታዲያ በኢንተርኔትሳቢያየተገኘውንማ ሕበረሰባዊለውጥ፤አዎንታዊአድርጎ ምላሽየሰጠውከየ5ቱአንዱነው። ለምሳሌ ያህልበ45 እና59 ዓመትየዕድሜእርከንከሚገኙት 16 ከመቶው የአሁኑንና መጪውን የዲጂታል ዘመን በብሩኅ ተስፋ የሚጠባበቁት ሲሆን፤ ዕድሜአቸው ከ 60 በላይ ከሆኑት፤ 10 ከመቶው ብቻ ናቸው በበጎ ዓይን የተመለከቱት። ከልጅነት አንስቶ በ «ስማርትፎንስ» እየተጠቀሙም ሆነ እየተገለገሉ ያደጉት ወጣቶች ኢንተርኔት መጻዔ ዕድልን ያሠምራል የሚል አመለካከት ነው ያላቸው።

እርግጥ ነው ፤ የግለሰቦችን የመረጃ ሰነድ አጠባበቅ በተመለከተ ፍጹም አስተማማኝ ሁኔታ አይችልም የሚል ጥርጣሬን በተመለከተ ፤ በተላይ አምና በሰኔ የቀድሞው የአሜሪካ ብሔራዊ የስለላ ድርጅት ባልደረባ ኤድወርድ ስነውደን ካጋለጠ ወዲህ ፣ብዙዎች ወጣቶችና ጎልማሶች ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው መሆኑ አልታበለም። ከዚህ ሌላ፤ በምርምር ዘርፍ ዲጂታል ሥነ ቴክኒክ፤ በእርምጃው ሰፊ ዕድል የሚያስገኝ ቢሆንም፤ ከተደቀነው አደጋ አንጻር ፣ የማሕበራዊና የሞራል ተግዳሮቶች ቀላል አለመሆናቸውም ነው የተነገረው።

የትምህርትና ምርምር ሚንስትር ዮኻና ቫንካ፣ ማንኛውንም አዲስ ሁኔታ፣ በተወሰነ ደረጃ በጥርጣሬ መመልከት ያለ ነገር ነው። ዘመናዊው ዲጂታል አገልግሎት፣ ለባልቴቶችና ለሽማግሌዎችም አያሌ ጠቀሚና ማራኪ ሁኔታዎች አሉት። ዘመናዊው ሥነ ቴክኒክ አሮጊቶችንና ሽማግሌዎችን በረዳትነት በሚገባ ማገልገል ይችላል። በዕድሜ በገፉ የሕብረተሰቡ ዓባላት ዘንድ ያለው ችግር አጠቃቀሙን ጠንቅቆ ያለማወቅ፤ መመሪያዎቹን ለማወቅ መቸገር ነው።

ዛሬ ማታ በይፋ የሚታወጀው 2014 «ዲጂታል ሕብረተሰብ » ሳይንሳዊ ዓመት ክፍተቶችን እንዴት እንደሚያቃልል በሚመጡት ወራት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ