1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፑቲን መመረጥና ፖለቲካዊ መርሕ

ሰኞ፣ የካቲት 26 2004

አያታቸዉን እየተከተሉ አልፎ፥ አልፎ ሥታሊን ወደነበሩበት ሥፍራ በቅ ይሉ ነበር-እንጂ የሌኒን፥የስታሊንን መርሕ እርምጃ በቅርብ ለመቅሰም የሚችሉበት እድሜም አጋጣሚም አልነበረም።የኬጂቢ ባልደረባ ነበሩ እንጂ የብሬዥኔቭን ፖለቲካዊ ሥልት መከተላቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

https://p.dw.com/p/14FRs
Die Bilder hat unser Korrespondent in St-Petersburg Wladimir Isotow gemacht. Die Rechte wurden an DW durch den Autor und die abgebildete Person(en) übertragen. Zulieferer: Yuliya Siatkova Beschreibung: Präsidentschaftskandidaten - ein großer Plakat im Wahllokal von der Stadt Wsewoloschsk/Vsevolozhsk Schlagworte: Wahlen, Russland, Putin, St-Petersburg, Wahlkampagne, Betrug, Präsidentschaftswahlen, Wsewoloschsk, Vsevolozhsk Jahr/Ort: 2012/Russland
እጩዎቹምስል DW

ፕሬዚዳንት በሪስ የልትሲን እያረቁ እንደ ሾሟቸዉ መርተዉ፥ እየጠረጠሩ ሥልጣናቸዉን አወረሷቸዉ።ታሕሳስ 1999 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)። የሩሲያ ሕዝብ ብዙም ሳያዉቃቸዉ የወረሱትን ሥልጣን በብዙ ድምፅ አፀደቀላቸዉ።ግንቦት ሁለት ሺሕ።በሳል ሰላይ፣ ጠንካራ ጂዶኛ ናቸዉ።ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን። እንደ በሳል ሠላይ፥ የሩቅ ዓላማ ስሜታቸዉን ደብቀዉ፣እንደ ጂዶዉ፣ በፖለቲካዉ ተገለባብጠዉ ክሬምሊንን ባደራ ካስረከቧቸዉ እንደሚረከቡ ትናንት አረጋገጡ።

«እንደምናሸንፍ ቃል ገብቼ ላችሁ ነበር።አሁን አሸነፍን።----

የዕሁዱ ምርጫ መነሻ፥ የፑቲን ፖለቲካዊ መርሕ እና ተቃዉሞዉ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።ታይም የተሰኘዉ የአሜሪካ ሳምንታዊ መፅሔት ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲንን «የዓመቱ ምርጥ ሰዉ ብሎ የሰየማቸዉ» ፑቲን በዉርስም፥ በምርጫም ብለዉ ስምንት አመት የቆዩበትን ሥልጣን ለማስረከብ ጠረጴዛቸዉን ሲጠራርጉ፥ የሞስኮና የለንደን፥ በለንደን በኩልም የሞስኮና የዋሽግተን፥ ዋሽግተኖች የሚመሩት ዓለም ግንኙነት በአንድ ሰላይ ግድያ ሰበብ በደፈራረሰበት ወቅት ነበር።ታሕሳስ ሁለት ሺሕ ሰባት።

ሐገሩን ከድቶ ብሪታንያ ተሸሸጎ የነበረዉ የቀድሞዉ የሩሲያ የስለላ ድርጅት ባልደረባ አሌክሳንደር ሊትቪኔንኮ በሁለት ሺሕ ስድስት ማብቂያ ለንደን ዉስጥ በመርዝ ተገደለ።መሸሸጊያ የሰጠችዉ ምናልባትም በመንታ ሰላይነት ያገለግላት የነበረዉ ሰላይ ርዕሠ-ከተማዋ ዉስጥ መገደሉ ለብሪታንያ በርግጥ ታላቅ ሐፍረት ነበር።አስገዳዮች የክርምሊን ባለሥልጣናት እንደሆኑ የርግጠኝነት ያሕል የጠረጡት የዳዉኒንግ ስትሪት ባለሥልጣናት ሞስኮዎች ዋናዉን ተጠርጣሪ አንድሬይ ሉጎቮይን አሳልፈዉ እንዲሰጧቸዉ ጠየቁ።

ሞስኮዎች ባንፃሩ በከዳ ሰላያቸዉ በአሰገዳይነት መጠርተራቸዉ አልበቃ ብሎ ታማኝ ሰላያቸዉን አሳልፈዉ እንዲሰጡ መጠየቃቸዉ ክብርነክ አድርገዉ ነበር ያዩት።የያኔዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራዉን በሞስኮዎች ክሕደትና እንቢተኝነት የጋመዉን የብሪታንያ ፖለቲከኞችን ስሜት ለማስተፈንስ በለንደን የሩሲያ ኤምባሲ ባልደረቦች የነበሩ አራት ዲፕሎማቶችን ከሐገራቸዉ አባረሩ።ሐምሌ 2007።አደረጉት።

ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን የብሪታንያ ዲፕሎማቶች ለማባረር አፀፋዉ አልዘገዩም፥አላመነቱምም። የለንደንና የሞስኮ አዲስ ዉዝግብ ወትሮም ከኢራቅ ወረራ እስከ ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር፥ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋት፥ እስከ ፀረ-ሚሳዬል-ሚሳዬል ተከላ፥ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ፥ እስከ ጋስ ዝዉዉር በሚደርስ በበርካታ ልዩነት ሰበብ ብዙ ጊዜ ዉስጥ ዉስጡን አልፎ፥ አልፎ ባደባባይ ሲናኮሩ የቆዩትን የሩሲያና የምዕራባዉያን ሐገራት ልዩነትን ለማስፋት ከበቂ በላይ ነበር።

የምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎች፣ ተቋማት፣ ተንታኞችና በምዕራባዉያኑ ይደገፋሉ የሚባሉ የሩሲያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ፑቲኒን በመብት ረጋጭነት፣ «በድንበር ዘለል» አስገዳይነት በሚያብጠለጥሉበት በዚያ ሰሞን እዉቁ የምዕራብ መፅሔት ታይም ለፑቲን የምርጥ ሰዉነት ክብር፥ ማዕረግ መስጠቱ እሳቸዉን ለተጨማሪ ዉግዘት፣ መፅሔቱንም ለሰላ ትችት ነበር የዳረገዉ።

ፑቲኒን ያኔም-አሁንም ከረር መረር አድርገዉ የሚተቹ፥ የሚያወግዙ ወገኖች በሙሉ ያሉትን የማለታቸዉን ያክል ሰዉዬዉ የሩሲያን አንድነት ማስጠበቅ፥ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ማሳደግ፥ የሕዝባቸዉ ኑሮ መለወጣቸዉን የሚያጣጥሉበት አንድም ሰበብ የላቸዉም። ፑቲን «የአመቱ ምርጥ ሰዉ» በተባሉ ሰሞን የተጠናከሩት ብዙዎቹ ተቺዎቻቸዉ እንደ ንጉስ ኢቫን አራተኛ (ኢቫን ጨካኙም ይባላሉ) እንደ ስታሊን እንደ ብሬዥኔቭ ከሰሩት ጥሩ ይልቅ የፈፀሙት ክፋት-ጭካኔ የሚያልባቸዉ መሪ ያደርጋቸዋል።

በእሁዱ ምርጫ ከተፎካከሯቸዉ አንዱ የረጅም ጊዜ ተቃዋሚዉ፥ የኮሚንስቱ ፓርቲ መሪ ቭላድሚር ዠርኖቭስኪ ከፑቲን አመራር ጥሩነት ይልቅ መጥፏቸዉ ያይላል ብሎ-ዉግዘትን በቀደም ደገሙት።«እዚሕ እኛ ዘንድ በርግጥ ቀላል አይደለም።ላለፉት አስራ-ሰወስት አመታት ሥልጣን ላይ ናቸዉ፥ ከ1999 ጀምሮ።ምናልባት ላንዳዶቹ ዉድቀቶች እሳቸዉ በግል ተጠያቂ አይሆኑ ይሆናል።የአስራ-ሰወስት ዘመን አመራራቸዉ ዉጤት መጥፎነቱ ግን ግልፅ ነዉ።»

ለደጋፊዎቻቸዉ ግን ሰዉዬዉ የዘመኑ ታላቁ ፔተር (ጴጥሮስ) ወይም ሌኒን ናቸዉ።

በሪስ የልትሲን ፑቲንን ያገኙት የሐገር፥ መንግሥታቸዉን የቁልቁሊት ሩጫ፥ ኪሳራ፥ ዝቅጠት፥ የቼቺያንያዉን ጦርነት ሽንፈት የሚገታላቸዉ ረዳት ፍለጋ በስምንት አመት ጊዜ አምስት ጠቅላይ ሚንስትር እየሾሙ፥ ሲሽሩ ቆይተዉ ነበር።1999።

የልትሲን ነሐሴ ማብቂያ 1999 በጠቅላይ ሚንስትርነት እስከ ሾማቸዉ ድረስ ሰላይነታቸዉን እንጂ፥ ፖለቲከኝነታቸዉ ለተቃዋሚዎቻቸዉ ቀርቶ ለየሊሲን ለራሳቸዉም ብዙም አይታወቅም ነበር። በአብዛኛዉ ሩሲያዊ ዘንድ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትርነት ከተሾሙም በሕዋላ ከሳቸዉ በፊት እንደ ተፈራረቁት አምስት ሰዎች በወራት ግፋ ቢል በአመት እድሜ የሚባረሩ ከመባል ባለፍ ምንም ነበሩ።

ፑቲን በተቃራኒዉ ከሩቅ የሚያዉቋቸዉን መሪ-ወዳጆቻቸዉን፥ ምንም የማያዉቃቸዉን ሕዝባቸዉን ጠንቅቀዉ ያዉቁ ወይም የሚያዉቁ መስለዉ ነበር።የሿሚቸዉን ልብ፥ የሕዝባቸዉን ቀልብ ለመሳብ ደግሞ በተቃራኒዉ የተቃዋሚዎቻቸዉን ድክመት ለማጋለጥ ቼችችንያ ላይ የድል ነጋሪት የማስጎሰምን ያክል ቀዳሚ ስልት እንደሌለ አላጡትም።ስለላን-ከፕሮፓጋንዳ፥ፖለቲካን ከጦር መሪነት፥ ጭካኔን-ከአብላሎ ገዢነት ባሰባጠረ ብልሐት፥ አሞሌን-ከዱላ በቀየጠ ስልት የቼችንያን ደፈጣ ተዋጊዎች ከፋፍለዉ-አጥፍተዉ ሥልጣን በያዙ በወራት እድሜ ግሮዝኔን ለጠላቶቻቸዉ ሐፍረት፥ ለወዳጆቻቸዉ ኩረት ግሮዝኔን ለክሬምሊን አስረከቡ።

የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት የመጨረሻ መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭ ከእሁዱ ምርጫ በፊት እንዳሉት ቭላድሚር ፑቲን ዳግም መራጭ ማግኘታቸዉ አጠራጣሪ ነበር።በጎ ምግባራቸዉ ግን በጎርቫቾቭ እምነት አይካድም።

«በድጋሚ ይመረጣሉ ብዬ አላስብም።እርግጥ ነዉ በጣም ጥሩ ነገሮችን አከናዉኗል።አሁን ግን ሁኔታዉ እንደሚያመለክተዉ የእሳቸዉ ጊዜ አልፏል።»

ራሳቸዉ ጎርቫቾዉ እንደ ሐገራቸዉ ሁሉ በታትነዉ፥ ለየልትሲን ያስረከቡትን ምጣኔ ሐብት በየልሲን ዘመን ጨርሶ ከትቢያ ተቀይጦ የነፔተር፥ የኔ ዩሪ ጋጋሪ ዉልዶች፥ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ልዕለ ሐያል፥ የነዳጅ ዘይት ቋቲቱ ሐገር ሕዝብ ተመፅዋች እስከመሆን ደርሶ ነበር።የልትሲን ከጎርቫቾቭ ተረክበዉ፥ ለፑቲን ያስረከቧት ሩሲያ በግጭት፥ ጦርነት፥ በወንበዴ፥ ማፍያዎች የተመሰቃቀለች ነበረች።

ቭላድሚር ፑቲን አባብለዉ፥ አስገድለዉም ሆነ አስገድደዉ ሠላም ሉዓላዊነቷን አስከብረዉላታል። ሥልጣን ሲይዙ ሰላሳ በመቶዉ ሩሲያዊ ከድሕነት ጠገግ በታች ነበር።ሥልጣናቸዉን ለዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ሲያስረክቡ ግን የደሐዉ ሕዝብ መጠን ወደ አስራ-አራት በመቶ ወርዷል።ፑቲን ሥልጣን ሲይዙ የመንግሥት ሠራተኛ ዝቅተኛ የወር ደሞዝ ሰማንያ ዶላር ነበር።በሁለት ሺሕ ስምንት ስድስት መቶ አርባ ዶላር አድርሰዉታል።

የሿሚያቸዉን ልብ ማርከዉ ክሬምሊንን የወረሱት፥የተቃዋሚዎቻቸዉን ድክመት አጋልጠዉ፥ በማያዉቃቸዉ ሕዝብ ዘንድ ተወደዉ በዉርስ ያገኙትን ስልጣን በምርጫ ያፀደቁት፥ የቼችንያን ድል፥ ገፀ-በረከት አቅርበዉ ነበር።ጎርቫቾቭ በቅርቡ እንዳሉት ፑቲን በሕዝብ ዘንድ ያላቸዉ ተወዳጅነት መቀነሱን ሲረዱት ደግሞ ከአስራ-ሁለት አመት በፊት አጠፋኋቸዉ ያሏችዉ የቼችንያ አማፂያን ሊገድሉኝ አሲረዉ ነበር አሉ።ወይም አሰኙ።ግን ማን ይፈራል «ሞት።»

«በኔ የሥልጣን ደረጃ ያሉ ሰዎች ከዚሕ ጋር መኖር አለባቸዉ።የግድያ ሙከራዎቹ ከስራዬ አናጥበዉኝ አያዉቁም።ወደፊትም ቢሆን ይሕ አይከሰትም።ከ1999 በዚሕ ሁኔታ ነዉ የምኖረዉ።ምን ምን ይደረጋል።የሚፈራ ሰዉ መኖር አይችልም።እነሱ አሸባሪዎቹ እኛን ይፍሩ-(እንጂ እኛ አንፈራም።)

ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ፑቲን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን አስቀድሞዉ ስላስገለሉ በምርጫዉ እሳቸዉን የሚያስንቅ እጩ አልተወዳደረም።በዚሕም ሰበብ ማሸነፋቸዉ ብዙም አላስገረመም። ተቃዋሚዎቻቸዉ ግን ከወር በፊት የተደረገዉ የምክር ቤት (ዱማ) እንደራሴዎች ምርጫ የትናንቱንም ፕሬዝዳንታዉ ምርጫ ተጨብርብሯል በማለት ይወነጅላሉ።በአደባባይ ሰልፍ ያወገዙም አሉ።

በያብሎኮ የትንታኔ ማዕከል የተሰኘዉ ተቋምም የተቃዋሚዎቹን ወቀሳ-ትችት ይጋራል።በማዕከሉ የፖለቲካ ጉዳይ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ ጋሊና ሚኻኤሎቫ እንደሚሉት ሁለቱም ምርጫዎች በፑቲን ደጋፊዎች ተጭበርብረዋል።

«ምርጫዉን ከመራጭች ሊግ ጋር ሆነን ታዝበናል።ሊጉ ከዱማ ምርጫ በሕዋላ የተመሠረተ አዲስ ገለልተኛ ድርጅት ነዉ።አብዛኞቹ በተቃዉሞ ሠልፉ ይሳተፉ የነበሩ ናቸዉ።እና አዎ፥ ብዙ በጣም የተዛቡ ነገሮች ነበሩ።በዱማዉ ምርጫ ወቅት ከተፈፀመዉ ጋር የሚመሳሰል ማጭበርበር ነበር።የመምረጥ መብት ያልተሰጣቸዉ ሰዎች በአዉቶብሶች እየተጓዙ መጥተዉ ድምፅ በሰጡበት ሞስኮ ዉስጥ ብቻ ሰወስት መቶ የማጭበርበር ጥፋት አይተናል።»

እርግጥ ነዉ ፑቲን ገና በሁለት ሺሕ አጋማሽ ሩሲያ የራስዋ እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ወይም የብሪታንያ ግልባጭ ዲሞክራሲ አያሻትም ብለዉ ነበር።በሳቸዉ በተቀመረዉ የዲሞክራሲ ልክ ተወዳድረዉ በስልሳ-አራት ከመቶ ድምፅ አሸነፉ።በድል ፌስታ አለቀሱ።

«ዉድ ወዳጆቼ! ከሁሉ በፊት ዛሬ በተደረገዉ የሩሲያ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተሳተፈዉን የሩሲያ ሕዝብ በሙሉ ላመሰግን እወዳለሁ።የተከረበረችዋንና ታላቅዋን ሐገራችንን በየመስኩ የደገፉትን ወገኖች በሙሉ አመሰግናለሁ።ለታላቅዋ ሩሲያ አወንታዊ መልስ የሰጣችሁትን በሙሉ አመሰግናለሁ። ከዚሕ ቀደም ማሸነፋችንን ትጠራጠራላችሁ ወይ ብዬ ጠይቄያችሁ ነበር።አሸነፍን።»

ሰዉዬዉ ከእሁዱ ምርጫ-ድልም የደረሱት የሚያወግዝ፣ የሚጠላቸዉ ወገን ብዛት፣ ጥንካሬ፣ በሚወድ፣ በሚደግፋቸዉ ሐይል ፊት እንደኮሰመነ-ነበር።ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ «የነብሱን ስሜት አገኘሁት» በማለት ካወደሷቸዉ ከሁለት ሺሕ አንድ ጀምሮ በየጊዜዉ ያመሰገኑ፣ ያደነቁቸዉን ያክል፣ እንደተቹ፣ እንደወቀሷቸዉ ነዉ ከዋይት ሐዉስ የተሰናበቱት።

ፑቲን መጀመሪያ የሌኒን ኋላ የስታሊን ምግብ አብሳይ የነበሩ አያታቸዉን (ያባታቸዉን አባት) እየተከተሉ አልፎ፥ አልፎ ሥታሊን ወደነበሩበት ሥፍራ በቅ ይሉ ነበር-እንጂ የሌኒን፥የስታሊንን መርሕ እርምጃ በቅርብ ለመቅሰም የሚችሉበት እድሜም አጋጣሚም አልነበረም።በብሬዥኔቭ የመጨረሻ ዘመነ-ሥልጣን በምሥራቅ ጀርመን የእዉቁ የስለላ ድርጅት የኬጂቢ ባልደረባ ኋላም ተጠሪ ነበሩ እንጂ የብሬዥኔቭን ፖለቲካዊ ሥልት መከተላቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

ግን ከእንግዲሕ እድሜና ጤና ከሰጣቸዉ በድሕረ-ዛሪሲት ሩሲያ በስታሊን ተቀድመዉ፥ ብሬዥኔቭን ቀድመዉ ክሬምሊንን ለረጅም ጊዜ በመቆጣጠር የመጀመሪያዉ መሪ ይሆናል።ቭላድሚር፥ ቭላድሚሮቪች ፑቲን።ሐምሳ ዘጠኝ አመታቸዉ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ
























ITAR-TASS: YEKATERINBURG, RUSSIA. An image of presidential candidate Vladimir Putin on a building. (Photo ITAR-TASS / Anton Butsenko)
ፑቲን፦ በተቃዋሚዎቻቸዉ እይታምስል picture-alliance/dpa
Russian Prime Minister and presidential candidate Vladimir Putin, has tears in his eyes as he emotionally reacts at a massive rally of his supporters at Manezh square outside Kremlin, in Moscow, Russia, Sunday, March 4, 2012. Vladimir Putin has claimed victory in Russia's presidential election, which the opposition and independent observers say has been marred by widespread violations. Putin made the claim at a rally of tens of thousands of his supporters just outside the Kremlin, thanking his supporters for helping foil foreign plots aimed to weaken the country. (Foto:Ivan Sekretarev/AP/dapd)
ፑቲን፦ የድል እንባምስል AP
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ