1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደርግ የተወገደበት ሃያኛ ዓመት

ሰኞ፣ ግንቦት 15 2003

ግንቦት 20 1983 አቶ ቡልቻ እንደገለፁት ሰዉዬዉ ቤቴ-የሳር ቤቴ አረጀች ብሎ አፈረሳት።ሌላ መስራት ግን አልቻለም።ግንቦት 2003 ሰዌዉ በቁር-ሐሩር እንደተኮደኮደ ነዉ።

https://p.dw.com/p/RPXg
ምስል AP Graphics/DW

የትዉልድ ቀየ፥ ዕድሜ፥ ሥራ፥ ልምድ ገጠመኝ፥ ዓላማም ሁለትነታቸዉን ይበልጥ ቢያራርቅ እንጂ ጨርሶ አያገናኛቸዉም።አንዲት ጠንካራ ገመድ ግን ታስተሳስራቸዋለች።ኢትዮጵያዊነት።የዚያን ዕለት አዲስ አበባ ላይ የሆነዉ-ሲሆን ያቺ ቋጠሮ እኩል አስደሰተቻቸዉ።

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፥ አንጋፋ ኢኮኖሚስት፥ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ እና ፖለቲከኛ።

አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ የኢሕአዲግ ነባር ታጋይና ጋዜጠኛ።ያዕለት በመጪዉ ቅዳሜ ሃያ አመት ይደፍናል።ግንቦት ሃያ።ሃያኛዉ ዓመት መነሻ፥ የሁለቱ ሰዎች ገጠመኝ ማጣቃሻ የዛሬዉ የኢትዮጵያ እዉነት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
ያዘመን።በቡልቻ ደመቅሳ አይን።

አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ።

Portraitbild von Äthiopiens Ex-Diktator Mengistu Haile Mariam
ምስል picture alliance/dpa

ዋዜማዉ።ለነባሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ታጋይ የደርግ ዉድቀት ዋዜማ ያዉ ጦርነት፥ ዉጊያ ነዉ።ግን በድል-አድራጊነት ሥሜት ተስፋ የታጀበ ዉጊያ።ለእሳቸዉም እንዳሉበት ቦታና ሁኔታ ተስፋም ነበር።

ለአስራ-ሰባት አመት ያሕል ቆራጡ፥ አብዮታዊዉ፥ ሐገር ወዳዱ እየተባሉ ይንቆለጳጰሱ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለ-ማርያም ሐገር-ሥልጣናቸዉን ለተከታዮቸዉ ትተዉ ከሐገር የወጡት ከሳምንት በፊት ነበር።የኮሎኔል መንግሥቱ ከሐገር መዉጣት የሚመሩት ወታደራዊ-ሶሻሊስታዊ ሥርዓት የፍፃሜ መጀመሪያ መሆኑ በርግጥ ብዙ አለነጋገረም።

የኢትዮጵያ-አንድነት፥ ደርግን የሚተካዉ ሐይል ማንነት፥ ከሁሉም በላይ ሠላሳ-አመት ያስቆጠረዉ ጦርነት የመቆሙ ፍንጭ አለመታየት ግን የብዙዉ ኢትዮጵያዊ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕሰ-ጭንቀትም ነበር።በንግግር-ጭንቀቱ መሐል የኤርትራ ሸማቂዎች አስመራን ተቆጣጠሩ።ግንቦትም አስራ-ስድስት አለ።1983።

የያኔዉ የኤርትራ ሕዝባዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (EPLF) ኤርትራን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ የኢትዮጵያ አንድነት በነበረበት ያለመቀጠሉ ግልፅ ምልክት ነበር።የኤርትራ ነፃ መዉጣት ከEPLF ሸማቂዎች ጋር አብረዉ ሲታገሉ ለነበሩት ለኢሕአዲግ ታጋዮች የድል ብሠራት ዋዜማ እንጂ በርግጥ የሥጋት ምልክት አልነበረም።በአራተኛዉ ቀን-የራሳቸዉ የኢሐዲጎች ታላቅ ድል አዲስ አበባ ላይ ተረጋገጠ።

የኢትዮጵያ አንድነት ከዲፕሎማሲ ጣጣ ባለፍ በርግጥ ያለቀለት ጉዳይ ነበር።የኤርትራ የነፃነት ተፋላሚዎች በኢትዮጵያ አጋሮቻቸዉ ድጋፍና ይሁንታ የኤርትራን ባንዲራ ለማዉለብለብ የቀራቸዉ አልነበረም።ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታም፥ ብቻ ያ ወታደራዊ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት መወገዱ ቡልቻ ደመቅሳን ለመሳሰሉት ሐገር ወዳድ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ የሰላም፥ የእድገት ጀምበር አዲስ ብርቀት ነበር።እና ነባሩ ታጋይ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ ምናልባት ክላሺንኮቭ አንገበዉ፥ ቴፕ-ማይክራፎን አንጠልጥለዉ አዲስ አበባ ከገቡ ከወራት በሕዋላ-አንጋፋዉ ኢኮኖሚስት እስኪሪብቶ ሰንቅረዉ ተከተሏቸዉ።

ማግሥት።ሁለቱን ሰዎች ሁለትነታቸዉን ጀቡኖ አንድ ያደረጋቸዉ ደስታ-ተስፋ አበቃ።ለሴኩቱሬ ማግስቱም በርግጥ ጣመን ማዉጪያ፥ መረጋጊያ አስደሳች አኩሪም ነዉ።ለቡልቻ ግን ከአስራ-ሰባት አመት በሕዋላ የተመለሱባት አዲስ አበባ ፈርታ-ታስፈራራቸዉ ገባች።ከወራት በፊት ደማቅ የነበረዉ ተስፋቸዉም «ነበር» ሊባል ይወይብ ገባ።አቶ ሴኩቱሬ ግን ከያኔ-እስካሁን ያለና የነበረዉ አቶ ቡልቻ ከሚሉት ተቃራኒዉ ነዉ- ባይ ናቸዉ።

አቶ ቡልቻ ይሕን አይቀበሉትም።ሃያ አመቱ የኢትዮጵያዉን መብት ነፃነት የተደፈለቀበት፥ ፍትሕ የተዳፈነበት፥በነፃ የመናገር መብት የተጨፈለቀበት ሥራ-አጥነት የኑሮ ዉድነት የናረበት፥ ፍርሐት የነገሠበት ዘመን ነዉ። ከእንግዲሕስ-አቶ ሴኩቱሬ ብሩሕ ተስፋ አላቸዉ። መጪዉ ዘመን ኢትዮጵያ የምትበለፅግበት፥ የሕዝቧ ሰብአዊ-ዲሞክራሲያዊ መብት ይበልጥ የሚከበርበት፥ያሻዉን የፖለቲካ ድርጅት በነፃነት የሚመርጥበት ነዉ።

ግንቦት 20 1983 አቶ ቡልቻ እንደገለፁት ሰዉዬዉ ቤቴ-የሳር ቤቴ አረጀች ብሎ አፈረሳት። ሌላ መስራት ግን አልቻለም። ግንቦት 2003 ሰዌዉ በቁር-ሐሩር እንደተኮደኮደ ነዉ። ሃያ አመት። ያንድ ወጣት ዕድሜ። ሁለቱን እንግዶች አመሰግናለሁ።

Premierminister Zenawi Meles von Äthiopien
ምስል AP Photo

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ



ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ