1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን ከሜደኑ ግድያ አንድ ዓመት በኋላ

ማክሰኞ፣ የካቲት 17 2007

በዩክሬን ዋና ከተማ ክየቭ በሜይደን የነፃነት አደባባይ ከ1 ዓመት በፊት ለተቃውሞ ሰልፍ ወጥተው የተገደሉት ሰዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ታስበዋል ።

https://p.dw.com/p/1Eggp
Gedenkmarsch für die Opfer des Aufstands auf dem Maidan in Kiew
ምስል S. Gallup/Getty Images

ባለፈው ዓመቱ የዩክሬኑ ህዝባዊ ንቅናቄ በክየቩ የነፃነት አደባባይ በሜደን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ሲያካሂዱ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ ከ110 እስከ 123 ይገመታል ። ከነዚህ አብዛኛዎቹ እጎአ የካቲት 20፣ 2014 በክየቩ የሜደን አደባባይ በአነጣጣሪ ተኳሾች የተገደሉ ናቸው ። የሰልፈኞቹ ገዳይ ማንነት ከዓመት በኋላ አሁንም መልስ አላገኘም ። ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎቻቸው ተኳሾቹ የዩክሬን ፖሊሶች ወይም የያኔውን ፕሬዝዳንት የቪክቶር ያኑኮቪች ደጋፊ ሩስያ ያሰማራቻቸው ተኳሾች ናቸው ይላሉ ። ሌሎች ደግሞ ከራሳቸው ከተቃዋሚዎቹ መካከል ሆን ብለው ብጥብጡ እንዲባባስ የፈለጉ ጽንፈኞች የፈፀሙት ነው ሲሉ ይናገራሉ ። በሜደኑ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገደሉት በታወሱበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻው የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሬሼንኮ አነጣጥሮ ተኳሾቹን ያደራጁት ከሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አማካሪዎች አንዱ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ዩክሬን አላት ብለዋል ። ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት ሪፖርትም ባለፈው ሳምንት ይወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነበር ። ያም ተባለ ይህ እስካሁን የገዳያቹ ማንነት በግልጽ አልታወቀም ። በግልፅ የሚታወቅ ነገር ቢኖር ይህ ግድያ ከተፈጸመ ከአንድ ዓመት በኋላ በዩክሬን ከዚህ ቀደም ባልተጠበቀ ሁኔታና በፍጥነት ብዙ ለውጦች መታየታቸው ነው ።በተቃዋሚዎች ላይ በተፈፀመው ግድያ ምክንያት የአውሮፓ ህብረት መልዕክተኞች ወደ ክየቭ ከተጓዙ በኋላ በያኔው ፕሬዝዳንትና በያኑኮቪች ላይ ጫና አድርገው ከተቃዋሚዎች ጋር ለተወሰኑ ወራት አብረው ለመሥራት ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ለመጥራትና ህገ መንግሥታዊ ለውጦችም ለማድረግ የሚያስችላቸው ስምምነት ተፈራረሙ ተብሎ በሰፊው ተነገረ ። ይሁንና ከሰዓታት በኋላ ያኒኮቪች የመሰወራቸው ዜና ተሠራጨ ። በማግስቱ ምሥራቅ ዩክሬን መግባታቸው ተሰማ ።ከዚያም የት እንዳሉ ሳይሰማ ቆይቶ ሩስያ መግባታቸው ተነገረ ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሩስያ ወታደሮች ደቡብ ዩክሬን የምትገኘዋንና ከጥንት ጀምሮ የሩስያ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር የነበረችውን ስልታዊ ከተማ የክሪምያን ልሳነ ምድር ይዘው ህዝቡ በሰጠው አከራካሪ ህዝበ ውሳኔ ግዛቱ ወደ ሩስያ ፌደሬሽን ግዛት እንድትጠቃለል ተደረገ ። ከአንድ ወር በኋላ የታጠቁ ኃይሎች በምሥራቅ ዩክሬን ግዛቶች የሚገኑ ህንፃዎችን መቆጣጠር ያዙ ። ይኽው ግጭት እየተስፋፋና እየከፋ ከ5600 በላይ ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሁለት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢደረጉም ግጭቱ ሊቆም አልቻለም ። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ አዲስ ፕሬዝዳንት ና መንግስት ያቋቋመችው ዩክሬን በሩስያ ይደገፋሉ ከሚባሉ ኃይሎች ጋር በምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል ባካሄደችው ውጊያ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱት ከሃገሪቱ ተሰደዋል ።ውጊያው እንዲቆም ከአንዴም ሁለቴ በሚንስክ ቤላሩስ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ላይ ቢደረሱም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን አልቻለም ።ሩስያ ዩክሬንና የዩክሬን አማፅያን በምሥራቅ ዩክሬንን የተባባሰውን ውጊያ ለማስቆም ከ10 ቀናት በፊት አዲስ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ይኽው በጀርመን መራሂተ መሥግሥት አንጌላ ሜርክልና በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ሸምጋይነት ሚንስክ ቤላሩስ ውስጥ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ጋር ለ17 ሰዓታት በተካሄደ ንግግር የተደረሰበት አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት እስካሁን በተለያዩ የምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደተጣሰ ነው ። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላለመከበሩ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ በማድረጉ ቀጥለዋል ። የዩክሬን መንግስት ግጭቱን በማባባስ እንደ ከዚህ ቀደሙ አሁንም ሩስያን በግንባር ቀደምትነት በመወንጀሉ ቀጥሏል ። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ የዛሬ 10 ቀኑ የተኩስ አቁም ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ ሩስያ በግዛቴ ጥቃት ፈፅማለች ሲሉ ከሰው ነበር ።

Ukraine Maidan Protest Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/Maxim
Ukraine Kiew Maidan ARCHIV & EINSCHRÄNKUNG
ምስል Oleksiy Furman

«ሚንስክ ውስጥ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ የፈተፀመው ጥቃት በዩክሬን ሰላማዊ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሚንስኩ ንግግር ውጤት ላይም የተፈፀመ ጥቃት ነው ። አንዳች ማብራሪያ ሳይሰጥ የሩስያ የማጥቃት ዘመቻ በጣም ተባብሷል።»

የተኩስ አቁሙ ይፀናል ከተባለበት ቀን በኋላም የዩክሬን አማፅያን ዴባልትሴቭ የተባለችውን ከተማ ከከበቡ በኋላ ከተማይቱን ከሞላ ጎደል ተቆጣጥረው ነበር ። በዴባልትሴቨው ጥቃት ሩስያዎችም ተሳትፈዋል ስትል አሜሪካን ከሳለች ። የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄን ፕሳኪ

Anschlag auf Maidan-Gedenkveranstaltung in Charkiw
ምስል picture-alliance/dpa/S. Kozlov

«የሩስያ ጦር ኃይል በዴባልትስቭ ዙሪያ የዩክሬን ይዞታዎችን የሚደበድብባቸውን በርካታ መድፎችን እና የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን አስፍሯል ።እነዚህ መሣሪያዎች የሩስያ ጦር ኃይል እንጂ የአማፅያኑ አለመሆናቸውን እርግጠኛ ነን ።የሩስያ ጦር ኃይል በዴባልትሴቨ አቅራቢያ የተተከለ የአየር ጥቃት መከላከያም አለው ።እነዚህም የሩስያ ጦር ኃይል እንጂ የአማፅያኑ ስላለመሆናቸው እርግጠኞች ነን ። ይህ ከዚህ ሳምንቱ መንፈስ ጋር አብሮ የሚሄድ እንዳልሆነ ግልፅ ነው ።»አነዚህን የዩክሬንና የአሜሪካን ክሶች የምታታጥለው ሩስያ በበኩልዋ ለዩክሬን ግጭት መፍትሄው ለምስራቅ ዩክሬን ህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ነው ትላለች። በተመድ የሩስያ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን በተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ይህንኑ አስታውቀው ነበር ።

«ከምሥራቅ ዩክሬን ህዝቦች ጋር መነጋገር አለብን። ግዛታቸው ፌደራላዊ ህገ መንግሥት እንዲኖረው ይፈልጋሉ። ያንን ነው ማድረግ ያለብን።»

በሚንስክ፣ ቤላሩስ ከ10 ቀናት በፊት በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ሁለቱም ወገኖች የጦር መሣሪያቸውን ውጊያ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች ማንሳት አለባቸው ። ይህ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ነጥብ ቢሆንም አሁንም ተግባራዊነቱ በሁሉም አካባቢዎች አልሰመረም ። በትናንትናው እለት እንኳን በዩክሬንዋ የወደብ ከተማ በማሪዩፑል አቅራቢያ የሩስያ ታንኮች በብዛት እየሰፈሩ መሆናቸውንና አማፅያንም በመንግሥት ወታደሮች ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን የክየቭ መንግሥት አስታውቋል ። መንግስት እንደሚለው ሩስያ ወደ ማርዮፖል 20 ታንኮችን ልካለች ። ከመካከላቸው ሁለቱ ባለፈው እሁድ በዩክሬን ይዞታዎች ላይ ድብደባ አካሂደዋል ።ሞስኮ ግን ለአማፅያኑ ድጋፍ ትሰጣለች መባሉን ትቃወማለች ። ማርዮፖል በአማፅያን እጅ ከገባች በሩስያ ድንበር በኩል ዩክሬንንና ክሪምያን በቀላሉ የሚያገናኝ መሸጋገሪያ ትሆናለች ። ጥቃቱ በዚህ መልኩ በመቀጠሉም ከተኩስ አቁም በስምምነቱ ጋር ሁለቱ ወገኖች የጦር መሣሪያዎቻቸውን ውጊያ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች እንዲያስወጡ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊነት የሚታሰብ አለመሆኑን ነው ከመንግሥት በኩል የተነገረው ። እስካሁን ሰላማዊ በነበሩ የምሥራቅ ዩክሬን አንዳንድ ከተሞችም ያጋጠሙ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ማሳሰባቸው አልቀረም ። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ና የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ በተገኙበት ኬቭ ውስጥ የሜደኑ ሰማዕታት በታሰቡበት እለት ሰላማዊ በነበረችው በምሥራቅ ዩክሬንዋ ከተማ በካራኪቭ የፈነዳ ቦምብ ሶስት ሰዎችን ከገደለ ወዲህ በከተማይቱ ውጥረት ሰፍኗል ። ያልፀናው የተኩስ አቁም ይብሱን እየተጣሰ ከሄደ በሩስያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ ምዕራባውያን መዛታቸውን ቀጥለዋል ። ከሚንስኩ የተኩስ አቁም ስምምነት በፊት አንዳንድ የአሜሪካን ፖለቲከኞች ወደ ዩክሬን የጦር መሣሪያ እንዲላክ ይጎተጉቱ ነበር ። ሆኖም የአውሮፓ ህበረት አባል ሃገራት በተለይም ጀርመን ወደ ለዩክሬን መንግስት የጦር መሣሪያ መስጠቱን በጥብቅ በመቃወም በሰላሙ ጥረት እንዲገፋ በያዘችው ጠንካራ አቋም ከፈረንሳይ ጋር ተፋላሚዎቹ ወገኖች የሚንስኩ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አብቅታለች ።በሜይደኑ መታሰቢያ ላይ የተገኙት የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ ለዩክሬን ወታደራዊው ድጋፍ የማይደርግ ከሆነ በሌላ መስክ ትብብሩ መጠናከር እንደሚገባው አሳስበው ነበር ።።

Ukraine Gedenken am 1. Jahrestag des Blutbads auf dem Maidan
ምስል Reuters/Valentyn Ogirenko

«በወታደራዊ እርምጃ ካልተሳተፍን ለዩክሬን ማህበረሰብ በምን ዓይነት መንገድ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት እንደምንችል ማሰብ አለብን ።አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን ማበርከት ብቻ ሳይሆን ወደ ዲሞክራሲና ወደ መረጋጋት የሚወስዱ ሂደቶችም የተሳኩ እንዲሆኑ ድጋፍ መስጠት ይኖርብናል ። »

Maidan (Film)
ምስል ATOMS & VOID

የዩክሬን ተፋላሚ ኃይሎች ከ10 ቀናት በፊት የተኩስ ቀቁም ለማድረግ መስማማታቸው ለአውሮፓ እፎይታ ተደርጎ ነበር የተወሰደው ። ተግባራዊ ይሁን ከተባለበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ ሲጣስ የቆየው የተኩስ አቁም ፀንቶ መቀጠሉም ሆነ ሁለቱ ወገኖች በተስማሙት መሠረት ከባድ የጦር መሣሪያዎቻቸውን በሙሉ ማስወጣታቸው በአሁኑ ደረጃ ማወቅ ያስቸግራል ። ከአንድ ዓመት በፊት የለውጥ ጥያቄ ይዞ የተነሳው የዩክሬን ህዝብ ሃገሪቱ ከገባችበት ውጊያ እንዴት ሊገላገል እንደሚችልም እስካሁን አልታወቀም ። በርካታ የዩክሬን ዜጎች ከፖሮሼንኮ ና ከመንግሥታቸው ድል ይጠብቃሉ ።ሆኖም አሳዛኙ እውነታ የዩክሬን ጦር ትልቁን ጠላቱን ሩስያን ማሸነፍ አለመቻሉ ነው ። ከዚህ ሌላ ከአንድ ዓመት በፊት ህዝቡ በሜደን አደባባይ ተቃውሞ ካቀረባቸው ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ አልተመለሱም ።ከመካከላቸው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ነፃ የፍትህ አካል መቋቋም እና ሙስናን ማስቆም የሚሉት ይገኙበታል ። አነዚህ መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎችና የምሥራቅ ዩክሬኑ ውጊያ አሁንም የሃገሪቱ ፈተናዎች ሆነው መቀጠላቸው አይቀርም ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ