1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨረቃ ግርዶሽ

ረቡዕ፣ መስከረም 19 2008

እሁድ መስከረም 16 ቀን 2008 ዓ.ም.እኩለ-ሌሊቱ እየገፋ ሲመጣ በምድራችን አንዳች አስደናቂ ክስተት ታይቷል፤ በተለይ በአውሮጳና በአፍሪቃ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለጥቂት ሰአታት ተስተውሏል።ጨረቃ ከተለመደው ውጪ ገዝፋ እና ቀልታ ለምድር ቀርባለች።

https://p.dw.com/p/1Gg0d
Deutschland Mondfinsternis Blutmond
ምስል picture-alliance/dpa/F.v. Erichsen

ደም መሳይ የጨረቃ ግርዶሽ

እናም በደረቁ ሌሊት በር ከፍተው ሰማዩን ያልማተሩ፤ አለያም በመሶኮት አሻግረው ቀዩዋን ግዙፍ ጨረቃን መመልከት ያልቻሉ ሰዎች ዳግም ይህን ክስተት ለመመልከት በርካታ ዓመታትን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ልዩ የጨረቃ ግርዶሽ በሰው ልጆች ታሪክ ለዘመናት በተደጋጋሚ ሆኖም ግን የተወሰኑ ዓመታትን እየጠበቀ የሚመጣ መሆኑን ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።


ለብዙዎች ግልጽ በሆነው መልኩ ምድር በራሷ ዛቢያ እየተሽከረከረች ፀሓይን ትዞራለች፣ ጨረቃ ደግሞ በምድር ዙሪያ ትሽከረከራለች። ፀሓይ ከመሀል ሆና ፕላኔቶችን ትዘውራለች። ምድር፣ ጨረቃና ፀሓይ በአንድ ወቅት አንድ መስመር ላይ የሚገናኙበት አጋጣሚ ወቅት እየጠበቀ ይከሰታል። ጨረቃ በመሬት ጥላ ውስጥ ስታልፍ አለያም መሬት በጨረቃና በፀሓይ መሀከል ስትሆን ያኔ የጨረቃ ግርዶሽ ይከሰታል። ሦስት አይነት የጨረቃ ግርዶሾች አሉ፤ እነሱም ሙሉ፣ ከፊልና ግማሽ የቸረቃ ግርዶሽ ይሰኛሉ። አሁን የተከሰተው ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ሲሆን፤ ጨረቃን ከመቼውም ጊዜ በላይ አግዝፎ ደም አስመስ ሏታል።

ጨረቃ ለመሬት በመቅረቧ ከወትሮው ገዝፋ ታይታለች
ጨረቃ ለመሬት በመቅረቧ ከወትሮው ገዝፋ ታይታለችምስል picture-alliance/dpa/F.v. Erichsen

ዶ/ር ጌታቸው መኮንን በደቡብ አፍሪቃ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስና የፕሮግራሚንግ መምህር ናቸው። የዶክትሬት ጥናታቸውን ያከናወኑት ርእደ-ጨረቃ (asteroseismology) ላይ ነው። የመስከረም 16ቱን ክስተት በሁለት አበይት ምክንያት ለየት ያለ ይሉታል።

በእርግጥ የጨረቃ ግርዶሽ በየዓመቱ ይከሰታል። የመስከረም 16ቱ የእኩለ-ሌሊት ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽን ዳግም ለመመልከት ግን አንድ ሕፃን ተወልዶ ለአቅመ አዳም እስኪደርስ ድረስ የሚያስጠብቅ ነው።


ዶ/ር ያብባል ታደሠ በሮም ቶርቨር ጋታ ዩኒቨርሲቲ የፕላንክ ሣተላይት መረጃ ተንታኝ ባለሙያ ናቸው። በአውሮጳ የኅዋ ተቋም የምድር አፈጣጠር ምሥጢርን ለመፍታት አሠሣ በሚያደርገው ሳተላይት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን መተንተን ነው ዋነኛ ሥራቸው። ጨረቃ ደም መስላና ገዝፋ ለምድር የቀረበበችበት የእሁዱ ክስተት ከሌሎቹ የጨረቃ ግርዶሾች በተለየ አስደናቂ የሆነበትን ምክንያት ይገልጣሉ።

ምድር ከጨረቃ በአማካይ 384 400 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። በጠፈር መንኵራኵር ወደ ጨረቃ የሚደረግ ጉዞ ጨረቃ ላይ ለመድረስ ሦስት ቀናትን ይፈጃል። በአውሮፕላን ሲሆን ደግሞ የሰው ልጅ ጨረቃ ዘንድ ለመድረስ ለ20 ቀናት መጓዝ ይኖርበታል። ዘንድሮ ጨረቃ ከመቼውም በላይ ለምድር ቀርባ ታየች ቢባልም፤ ቅርብ የተባለው ርቀት 356 000 ኪሎ ሜትር ያህል እንደሆነም ሣይንቲስቱ ይናገራሉ። ቀርባ በመታየቷም ከወትሮው ግዘፏ በ14 በመቶ ልቃ ደምቃለች። እይታው እጅግ ውብና ልዩ እንደነበረም ተገልጧል።

በነገራችን ላይ ምድር አንድ ጨረቃ ሲኖራት ጁፒተር የተሰኘችው ፕላኔት 67 እንዲሁም ሣቱርን 63 ጨረቃዎች አሏቸው። እንደ ቬኑስ እና ሜርኩሪ ያሉ ፕላኔቶች ደግም አንዳችም ጨረቃ የላቸውም ይባላል። የምድራችን ብቸኛዪቱ ጨረቃ አስደናቂ ግርዶሽን ለማየት እድሉ ያልገጠማችሁ ሌላ 18 ዓመታትን መጠበቅ እንደሚኖርባችሁ ሣይንቲስቱ ይናገራሉ።

ሣይንቲስቶች ይህች አስደናቂ፣ ውብ ጨረቃ እንዴት እንደተፈጠረች መቶ በመቶ በውል ለመናገር ይቸገራሉ። ስለሆነም ለጨረቃ መፈጠር የተለያዩ መላ ምቶችን ይሰነዝራሉ። ከመላምቶቹ አንደኛው፦ ጨረቃ የተፈጠረችው ከ4,5 ቢሊዮን ዓመት በፊት ነው የሚለው ይገኝበታል። ምድር ከግዝፈቱ የተነሳ ማርስ የተሰኘችውን ፕላኔት ከሚያህል ታያ ከተሰኘ ኮከብ ጋር ትላተማለች። በልትሚያውም ምድርና ታያ ይቀልጣሉ፣ ቀልጠውም አላበቁ አንዳች ግዙፍ ፍርስራሽ ይወጣቸውና ይህ ፍርስራሽ አለቅጥ ይሽከረከራል። ቀልጦ አለቅጥ የተሽከረከረው ግዙፍ ፍርስራሽ አሁን በምሽት ደምቃ የምናያትን ጨረቃ ከሰተ ሲሉ መላምታቸውን ያቀርባሉ። ፈጣሪ ከዋክብቱንና ጨረቃን ፈጠረ ከሚለው እምነት ጋር እጅግ የሚቃረን አስተሳሰብ ነው። የጨረቃ ግርዶሽ ግን ምድር ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ውብ ገጽታውን ይዞ በተደጋጋሚ ይከሰታል።

ጨረቃ የመሬት ጥላ ያረፈበት አካሏ ጠቆር ብሎ ይታያል
ጨረቃ የመሬት ጥላ ያረፈበት አካሏ ጠቆር ብሎ ይታያልምስል picture-alliance/dpa/F. Gambarini


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ