1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልለየለት የቡርኪና ፋሶ ዕጣ

ሐሙስ፣ ኅዳር 4 2007

በቡርኪና ፋሶ የቀድሞው ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ በሕዝብ ኃይል የታከለበት ተቃውሞ ከሥልጣናቸው ወርደው ወደ ጎረቤት ኮት ዲቯር ሸሽተዋል። ሕዝቡ ካምፓዎሬ በህገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ በማስደረግ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ያደረጉትን ጥረት በመቃወም ያካሄደው ዓመፅም አብቅቷል።

https://p.dw.com/p/1DmUV
Ouagadougou Burkina Faso Putsch Parlamentsgebäude 8.11.2014
ምስል Jan-Philipp Scholz

የጦር ኃይሉ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ሲቭሉ ማህበረሰብ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረትም ተስማምተዋል። የፕሬዚደንቱ ከሥልጣን መወገድ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የአንድ ግለሰብ አገዛዝ በማክተሙ በሀገሪቱ እፎይታ ፈጥሯል። ያም ቢሆን ግን፣ ይኸው ርምጃ በቡርኪና ፋሶ ሰላም እና መረጋጋት ማምጣቱ አሁንም አጠራጣሪ እንደሆነ ይገኛል።

Ouagadougou Burkina Faso Putsch Krankenhaus Verletzte 8.11.2014
ምስል Jan-Philipp Scholz

የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬን የ27 ዓመታት አገዛዝ ለማራዘም በማሰብ ለምክር ቤቱ የቀረበውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ በመቃወም በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ነበር በመዲናይቱ ዋጋዱጉ ለበርካታ ቀናት አደባባይ የወጣው። የወጣበት ዓላማውንም ከግብ በማድረስ ሥልጣኑን እንደጨበጡ ለመቆየት የሞከሩትን ፕሬዚደንቱን ማባረር ችሎዋል። ለዚህ ግን ትልቅ መሥዋዕትነት ነበር የከፈለው። የሲቭሉ ማህበረሰብ ተወካዮች እንዳመለከቱት፣ በዚሁ ተቃውሞ ቢያንስ 30 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ180 የሚበልጡ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው አሁንም በሐኪም ቤት ውስጥ ይገኛሉ። ከነዚሁ መካከል አንዱ የ25 ዓመቱ ባሶሌ ኮንስቶን ሲሆን፣ ተቃዋሚውን ለመበተን የተሰማራው የፀጥታ ኃይል ዛቻ ዓላማውን እውን ከማድረግ እንዳላገደው በቆራጥነት ነበር የገለጸው።

Burkina Faso Isaac Zida mit Mogho Naba 04.11.2014
ምስል AFP/Getty Images/I. Sanogo

«እንደሚተኩሱብን ቢያስጠነቅቁንም፣ እኛ ለነርሱ ዛቻ እንደማንበረከክ በመገለጽ ተቃውሞአችንን በቁርጠኝነት ቀጥለንበታል። በዚህ ጊዜ ነበር እኔ እጄን፣ ከኔ ጋር የነበረው ደግሞ ራሱን በጥይት የተመታነው ። »

ባሶሌ ኮንስቶ ከሞት በመትረፉ ደስተኛ መሆኑን በማስታወቅ፣ ካምፓዎሬን ያወረደው የሕዝብ ዓመፅ ያለውጤት እንደማይቀር ተስፋውን ገልጾዋል። ይሁንና፣ በቡርኪና ፋሶ የሕዝቡን ተቃውሞ በተከተሉት ቀናት የታየው ሁኔታ ግን ይህ ተስፋው እውን መሆኑን አጠራጣሪ አድርጎታል።

Burkina Faso Oppositionspolitikerin Saran Sereme
ምስል Issouf Sanogo/AFP/Getty Images

ካምፓዎሬ እንደወረዱ የጦር ኃይሉ ሥልጣን በያዘበት ድርጊት ያልተደሰቱት የቡርኪና ፋሶ የተቃዋሚ ቡድኖች እና የሲቭሉ ማህበረሰብ ከብዙ ውይይት በኋላ ለአንድ ዓመት የሚቆይ በሲቭሉ የሚመራ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ተስማምተዋል። በስምምነቱ መሠረት፣ እአአ ህዳር 2015 ዓም በሀገሪቱ ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይደረጋል። ይሁንና፣ የሽግግሩን መንግሥት ምን እንደሚመራው እስካሁን በግልጽ አልታወቀም። እንደሚታየው፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በጣም መ የተከፋፈሉ ናቸው። የብዙዎቹ መሪዎች በብሌዝ ካምፓዎሬ የዴሞክራሲ እና መሻሻል ፓርቲ አባላት የነበሩ ናቸው፣ ከነዚህም በቀድሞው ፕሬዚደንት ችላ እንደተባሉ የተሰማቸው ጥቂት የማይባሉት የራሳቸውን ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማ ይዘው የተነሱ መሆናቸው ይነገራል። እና ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንዳስረዱት፣ የሽግግሩን መንግሥት አመራር በወቅቱ የያዙት የጦር ኃይሉ ሊየተና ኮሎኔል ያኩባ ኢዛክ ዚዳ በሥልጣኑ ኮርቻ እንደተቆናጠጡ ይቆያሉ የሚለው ሳይሆን ችግሩ፣ እስከ ምርጫው ድረስ ሊተካቸው የሚችል ተስማሚ ሲቭል ዕጩ መታጣቱ ነው። ተሰሚነት ያላቸው የተቃዋሚው ቡድን ተወካይ እና ራሱን የልማት እና የለውጥ ፓርቲ ብሎ የሚጠራው ፓርቲ መሪ ሳራ ሴሬም ግን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ምክክር የያዙት የተለያዩት ወገኖች የሽግግሩን መንግሥት በሚመራው ዕጩ ላይ በቅርቡ ገላጋይ ሀሳብ ላይ መድረሳቸው እንደማይቀር ለቡርኪና ፋሶ ሕዝብ ቃል በመግባት፣ በሀገሪቱ ደህና ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

« ሰላም እንደሚሰፍን እና አዲሶቹ መሪዎችም ለሕዝቡ እና ለሀገሪቱ የሚበጀውን ልማት እና መሻሻል እንደሚያስገኙ ተስፋችን ነው። የሽግግሩ ጊዜ ትክክለኛ፣ ሰላማዊ፣ ወደዴሞክራሲያዊው ምርጫ የሚያመራ እና በሀገሪቱም ዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት የሚተክል እንደሚሆን ነው ተስፋ የምናደርገው። »

ያን ፊሊፕ ሾልስ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ