1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕረስ ነፃነት በአፍሪቃ ቀንድ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 26 2004

የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን በየዓመቱ እንደሚሆነዉ ሁሉ የዘንድሮዉ ዛሬ በመላዉ ዓለም ታስቦ ዉሏል።የተለያዩ የፕረስ ነፃነትና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዕለቱን ምክንያት አድርገዉ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት በአንዳንድ የአረብ ሐገራት አምና-

https://p.dw.com/p/14p6J
ምስል dapd

የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን በየዓመቱ እንደሚሆነዉ ሁሉ የዘንድሮዉ ዛሬ በመላዉ ዓለም ታስቦ ዉሏል።የተለያዩ የፕረስ ነፃነትና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዕለቱን ምክንያት አድርገዉ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት በአንዳንድ የአረብ ሐገራት አምና-ዘንድሮ የተደረጉት ፖለቲካዊ ለዉጦች ለፕረስ ነፃነት መሻሻል አስተዋፅኦ አድርገዋል ። በአጠቃላይ በዓለም ላይ ያለዉ የፕረስ ነፃነት ሁኔታ ግን ብዙም ለዉጥ አልታየበትም ። ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘዉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት እንደሚለዉ ደግሞ በአፍሪቃ ቀንድ የፕረስ ነፃነት ዘንድሮ ይበልጥ እየተደፈለቀ፥ ጋዜጠኞችም እንደታሰሩ ነዉ ። ነጋሽ መሐመድ የድርጅቱን የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ አምብሯዝ ፕየርን አነጋግሮ ያጠናቀረዉ ዘገባ አለዉ።
የአፍሪቃ ሕብረት፥ የኢትዮጵያ፥ የኬንያ እና የሽግር መንግሥቷ ጦር በጠላቶቻቸዉ ላይ የተቀዳጁት ድል-የሚተረክ፥ የሚነገርባት ሐገር ዘንድሮም፥እንዳምና ሐቻምናዉ ለጋዜጠኞች ከአፍሪቃ እጅግ አደገኛዋ ሐገር ናት።ሶማሊያ።
አምብሯዝ ፕየር፣-አለመታደል ይሉታል።

Symbolbild Medienfreiheit
ምስል Fotolia/wellphoto
---
Presseausweis Symbolbild
ምስል Fotolia


ድምፅ
«እንዳለ መታደል ሆኖ ሶማሊያ የሚፈፀመዉ የአመፅ-ጥቃት ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ አላሳየም። ሶማሊያ ከአፍሪቃ በርካታ ጋዜጠኞች የሚገደሉባት ሐገር ናት።በሁለት ሺሕ-አስራ ሁለት እስካሁን ድረስ ብቻ አራት ጋዜጠኞች ሆን ተብሎ ተገድለዋል።ጋዜጠኞች ሆን ተብሎ ባይገደሉ እንኳን በየሥፍራዉ የሚደርሱ የቦምብ ጥቃቶች ሰለቦች ናቸዉ።»

ፔሪ መጋቢት ማብቂያ ርዕሠ-ከተማ መቃዲሾ ትያትር ዉስጥ የተጣለዉን የቦምብ አደጋ ምሳሌ ያደርጉታል።ባለሥልጣናትን አጥፍቶ ለማጥፋት ያለመችዉ ወጣት ያፈነዳችዉ ቦምብ እዚያ አዳራሽ ዉስጥ ሥለነበረዉ ድግስ ለመዘገብ የተሰበሰቡ ጋዜጠኞችንም አልማረም።

እና ሶማሊያ ብዙ ጋዜጠኞችን በማስገደል ከአፍሪቃ አንደኛ ናት።ብዙ ጋዜጠኞችን በማሰርም ከዓለም የአንደኝነቱን ደረጃ ሌላዋ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገር ይዛዋለች ። ኤርትራ።ከሰሜን ኮሪያም የባሰች ይሏታል-ፕየር።
ድምፅ
«ኤርትራ ለጋዜጠኞች በጣም መጥፎ ሥፍራ ናት ። ኤርትራ የግሉ ፕረስ ከአሥር-አመት በፊት የተዘጋባት ዝግ-ሐገር ናት ። ባሁኑ ወቅት ከሰላሳ-በላይ ጋዜጠኞች እንደታሰሩ ነዉ።»


ፔሪ እንዳሉት አንዳዶቹ ከታሠሩ አስራ-አንደኛ አመታቸዉን ይዘዋል ። ገሚሶቹ የታሠሩት ከስድስት ዓመት በፊት ነዉ።የዛሬ ሰወስት አመት ግድም የታሰሩም አሉ ። በዚሕም ብሎ በዚያ አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት እንደሚለዉ የኤርትራ መንግሥት የሚወስደዉ እርምጃ ያቺኝ ሐገር ለጋዜጠኞች በጣም መጥፎ አድርጓታል።
ድምፅ
«ይሕ ሁኔታ (ለጋዜጠኞች) በጣም መጥፎ ነዉ።ከሰሜን ኮሪያ እንኳን የከፋ ነዉ።»

የፕረስ ነፃነት፥ በድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ጥናት መሠረት ከመሻሻል ይልቅ የዘቀጠባት ሰወስተኛዋ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገር ኢትዮጵያ ናት ። እርግጥ ነዉ አምብሯስ ፕየር እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከሶማሊያና ከኤርትራ ጋር ሲነፃፀር ሰዎች እራሳቸዉን በነፃነት የሚገልፁባት፥ አንዳዴም መንግሥትን ጠንከር አድርገዉ የሚተቹ የግል ጋዜጦች የሚታተሙባት ሐገር ናት።

ካለፈዉ ዓመት (ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር) ወዲሕ ግን ፕየር እንዳሉት ይሕ የፕረስ ነፃነት በጣም አሽቆልቁሏል።ምክንያት፥-

ድምፅ
«ምክንያቱ በ2009 የፀደቀዉ የፀረ-ሽብር ሕግ ነዉ።ይሕ ሕግ ሐሳብን በመግልፅ ነፃነት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።ጋዜጠኛ ሆነሕ ሥለ ኦጋዴን አማፂያን ወይም ዉጪ፥ ለምሳሌ ዩናትድ ዉስጥ ሥለሚገኙ ተቃዋሚ ቡድናት የምትዘግብ ከሆነ ይሕን ማድረግ አትችልም። ምክንያቱም ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት አለሕ በሚል ትወነጀላለሕ።በሁለት የዉጪ ጋዜጠኞች (በስዊድኖች) ና በተወሰኑ ኢትዮጵያዉን ጋዜጠኞች ላይ የደረሰዉም ይኸዉ ነዉ።(የተወነጀሉት) ሥራቸዉን በመስራታቸዉ ነዉ።»

ነጋሽ መሃመድ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ