1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልተወገደው የዶቸ ቨለ የአማርኛው ሥርጭት መሰናክልና የሥራ አስኪያጁ መግለጫ፧

ሐሙስ፣ ጥር 29 2000

ዶቸ ቨለ፧ የአማርኛው አገልግሎት ከኅዳር 1 ቀን 2000 ዓ ም አንስቶ፧ አልፎ-አልፎ፧ ሥርጭቱን የሚያሠናክል እርምጃ አጋጥሞታል። ችግሩ እስካሁን ፈጽሞ አልተወገደም። ቦን በሚገኘው የዶቸ ቨለ መሥሪያ ቤት፧ የአማርኛው አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ሉድገር ሻዶምስኪ፧ በቅርቡ ኢትዮጵያ ደርሰው የተመለሱ ሲሆን፧ የጉዞአቸው ዓላማ ምን እንደነበረ፧ ተክሌ የኋላ አነጋግሯቸዋል።

https://p.dw.com/p/E0Wt
«ወደ ኢትዮጵያ የተጓዝኩት በርሊን ከሚገኘው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር መሥሪያ ቤታችን የገጠመውን የሥርጭት መታወክ በተመለከተ፧ ከተነጋገርሁ በኋላ ነበር። እናም፧ ይህን የፖለቲካ ርእስ አድርጎ ለመወያየት ነበረ ወደ ኢትዮጵያ የሄድሁ። እንደሚታወቀው ከኅዳር 1 ቀን 2000 ዓ ም አንስቶ የማሠራጫ ሞገዶቻችን ፧ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወክ ደርሰንበታል። የመሥሪያ ቤታችን የሥነ-ቴክኒክ ጠበብትም ሆኑ የአሜሪካ የመገናኛ ኮሚሽን (FCC) ጭምር ማሣራጫ ሞገዶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወኩ ያለጥርጥር ነው ያረጋገጡት።
ትክክለኛውን የፕሮቶክል ደንብ በመጠበቅ በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ፧ ለኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባቀረበው ጥያቄ ላይ፧ ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የፖለቲካ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖንና ከማስተወቂያ ሚንስትር አቶ ብርሃን ኃይሉ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲያዝ በትኅትና ጠይቀው ነበር። ይሁንና ሁለቱንም ቀጠሮዎች እንደማይቀበሉ በመገንዘባችን በጣም ነው ያዘንሁትና ቅር የተሰኘሁት። ቀደም ባሉት ጊዜያት፧ ስለ ችግሮቻችን ቢያንስ በወዳጅነት መንፈስ ሐሳብ እንለዋወጥባቸው ነበር። ቀጠሮ እንኳ ያላገኝንበትን ይህን ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ እዚያው በግልጽ አሳውቄአለሁ፥«
በትክክል እንደገለጹት፧ የአሜሪካ የመገናኛ ኮሚሽን (FCC) እና የዶቸ ቨለ የሥነ ቴክኒክ ጠበብት፧ የዶቸ ቨለና የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ፧ የአማርኛና የኦሮምኛ አገልግሎት ሥርጭት መሰናክል የሚያጋጥማቸው ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መሆኑን ደርሰውበታል። የሚያውከው ድምፅ፧ ምንጩ ከኢትዮጵያ መሆኑን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥጣናት ይህ ሲነገራቸው ምን ይላሉ?
«የዶቸ ቨለ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኤሪክ በተርማን ሥርጭታችን መታወክ እንደጀመረ በበርሊን ለሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ካሣሁን አየለ፧ በጻፉት ደብዳቤ ላይ የችግሩን መንስዔ በማጣራቱ ረገድ፧ ከኢትዮጵያ በኩል የትብብር ጥረት እንዲደረግ ጠይቀው ነበር።(ከዶቸ ቨለ ጋር በመተባበር፧ የዚህ አዋኪ ሞገድ ምንጭ ከየት እንደሆነ ለማፈላለግ ማለት ነው።) ይሁንና ሦስት ወራት፧ ምንም መልስ ሳይሰጥ አሁን በቅርቡ ጥር 19 ቀን 2000 ዓ ም፧ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሙን ያንፀባረቀበትን ደብዳቤ ለጀርመን መንግሥት ጽፏል። በዚህ መግለጫም፧ ማንኛውንም የማሠራጫ ሞገድ የማሠናከል እርምጃ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደማይቀበለው፧ ኢትዮጵያ የዶቸ ቨለንም ሆነ የማንኛውንም ከባህር ማዶ የሚያሠራጭ ራዲዮ ወይም የቴሌቭዥን ጣቢያ ተግባሩ እንዲሠናከል አታደርግም። የኤርትራን የማሠራጫ ሞገድም ቢሆን አታሰናክልም ይላል። እንግዲህ ያገኘነው ይፋው የኢትዮጵያ መግለጫ ይህን ይመስላል።«
ተጨባጩ ሁኔታ ወይም ሀቁ ግን ሌላ ነው.......።እንደሚታወቀው ኢትዮጵያና ጀርመን ወዳጅ መንግሥታት ናቸው። ጥሩ ግንኙነት አላቸው። ጅመን፧ በተለያዩ የልማት መስኮች በአጋርነት ተሠልፋ ትገኛለች። በልማት እርዳታ፧ በትምህርት፧ በግብርናና በመሳሰለው....ቀደም ሲል የገለጹት፧ የዶቸ ቨለ ሥርጭትት ከገጠመው እክል አኳያ፧ «ያደረሰው በጣም ቅር የሚያሰኝና የሚያሳዝን ሁኔታ፧ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ የሚያስከትለው ሳንክ አይኖርም ይላሉ?
«በእርግጥ ይህ ሥጋት አለ። በአዲስ አባባ የሚገኙት የጀርመን አምባሰደርም፧ ይህን ሥጋታቸውን በይፋ አሳውቀዋል። ለምሳሌ ያህል፧ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፧ ጀርመንን ለመጎብኘት ወደ በርሊን ይመጣሉ። እልባት ያልተደረገለት፧ ችግር መነሳቱ አይቀርምና በጉብኝቱ ላይ ጥላ ሊያሣርፍበት ይችላል። የኢትዮጵያና የጀርመን፧ ሁለቱም መንግሥታት፧ በቀጠሮው መሠረት፧ በሰሜኑ ንፍቀ-ክበብ የፀደይ ወቅት፧ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍም ይችላል። እንደእውነቱ ከሆነ፧ በኢትዮጵያ በኩል ካለው ጥቅም አኳያ፧ ቢያንስ እንኳ፧ ለመነጋገር ፈቃደኛነትን ማሳየት የሚጠበቅ ነው። ይህ የወዳጅነት ያልሆነ የሥርጭት ማሰናከያ ተግባር ተጣርቶ እልባት የሚያገኝበትን ብልሃት ለመሻት ዝግጁ መሆን ያሻል።
ከኢትዮጵያ በኩል በይፋ እንደሚገለጸው የመገናኛ ብዙኀን ነጻነትን ለማስፋፋት ዝግጁነት አለ። ፓርላማውም በመገናኛ ብዙኀኑ ደንብ ላይ ይወያይበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ዓይነቱ ቁርጠኝነት ካለው፧ እኔ የምጠይቀው...ከዶቸ ቨለ ጋር በመነጋገር ይህን የወዳጅነት መንፈስ የማያንጸባርቀውን ሁኔታ በማስወገድ መፍትኄ እንዲፈለግ ነው።«