የ DW ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ጉብኝት
የ DW ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ጉብኝት
ሸገር ኤፍ ኤም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የጀመሩት ማሻሻያ አንድ ዓመት ከሆነው በኋላ DW ኢትዮጵያ ውስጥ እንቅስቃሴውን ይበልጥ በማስፋፋት ላይ ነው። የ DW ዋና ዳይሬክተር ፔተር ሊምቡርግ መቶ ሚሊየን ሕዝብ ባለባት የምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከተለያዩ የራዲዮ የኤፍ ኤም ጣቢያዉች ጋር የትብብር ውሎችን ተፈራርመዋል። ከነዚህም ዉስጥ ሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮ አንዱ ነዉ።
የትብብር ዉሎች
ከተጓዳኞች መካከል ሸገር ኤፍ ኤም፤ አሃዱ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን፤ ኢትዮ ኤፍ ኤም እና አፍሮ ኤፍ ኤም ይገኙበታል። የሸገር ኤፍ ኤም ባለቤት አቶ አበበ ባልቻ እና የ DW ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ ትብብሩን በተፈራረሙበት ወቅት የሸገር ኤፍ ኤም ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ «ዶይቼ ቬለ በሚያቀርባቸው ሚዛናዊ እና ጠንካራ ዘገባዎች የተከበረ ነው።» ስትል ተናግራለች።
ኢትዮ ኤፍ ኤም እና አሃዱ ራዲዮ
የኢትዮ ኤፍ ኤም ሥራ አስኪያጅ ሰይፉ ፋንታሁን በበኩሉ «በተለይ የመረጃዎች አጠራጣሪነት ሲከሰት DW ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ነው።» ብሎአል። በኢትዮ ኤፍ ኤም እና በአሃዱ ራዲዮ የ DW ተወዳጅ ዝግጅቶች ዳግም መሰራጨት ጀምረዋል። በዚያም ላይ በተደረገው የትብብር ስምምነት መሠረት የፌስቡክ እና የመጀመሪያው የቴሌቪዥን የቅብብል ስርጭት ይፋ ተደርጓል።
DW የተሰጠዉ ከፍተኛ ቦታ እኛን አኩርቶናል
የ DW ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሊምቡርግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የ «DW» ዘጋቢዎች ጋር ስብሰባ ባካሄዱበት ወቅትም «ለዶይቼ ቬለ እዚህ የሚሰጠው ከፍተኛ ስፍራ እኛን አኩርቶናል።» ብለዋል። «በጠንካራ እና ሚዛናዊ አዘጋገብም የዚህ አስቸጋሪ የለውጥ ሂደት ተጓዳኝ መሆን እንፈልጋለን» ሲሉም አክለዋል።
የልምድ ልዉዉጥ
DW የሀገር ውስጥ ዘጋቢዎቹን ቁጥር ከሁለት ወደ ስምንት ከፍ አድርጓል። ከዓመታት ጥረት በኋላ አዲሱ መንግሥት ለአማርኛው አገልግሎት ለስድስት ዘጋቢዎች ፈቃድ ሰጥቷል። ይህም DW አሁን በጎሳ ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን አስመልክቶ ተከታታይ ዘገባዎች ለማቅረብ አስችሎታል። አዲሶቹ ዘጋቢዎች ስማርት ስልኮችን ተጠቅመው የቪዲዮ ዘገባዎችን የሚያጠናቅሩበት የአጭር ጊዜ ስልጠና እንዲያገኙ በመደረጉም በምስል የተደገፉ ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው። በቅርቡ የተከሰከሰውን የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ገጠመኝ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
DW አካዳሚ የጋዜጠኝነት ስልጠና ተጠይቆአል
አዳዲሶቹ አጋር የመገናኛ ብዙሃንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከ DW አካዳሚ የስልጠና ድጋፍ ጠይቀዋል። የDW አካዳሚ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ለኢትዮጵያ አዲስ መርሃግብር ይፋ ያደርጋል።
ዉይይት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ
ከፍተኛ አመራሮች ያካተተው የ DW ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ኹኔታ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን እና የሲቪክ ማኅበራት መሪዎች ጋር ተወያዩ። ውይይቱን ያዘጋጁት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫግነር ናቸው። በዉይይቱ የአማራጭ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ የትነበርሽ ንጉሴ፣ የሶል ሪቤልስ መስራቿ ቤተልሔም ጥላሁን፣ ጦማሪ እና የሰብዓዊ መብት አቀንቃኙ በፍቃዱ ኃይሉ ተገኝተዋል።
ዉይይት ስለሽግግር ሂደቱ መሰናክሎች
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫግነር ባዘጋጁት የክብ ጠረጴዛ ውይይት ኢትዮጵያን የወከሉት ወገኖች ስለሽግግር ሂደቱ መሰናክሎች፣ ስለመረጃዎች መዛባት እና ተጠያቂነት ስለመጥፋቱ አንስተዋል። የሕግ ባለሙያ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የአማራጭ ኖቤል ተሸላሚዋ የትነበርሽ ንጉሤ፣ የ42 ዓመቱ የለውጥ አራማጁ ዐቢይ ኢትዮጵያን ለአስርት ዓመታት ከተቀፈደደችበት አገዛዝ «ወደ ፍቅር አገዛዝ » አምጥተዋታል ብላለች።
የጎንደር ጉብኝት
የ DW ከፍተኛ አመራሮች በጎንደር ጉብኝት አድርገዋል። ከልዑካኑ መካከል የDW ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ሉምቡርግ፣ የአፍሪካ ክፍል ተጠሪ ክላውስ ሽቴከርና የአማርኛዉ ክፍል ተጠሪ ሉድገር ሻዶምስኪ ይገኙበታል።
የሽኝት ስነ-ስርዓት በአዲስ አበባ
በስነ ስርዓቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተጀመረዉን የለዉጥ ሒደት የሐገሪቱ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በትክክል እንዲረዳዉ አዲሱ መንግሥት ለጋዜጠኞች በሩን እንዲከፍትና መረጃ እንዲሰጥ የ DW ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጠይቀዋል።ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔተር ሊምቡርግ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሦስት ቀን ጉብኝት ሲያጠናቅቁ እንደተናገሩት በጉኝታቸዉ ወቅት ባዩትና ከተለያዩ ወገኖች ጋር ባደረጉት ዉይይት በሐገሪቱ ያለዉን ሁኔታ ተገንዘበዋል። ኢትዮጵያን በማየታቸዉም ደስተኛ ናቸዉ።
ፒተር ሊምቡርግ እና የ DW ዘጋቢዎች
ለበርካታ አስርት ዓመታት በአጭር ሞገድ ብቻ ይሰራጭ የነበረው የአማርኛው ፕሮግራም በቀደመው የመንግሥት አስተዳደር ስልታዊ በሆነ መንገድ በመታፈን ሲደናቀፍ ነበር። በኢትዮ ኤፍ ኤም እና በአሃዱ ራዲዮ የDW ተወዳጅ ዝግጅቶች ዳግም መሰራጨት ጀምረዋል። ፒተር ሊምቡርግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የዲ ደብልዩ ዘጋቢዎች ጋር ስብሰባ ባካሄዱበት ወቅትም «ለዶይቼ ቬለ እዚህ የሚሰጠው ከፍተኛ ስፍራ እኛን አኩርቶናል።» ብለዋል። «በጠንካራ እና ሚዛናዊ አዘጋገብም የዚህ አስቸጋሪ የለውጥ ሂደት ተጓዳኝ መሆን እንፈልጋለን» ሲሉም አክለዋል።