1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደማስቆ የሶሪያ መከላከያ ሚኒስትር ተገደሉ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 11 2004

ሶሪያ መዲና ደማስቆ ውስጥ ዛሬ በአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት የሶሪያ መከላከያ ሚኒስትርና ና የሶሪያው ፕሬዝዳንት አማች ተገደሉ ።

https://p.dw.com/p/15aUx
ምስል picture-alliance/dpa

በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሰረት ደማስቆ በሚገኘው የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ በማካሄድ ላይ ሳሉ በደረሰው በዚሁ አደጋ የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ጀነራል ዳውድ ራጃ ና የፕሬዝዳንቱ አማች አሴፍ ሻውካት ተገድለዋል ። በቦብም ጥቃቱ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ አል ሻር ና የብሔራዊ ፀጥታ መስሪያ ቤት ሃላፊ ጀነራል ሂሻም ኢክቲያር ከቆሰሉት መካከል ይገኙበታል ። ከአደጋው በኋላ የሶሪያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አሸባሪነትን መዋጋቱን እንደሚቀጥል አስታወቋል ። በዛሬው አደጋ የተገደሉት ጀነራል ራጃ ከ,መከላከያ ሚኒስትር ሥልጣናቸው በተጨማሪ የጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርም ነበሩ ።

ኮፊ አናንና ቪላድሚር ፑቲን
ምስል dapd

ሻውካት ደግሞ ምክትል መከላከያ ሚኒስትርና የቀድሞ የስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊ ነበሩ ። የሶሪያ አማፅያን ትግሉ ከሶሪያ ክፍለ ግዛቶች ወደ መዲናይቱ ደማስቆ መሸጋገሩን ትናንት አስታውቀው ነበር , ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶሪያውን የርስ በርስ ግጭት ለማስቆም የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸውን ቀጥለዋል ። ባን ኪሙን ዛሪ ከቻይና መንግሥት መሪዎች ጋር በጉዳዮ ላይ ለመምከር ቻይና ነበሩ ። ባን እንዳሉት ቻይና ግጭቱን በማስቆም ረገድ ወሳኝ ድርሻ አላት ።
« ቻይና በጣም ጠቃሚ ሚና ልትጫወት ትችላለች ። እዚህ ከተገኘሁበት ምክንያት አንዱ ይህ ነው ። ይህን ጉዳይ ከቻይና መንግሥት መሪዎች ከቻይና ፕሬዝዳንት ከሁጅንታው ና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩንግ ዴችና እንዲሁም ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር እመክርበታለሁ ። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል ። ሆኖም የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በከፍተኛ ደረጃ እንዲተባበር ይጠበቃል ። ምክር ቤቱ ደም መፋሰሱ እንዲቆም ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል »

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ