1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2013 ዓ.ም ሳይንሳዊ ግኝቶች ቅኝት በከፊል

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 3 2013

የንቦችን ዝርያ ከጥፋት የሚታደገው የዘረ-መል ባንክ የዩሪ ጋጋሪን የጠፈር ጉዞ 60ኛ ዓመት ደመናን ወደ ዝናብ የሚቀይረው ቴክኖሎጅ እንዲሁም «ሜሴንጀር አር.ኤን ኤ»ቴክኖሎጅና የመከላከያ ክትባቶቸ እየተገባደደ ባለው 2013 ዓ/ም በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ከዳሰስናቸው ዋና ዋና ሳይንሳዊ ጉዳዮች መካከል ነበሩ።

https://p.dw.com/p/405S0
Milchstraße
ምስል X-Ray:NASA/CXC/UMass/D. Wang et al.; Radio:NRF/SARAO/MeerKAT

የ2013 ዓ/ም ሳይንሳዊ ዓግኝቶች ቅኝት በከፊል



እየተገባደደ ባለው  2013 ዓ/ም  ከቀረቡ ሳይንስ ነክ ዘገባዎች መካከል በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ያገኙ ሶስት ሳይንቲስቶችን የቃኘንበት ዝግጅት አንዱ ነበር። ስዊዲን ስቶኮልም የሚገኘው የኖቬል ኮሚቴ በጎርጎሪያኑ 2020  በኢትዮጵያ አቆጣጠር  ደግሞ በ2013 ዓ/ም መጀመሪያ ለብሪታንያዊው ሳይንቲስት ሮጀር ፔንሮሴ፣ ለጀርመናዊው የስነ-ፈለክ ተመራማሪ ሬንሃርድ ጌንዝል እና ለአሜሪካዊዋ የፊዚክስ ሊቅ አንድሪያ ጌዝ  በፊዚክስ ዘርፍ  የኖቬል ሽልማት ሰጥቷል። ሊቃውንቱ ሽልማቱን ያገኙት «ብላክ ሆልስ»ተብለው በሚጠሩት የአፅናፈ-ሰማይ ጨለማ ክፍል ላይ ባደረጉት ምርምር ነው።
 ተመራማሪው   ሮጀር ፔንሮዝ ጥቋቁር ጉድጓዶች ወይም «ብላክ ሆልስ»  የአጠቃላይ የአንፃራዊነት ፅንሰ-ሀሳብ ቀጥተኛ ውጤት መሆናቸውን አሳይተዋል።ፕሮፌሰር ሬይንሃርድ ጌንዘልና አንድሪያ ጌዝ  ደግሞ «ጋላክሲ» ተብሎ በሚጠራው  የከዋክብት ክምችት ማዕከል ብርሃን በውስጣቸው የማያልፍባቸው ግዙፍና የታመቁ  ጨለማ ክፍሎች ወይም «ብላክ ሆልስ» መኖራቸውን ያረጋገጠ  ግኝት ሰርተዋል።
 በጎርጎሪያኑ 1965 ዓ/ም የታተመው የፔንሮሴ ምርምር ከአልበርት አንስታይን አጠቃላይ የአንፃራዊነት ፅንሰ-ሀሳብ ወዲህ በዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ግኝት የተባለ ሲሆን፤የጌንዝልና የባልደረባቸው ግኝት ደግሞ እንደ ኮሚቴው ገለፃ  «ብላክ ሆልስ»ን በተመለከተ እስካሁን ከተረጉት ምርምሮች ሁሉ በጣም የሚያሳምኑ ማስረጃዎችን የያዘ ግኝት ነው። ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ራየንሀርድ ጌንዘልም ለምርምሩ አድናቆት አላቸው።
«በጣም ጠንካራ ቡድን ነው።በ«ብላክ ሆልስ» ላይ በተደረገው ምርምር ስለ ስበት በስፋት  ለማሰላሰል አግዟል። ከዓመታት በፊት ካከበርነው የአጠቃላይ አንፃራዊነት ጽንሰ-ሀሳብ   በ«ብላክ ሆልስ»  በኳንተም ፊዚክስ፣ እና በበርካታ ጎራዎች እንዲሁም በስበት ኃይል ላይ  ምርምር መደረጉ እጅግ በጣም አስደሳች ነው። »

Schweden Die 3 Physik-Nobelpreisträger 2020
ምስል Fredrik Sandberg/Reuters

የኖቬል ኮሚቴ አባሉ ፕሮፌሰር ኡልፍ ዳንኤልሰን እንደሚሉት ይህ ህልም የተሳካው እንግሊዛዊው ሊቅ ጆን ሚሸል  ንድፈ ሀሳቡን ካቀረበው ከ200 ዓመታት በኋላ ነበር።
 የንቦችን ዝርያ  ከጥፋት የሚታደገው የዘረ-መል ባንክ
ሌላው በ2013 ዓ/ም ከዳሰስነው ሳይንሳዊ ግኝት መካከል የንቦችን ዝርያ  ከጥፋት የሚታደገው የዘረ-መል ባንክን  የቃኝንበት ዝግጅት ይገኝበታል።
በተፈጠሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች  ንቦች ብዝሃነታቸው ላይ ስጋት እየተደቀነ መምጣቱን ተመራማሪዎች በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። ይህንን ችግር  ለመከላከል  የንቦችን ዘረ-መል በሳይንሳዊ ዘዴ  በቤተ-ሙከራ ማቆየት ተጀምሯል።እዚህ ጀርመንም በአውሮፓ የመጀመሪያው የንቦች  የዘረ-መል ባንክ  ስራ የጀመረው በዚህ ዓመት ነው።
በጀርመን  የበርሊን ግብርና ምርምር ተቋም በማር ንቦች ላይ ተመራማሪ የሆኑት ያኮብ ቫግነር  የንቦችን ዘረ-መል ለማቆየት ምርምር ያደርጋሉ።ተመራማሪው የዘረ-መል መረጃን የተሟላ ለማድረግ በመላው ጀርመን ከሚገኙ የተለያዩ  የንብ  ዝርያዎች ናሙናዎችን  ይሰበስባሉ።
  «የማር  ንቦች  እጅግ  በጣም የተለያዬ ዝርያና ዘረ-መል ያላቸው ናቸው።ከነዚህም አንዱ በአሁኑ ወቅት እየጠፋ የመጣው የአውሮፓ ጥቁር የማር ንብ ዝርያ ይጠቀሳል።ለዚህም ነው ዛሬ ናሙናዎችን ለመሰብሰብ እዚህ የተገኘነው።»
የዘረ-መል ባንክ የዕፅዋትንና የእንስሳትን ዝርያ ከጥፋት ለመታደግና የዘረ-መል ሀብትን ለማቆየት የሚረዳ ሳይንሳዊ ዘዴ ነው።መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ዘዴ በነብሳት ላይ ብዙ ያልተሰራበት ሲሆን ቀደም ሲል በአሜሪካ በቅርቡ ደግሞ በጀርመን፤ የንቦችን  ዘረ-መል በሳይንሳዊ ዘዴ ማቆየት ተጀምሯል። ተመራማሪው ቫግነር እንደሚሉት ይህ የጀርመን ምርምር በአውሮፓ የመጀመሪያው ነው።
ነገር ግን ይህ ሳይንሳዊ ዘዴ  ከፍተኛ ወጪንና ቴክኖሎጅን የሚጠይቅ በመሆኑ ለአፍሪቃም ይሁን ለኢትዮጵያ ከዚህ ይልቅ አደጋዎቹን መከላከል የበለጠ ተመራጭ መሆኑን ነው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህርና የነብሳት ተመራማሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር ኢልማና ጌቱ በወቅቱ የገለፁት።
ደመናን ወደ ዝናብ የሚቀይረው ቴክኖሎጅ
 ሊጠናቀቁ ቀናት በቀሩት 2013 ዓ/ም ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ መንገድ ደመናን ወደ  ዝናብ  የመቀየር ስራ መጀመሯን የገለፀችበት ዓመት ነበር።በሰው ሰራሽ መንገድ ደመናን ወደ ዝናብ መቀየር  ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር Cloud seeding በደመና ውስጥ እርጥበትን በመፍጠር ዝናብ ለማግኜት የሚደረግ  ሰው ሰራሽ  የአየር ሁኔታ ማሻሻያ ነው።ይህ ዘዴ በተበታተኑ የደመና ቅንጣቶች ላይ  «ሲልበር  አዮዳይድ»እና « ፖታሼም ክሎራይድ»ን የመሳሰሉ  ንጥረ ነገሮችን  ወደ ከባቢ አየር በመበተን ደመናን ወደ በረዶ ከዚያም ወደ ዝናብ የመለወጥ  ሂደት ነው።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜትርዮሎጅ ኤጀንሲ የአየር ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታምሩ ከበደ እንደሚገልፁት ደመናን ወደ ዝናብ ለመቀየር የሚደረገው የንጥረ ነገር ርጭትም አውሮፕላንን በመጠቀም አልያም መሬት ላይ በሚተኮሱ መሳሪያዎች አማካኝነት በሁለት መንገድ  የሚከናወን ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ  ቴክኖሎጂ ከ10 እስከ 15 በመቶ የዝናብ መጠንን ከፍ ሊያደርግ ይችላል።ያም ሆኖ ይህ ዘዴ በተፈጥሮ የሚገኝ ደመናን የሚፈልግ ነው።ያ ካልሆነ  ግን ደመና የመፍጠርም ይሁን ዝናብ የማመንጨት  አቅም የለውም።

Bildergalerie: Waldbrände in Indonesien
ምስል picture-alliance/AP/F. Chaniago

በጎርጎሪያኑ 18 91 ሊዊስ ጋትማን የተባሉ የሳይንስ ሊቅ ፈሳሽ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን ደመና ላይ በመርጨት ዝናብ ማግኘት ይቻላል የሚል ፅንሰ-ሃሳብ ያፈለቁ ሲሆን፤ ኢርቪንግ ላንግሙየር የተባሉ አሜሪካዊው የኖቬል ተሸላሚ  የሳይንስ ሊቅ ይህንን ንድፈ ሃሳብ በቤተ ሙከራ ውስጥ በጎርጎሪያኑ 1946 አረጋግጠዋል።
 ይህ ቴክኖሎጅ   በ1948 በኒው ዮርክ  የተጀመረ ሲሆን፤ በ 2008 ቤጂንግ በተካሄደው ኦሎምፒክ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓትም  ዝናብን ለመከላከል ይህንን ቴክኖሎጅ መጠቀሟ ይነገራል።
እንደ ዓለም አቀፉ የአየር ትንበያ ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም ላይ ከ50 በላይ ሀገራት ይህንን ቴክኖሎጅ ተጠቅመዋል።በ2013 ዓ/ም ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ተጠቃሚ አፍሪቃዊት ሀገር ሆናለች።ቴክኖሎጅው የሚያደርሰው ተፅዕኖና ጉዳት ግን በተመራማሪዎች ዘንድ አሁንም ድረስ  አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል።

የዩሪ ጋጋሪን  የጠፈር ጉዞ  60ኛ ዓመት 
በጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 12 ቀን 1961 ዓ/ም የሩሲያው ጠፈርተኛ ዩሪ አሌክሲይቪች ጋጋሪን «ቫስቶክ 1» በተባለች ሮኬት ወደ ጠፈር በመጓዝ ምድርን የዞረ የመጀመሪያው ሰው በመሆን ታሪክ ሰርቷል። ይህ የጋጋሪን ታሪካዊ ጉዞ 108 ደቂቃዎችን የፈጀ ሲሆን ያለፈው ሚያዚያ ወር 2013 ዓ/ም  60ኛ አመቱን ደፍኗል።፤ከስድስት አሥርተ ዓመታት በፊት ዩሪጋጋሪን በሞስኮ ቀዩ አደባባይ የተቀበሉት ሩሲያውያንም ለዩሪ ጋጋሪ  ክብር ከካርቶን እና ከፕላስቲክ  የተሰሩ ሮኬቶችን ወደ ሰማይ በመተኮስ  በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የጠፈርተኛው ቀን ዘክረዋል።
የጋጋሪን ስኬት ሶቬት ህብረት የህዋ ምርምር  ዕውቀትን ለማሳደግ ከአሜሪካ ጋር ለነበረው ውድድር ወሳኝ ምዕራፍ ቢሆንም፤ ሰርጌ ኒኪታ ኩሩሾፍ  እንደሚሉት ተልዕኮው ሙሉ በሙሉ በታቀደው መንገድ የሄደ ባለመሆኑ ጉዞው ሊሰናከል ይችላል የሚል ስጋት ነበር።ያም ሆኖ  «ቮስቶክ -1» መንኮራኩር  ጋጋሪን ይዛ በሰላም ወደ ምድር ተመለሰች።የደረሰው ግን እንዲያርፍ  ከተወሰነለት ቦታ ርቆ በሩሲያ ሳራቶቭ ክልል  አንዲት አሮጊትና የልጅ ልጃቸው  ድንች በሚቆፍሩበት አንድ ማሳ ላይ ነበር።

Russland Tag der Kosmonauten | 60 Jahre bemannte Raumfahrt
ምስል Vladimir Gerdo/TASS/dpa/picture alliance

በ34 ዓመቱ በ1968 ዓ/ም  የሚሰለጥንበት የተዋጊ ጀት በመከስከሱ  ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ጋጋሪን፤ወደ ህዋ በመጓዝ ዛሬም ድረስ የዘለቀውን የሶቪዬት ህብረት የጠፈር ምርምር ልዕለ ኃያልነት ሚና አጠናከሯል።ተመራማሪዎች እንደሚሉት ንድፈ ሀሳብን  ወደ ተግባር በመለወጥ ለህዋ ሳይንስ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
የምስራቅና የምዕራቡ ፍጥጫ እና የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት መደብዘዝ ተከትሎ በዘርፉ የነበረው ፉክክር ከ1980 ዎቹ መገባደጃ ጀምሮ ወደ ትብብር አድጓል።ከዩሪ ጋጋሪን የመጀመሪያው ታሪካዊ የጠፈር ጉዞ በኋላ ወደ ህዋ  የሚደረጉ የጠፈር ጉዞዎችም መደበኛ ሆነዋል። ያም ሆኖ የጠፈር ምርምር የሀገራት  የኃይልና የክብር ማሳያ መሆኑ  አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው።
«ሜሴንጀር አር.ኤን ኤ»ቴክኖሎጅና  የመከላከያ ክትባቶች
የኮቪድ-19 በሽታ ከተከሰተ ወዲህ ተመራማሪዎች «ሜሰንጀር ሪቦ ኒዩክሊክ አሲድ»  በምህፃሩ« ኤም አር ኤን ኤ»በተባለው ቴክኖሎጅ ከ32 በላይ  የመከላከያ ክትባቶች ወደ ሦስተኛ ደረጃ  ሙከራዎች እንዲደርሱ አድርገዋል። ስምንት የሚሆኑት ደግሞ ማረጋገጫ አግኝተው  እንዲመረቱ ተደርጓል። ሌሎች 90 ክትባቶች ደግሞ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ  ሙከራ ላይ  ይገኛሉ ፡፡ 
ከዚህ የተነሳ ይህ  ቴክኖሎጂ፤  በአሁኑ ወቅት ለበርካታ በሽታዎች የመከላከያ ክትባትን ለማግኘት ይረዳል የሚል እምነት እያሳደረ መጥቷል። ከዚህ  በመነሳትም ሊቃውንቱ በዚህ ቴክኖሎጅ የካንሰር ፣ የወባ በሽታ እና  የኤች አይ ቪ ኤድስ ክትባትን ለማግኘት ሰፊ ተስፋ ሰጭ ምርምሮች እያካሄዱ  መሆናቸውን  ገልፀዋል።

Biontech
ምስል Boris Roessler/dpa/picture alliance

ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ  ቴክኖሎጂ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያንን ዋና ዋና ክፍሎችን የያዙ ሰው ሰራሽ ዘረመሎችን ወደ ሰዎች ህዋሳት በመላክ የሰውነት የተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅም ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው። 
በዚህ ቴክኖሎጅ የሚመረት ክትባት ወደ ማዕከላዊ የህዋስ ክፍል ወይም «ኒዩክለስ» ውስጥ ዘልቆ ሳይገባ «ሳይቶፕላዝም» በተባለው ፈሳሽ የህዋስ ክፍል ላይ ፀረ-ባዕድ አካላት የሆኑ ፕሮቲኖች እንዲመረት  ትዕዛዝ የሚሰጥ  ነው።ዓላማዉም  የሰውነትን የመከላከያ አቅም በማነቃቃት በሽታውን ቀድሞ መከላከል ነው።
የመከላከያ ክትባቱን በቀላሉ በማምረት በብዛት ለማዳረስ የሚመች መሆኑ ደግሞ ቴክኖሎጅውን  ለየት ያደርገዋል ተብሏል።
«ሜሰንጀር ሪቦ ኒዩክሊክ አሲድ»  በምህፃሩ« ኤም አር ኤን ኤ» በጎርጎሪያኑ 1990 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአይጦች ላይ  የተሞከረ ቴክኖሎጅ ሲሆን፤በዚህ ሙከራ  ህይወት ባለው ህዋስ ውስጥ ዘረ-መላዊ መረጃ በማስተላለፍ  ተከላካይ ፕሮቲን እንዲመረት ማድረግ እንደሚቻል ፍንጭ ተገኝቷል።ሙከራው በዘጠናዎቹ የቀጠለ ሲሆን፤በ2005 ዓ/ም  የተሻለ ሙከራና ውጤት በማሳየቴ የሲካ ተዋህሲን፣የዕብድ ውሻ በሽታና እንፍሉዌንዛን በመሳሰሉት በሽታዎች ላይ ሲሞከር ቆይቷል።የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ደግሞ በታህሳስ 2020 ዓ/ም የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለማበልፀለግ ውሏል። 
በክትባቱ ዘርፍ ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ግዙፉ የአሜሪካ የክትባት አምራች  ኩባንያ ሞደርና በሁለት የኤች.አይ.ቪ ክትባቶች ላይ ምርምር እያደረገ  ነው ፡፡ የመጀመሪያው  «ኤም አር ኤን ኤ- 1644» ተብሎ የሚጠራው ዕጩ ክትባት  በጎርጎሪያኑ 2021 መጨረሻ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራዎችን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
መቀመጫውን ጀርመን ያደረገዉ የባዮንቴክ የምርምር ቡድንም በዚሁ ቴክኖሎጅ ላይ ተመስርቶ በጎርጎሪያኑ 2022 መጨረሻ የወባ መከላከያ ክትባትን  በሰዎች ላይ ለመሞከር  ማቀዱንም ይፋ አድርጓል። 
እነዚህ  የክትባት ምርምሮች   እንደታሰበው ከተሳኩ የበርካታ  ሰዎችን  ህይወት ይታደጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ