1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደ.ሱዳን፤ ዳግም ግጭት ተቀሰቀሰ

እሑድ፣ ግንቦት 3 2006

የደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለት ቀንም ሳይሞላው ዛሬ ሳይጣስ እንዳልቀረ ተነገረ። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪርና ሪኤክ ማቸር ተኩስ ለማቆም ከትናንት በስተያ ነበር አዲስ አበባ ውስጥ የተፈራረሙት። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ስለመጣሱ የመንግሥትና የተፋላሚ ወገኖች እየተወነጃጀሉ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1BxvY
Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images

ለአምስት ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያቆም የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የልማት በይነ-መንግሥታት (IGAD) ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላትን አርብ ዕለት ሲያፈራረሙ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነበር። ዓማፂያኑ በመግለጫቸው የፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር ታማኝ ወታደሮች በእግረኛ ጦር ታጅበው በነዳጅ ሀብት የታደሉ ሁለት የሰሜናዊ ይዞታቸው ላይ የመድፍ ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው ጠቅሰዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት የመከላከያ ሚንሥትር ኮውል ማንያንግ በበኩላቸው ዓማፂያን አስቀድመው ጥቃት ቢያደርሱብንም ከፍተኛ ዕልቂት ደርሶባቸዋል ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP)ተናግረዋል። በስፍራው የሚገኙ ገለልተኛ የሠብዓዊ ዕርዳታ ሰጪ አካላት የተኩስ ልውውጥ የሰሙ መሆናቸውን ሆኖም ማን ቀድሞ ተኩስ እንደከፈተ እንደማያውቁ መስክረዋል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና አምባሳደር ስዩም መስፍን በተገኙበት የተኩስ አቁም ስምምነት ያደረጉት ከትናንት በስትያ አርብ ነበር።

Südsudan - Abkommen
ምስል Reuters

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በአማጽያኑ መሪ ሪኤክ ማቻር መካከል ባለፈው ታኅሳስ ወታደራዊ ፍልሚያ ተጀምሮ በሺ የሚቆጠሩ መገደላቸውና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከቀየው መፈናቀሉ ታውቋል። በእርግጥ ጥር አጋማሽ ላይ ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ባላንጣዎች በኢጋድ አደራዳሪነት በሸራተን አዲስ የመጀመሪያውን የሰላም ውል መፈራረማቸው ይታወሳል። ሆኖም ግን በዓማጺያኑ በኩል የቀድሞው ም/ፕ ሪክ ማቻር ሁሉንም ዓማጺያን አይወክክሉም ከሚለው ስጋት አንስቶ በሁለቱም ወገን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውሎ ሳያድር ነበር የተጣሰው።

አዲስ አበባ ውስጥ እንደገና የሰላም ውይይት እንዲጀመር ያግባቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙንና የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ጆን ኬሪ ናቸው። ለተኩስ አቁም ስምምነቱ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ አበባ የነበሩት የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአማጽያን መሪ ሪኤክ ማቻር፣ በቅድሚያ ከ2 ሳምንት በፊት ከእስር የተለቀቁትን 4 ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች አነጋግረዉ ነበር።

ማቻር ፣ ሽምግልናውን ከሚያካሂደው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሊቀ መንበር ፤ የኢትዮጵያን ጠ/ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝንም ማነጋገራቸው ተገልጿል። ምንም እንኳን ለአምስት ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የትናንቱ ስምምነት ለሁለተኛ ጊዜ ቢሆንም ቀደም ሲል በተካሄደው ስምምነት ወቅት ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ተገናኝተው አልተነጋገሩም። በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደዉ ስምምነት ወቅት ግን ሁለቱ ተቀናቃኞች ፊት ለፊት ለመገናኘት ችለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ጆን ኬሪ፤ ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪርን ደቡብ ሱዳን ውስጥ አግኝተው ካነጋገሩና ተቀናቃኛቸው የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪኤክ ማቸርን በስልክ ካወያዩ ከአንድ ሣምንት በኋላ ነው ሁለቱ ተቀናቃኞች ፊት ለፊት ተገናኝተው ስምምነቱን የተፈራረሙት። የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እየተደረገበት እንደሆነ ለማሳየትና ጫና ለማሳደር የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙንም ደቡብ ሱዳን አቅንተው እንደነበር የሚታወስ ነው።

Südsudan Riek Machar Soldaten April 2014
ምስል AFP/Getty Images

በሌላ በኩል በርካታ የዓለም መንግሥታት የደቡብ ሱዳኑን የተኩስ አቁም ስምምነት አወድሰዉ ነበር። የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የደረሱትን ስምምነት አስመልክተዉ«በጦርነቱ ዉስጥ ላለዉ ማህበረሰብ የአዲስ ተስፋ ምልክቱ ነዉ» ሲሉ መናገራቸዉ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ