1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩጋንዳና አማጺው ኃይል LRA፧

ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2000

የዩጋንዳ መንግሥት The Lord’s Resistence Army (LRA) በመባል ከታወቀው በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ይንቀሳቀስ ከነበረው አማፂ ኃይል ጋር ባለፈው ቅዳሜ፧ ከ 20 ዓመት በላይ የሆነው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲገታ ከሚያስችልና ወደ መጨረሻው ዐቢይ የሰላም ውል ከሚያሸጋግር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቆ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

https://p.dw.com/p/E0ZN
LRA የተባለው የደፈጣ ውጊያ ድርጅት አስገድዶ ካሰለፋቸው የልጅ ታጣቂዎች መካከል አንዱ፧
LRA የተባለው የደፈጣ ውጊያ ድርጅት አስገድዶ ካሰለፋቸው የልጅ ታጣቂዎች መካከል አንዱ፧ምስል AP

ይሁንና በጥቂት ቀናት ልዩነት፧ ማለትም፧ ትናንት፧ አማጽያኑ፧ ስምምነት በመጣስ ወደ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ከገቡ በኋላ ሲብሎችን ገድለዋል በማለት ከሷል። የአማጽያኑ ኃይል ዋና ተደራዳሪ ዴቪድ ኒኮራች ማትሳንጋ ግን፧ አሁን መንግሥት የሰነዘረው ክስ ትክክል ባለመሆኑ ፋይዳቢስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል

በዩጋንዳ መንግሥትና The Lord’s Resistence Army በተባለው አማጺ ኃይል መካከል፧ እ ጎ አ ከ 2006 ዓ ም አጋማሽ ገደማ አንስቶ ሲደናቀፍ የቆየው ዋና ነጥብ፧ ባለፈው ቅዳሜ፧ ነበር፧ በደቡባዊው ሱዳን ርእሰ-ከተማ ጁባ፧ ሸምጋዮችን የተባበሩት መንግሥታትን ልዑክ፧ የቀድሞውን የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት፧ ዮዓኺም ቺሳኖን ጭምር ባስፈነደቀ ሁኔታ እልባት ያገኘው። የቀረው አማጽያኑ ትጥቅ የሚፈቱበት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ሲሆን፧ እርሱም በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ፧ እማኞቹ ሁሉ ተስፋ አድርገው ነው ስምምነቱን ያወደሱት። የ LRA ሹማምንት፧ ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ፧ አማጺው ኃይል ማዕከላዊት አፍሪቃ ውስጥ ሠርጎ ገብቶ ሰዎች ገደለ የሚሉት ወገኖች ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። በዩጋንዳ የአካባቢ ትብብር ጉዳይ ሚንስቴር፧ ሚንስትር ደኤታ አይሳክ ሙሱሙባ እንደሚሉት፧ መንግሥታቸው ከማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ባለሥጣናት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የአሁኑን የውዝግብ ሂደት ይመረምራል። የ LRA ባለሥልጣናት፧ የማንኛውንም የትጥቅ መፍታት ረቂቅ የውል ሰነድ በኮንጎ ድንበር አቅራቢያ እንደሚገኙ ለሚነገርላቸው የደፈጣ ተዋጊው ኃይል መሪ ጆሰፍ ኮኒ በቅድሚያ እንደሚያቀርቡ ነው የገለጡት። የትናንቱ ክስ፧ ባለፈው ቅዳሜ በተደረሰው ስምምነት ላይ ጥላ ያሳርፍ ይሆን?
እንደገና ውሃ-ቅዳ ውሃ-መልስ መሰሉ ክስ፧ መሠረት ያለው ወይስ በድርድሩ፧ የላቀ ጠቀሜታ ለማግኘት በመሰላሰል የሚሠነዘር ነው? የዶቸ ቨለ የኪስዋሂሊው ክፍል ዋና አዘጋጅ፧ ሙሐመድ አብድረህማን አስተያየቱን እንዲህ አካፍሎናል።
«እንደሚመስለኝ፧ ይህ ዓይነቱ ክስ ድሮም ነበረ። የሰላሙ ሂደት-ነክ ውይይት እ ጎ አ በ 2005 ዓ ም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የቀጠለ ነው። እስቲ በመጀመሪያ ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ስለተፈረሙት ሁለት ስምምነቶች ላውሳ! በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ማለትም፧ በዩጋና መንግሥትና በተፋላሚው(LRA) መካካል የተደረሰው ስምምነት፧ «በሰብአዊነት ላይ ወንጀል የፈጸሙት ወገኖች« በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሄግ ውስጥ ሳይሆን፧ ዩጋንዳ ውስጥ እንዲዳኙ የሚል ነው። የዩጋንዳ መንግሥት እ ጎ አ በ 2005 ዓ ም፧ በዓለም አቀፉ፧ የጦር ወንጀለኞች ተከታታይ ፍርድ ቤት የቀረበው መጥሪያ ደንብ ይሰረዝ! ይህ ሲሆን በዩጋንዳ ዕርቅና ሰላም የሚሠምሩበት ዕድል ይኖራቸዋል ማለቱ አይዘነጋም። ይህ ጥያቄና የሰላም ፍላጎት በ LRA የቀረበ እንደነበረ እሙን ነው። ነግ ግን ይህን አቋም ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎታል። ይሁን እንጂ፧ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ጁባ ላይ ተስማምተውበታል። ከዚያ የተከተለው በዩጋንዳ ሰላም የሚሠፍንበት ፈው መቅደዱን የሚያበሥር ዜና ነበር። ባለፈው ሳምንት ደግሞ የተኩስ አቁሙን ውል ከሚያራዝም ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህ በእርግጥ የመጨረሻው የሰላም ውል መፈራረም የሚያስችል አንድ ዐቢይ እመርታ ሆኖ ነው የታየው! ስለዚህ አሁን ከሁለቱም በኩል የሚሰማው የቃላት ልውውጥ የፖለቲካ ስልት ነው። እያንዳንዱ ወገን፧ በጁባ በመካሄድ ላይ ካለው የሰላም ውይይት፧ የየራሱን አቋም አጠናክሮ የሚበጀውን ውጤት ለማግኘት መሻቱ አይቀሬ ነው።«
ከ 20 ዓመት በላይ የሆነው፧ ሰሜናዊውን ዩጋንዳ፧ ምሥራቃዊውን ኮንጎና ደቡብ ሱዳንን ሲያናጋ የቆየው በ 10 ሺ የሚቆጠር ህዝብ ያለቀበትና 2 ሚልዮን ያህል ሰዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉበት የእርስ-በርስ ጦርነት በተቻለ ፍጥነት እልባት ያገኝ ዘንድ፧ ሰላም በማጣት ሲታመስ የቆየው ህዝብና ሰላም ወዳድ የሆኑ ወገኖች ሁሉ ፍላጎት ነው።