1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣3ኛ ወንጀል ችሎት ብይንና የ A I አስተያየት፤

ዓርብ፣ ጥር 11 2004

ዐቃቤ ህግ ፀረ ሽብር ህግን አስመልክቶ ክስ በመሠረተባቸው 5 ሰዎች ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት፣ በትናንትናው ዕለት ጥፋተኞች ናቸው ሲል መበየኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/13nQU
Logo amnesty international

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች AI ,HRW እና ለጋዜጠኞች ደኅንነት የሚታገለው ድርጅት (CPJ) ውሳኔው አግባብነት የለውም ብለዋል። ተክሌ የኋላ፣ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተመራማሪ ክሌር ቤስተንን አነጋግሮ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

የጥፋተኛነት ብይን የተላለፈባቸውን የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎች፣ የነበሩ ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ባስቸኳይ መልቀቅ ይገባዋል የሚል መግለጫ ነው AI ያቀረበው ። ብይኑን ድርጅቱ እንዴት እንደተመለከተው ክሌር ቤስተን--

«እኛ እንደምናምነው፤ 5ቱም ተካሳሾች፤ የፍርድ ቤት ምርመራ የተካሄደባቸውና የተበየነባቸው ህጋዊ ተግባራቸውን በማከናወንና ሰላማዊ ድርጊቶችን በመፈጸማቸው ነው። እናም እንደኛ እምነት፣ ያላንዳች ቅደመ-ግዴታ፣ ባስቸኳይ መፈታት ይኖርባቸዋል።

3 ወንዶችና 2 ሴቶች፤ ወንጀል ለመሥራታቸው አናዳች ማረጋገጫ የለም። 5 ቱም የታወቁበት ቢኖር ፣ በአሁኑ ጊዜም ሆነ ቀደም ባለው ጊዜ፣ መንግሥትን በመተቸት ነው። በጋዜጠኛነትም ሆነ በተቃውሞ ፓርቲ አባልነት የሆነው ይህ ነው። »

የተከሰሱትን አብዛኞቹን፤ ከመያዛቸው በፊት መንግሥት በጥብቅ ሲከታተላቸው እንደነበረ ይታወቃል። በፍርድ ሂደቱ፣ በተጨማሪ ጉዳይነት እንደማስረጃ የቀረበው፤ በጋዜጠኛነት ሥራቸውና አዲስ አበባ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢ እ ጎ አ፣ በ 2011 መግቢያ አካባቢ «በቃ!» በተሰኘው መፈክር መሠራጨት ሳትኖሩበት አልቀራችሁም ተብለው ነው። በቃ የተሰኘው መፈክር ፤ ህዝቡ በመንግሥት ላይ ተቀውሞ እንዲያነሣ ጥሪ የተላለፈበት ነው ማለት ይቻላል። ይህም ግንቦት 20 ያሁኑ መንግሥት ሥልጣን የጨበጠበት 20ና ዓመት ሲከበር ማለት ነው። ይህ ታዲያ ይላሉ ፣ ክሌር ቤስተን በመቀጠል--

«እንደ ተጨባጭ ማስረጃ ተቆጥሮ ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀረበው፤ የሚያስረዳው ቢኖር፣ በነጻ ሐሳብን የመግለጽ መብት በዚህ የፍርድ ቤት ምርመራ እንደወንጀል መቆጠሩ ነው። መንግሥትን መንቀፍና ህዝብ እንዲቃወም ማሳሰብ እንደወንጀል ሆኗል የተቆጠረው።»

AI እና መሰል ድርጅቶች፤HRW, CPJ, RSF ን የመሳሰሉት ሁሉ «ፍትኅ ተጓደለ፤ ሰብአዊ መብት ተጣሰ» እያሉ በየጊዜው ይሟገታሉ። እዚህ ላይ እርስዎ ፤ ወ/ት ክሌር ቤስተን፤ የብሪታንያ ተወላጅና ዜጋ፤ የአገርዎ መንግሥት፣እንዲሁም የዩናይትድ እስቴትስ መንግሥት ፤ ሁለቱም የአሁኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚደግፉት ዋንኞቹ ናቸው።

ይህ፣ ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ ነው?

«እውነትህን ነው፤ ተስፋ አስቆራጭነት አለበት። የብሪታንያና የዩናይትድ እስቴትስ መንግሥታት፤ እንዲሁም ሌሎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ የሆኑ መንግሥታት የኢትዮጵያን ባለሥልጣናት በጥብቅ የሚደግፉ ናቸው። እነዚህም መንግሥታት፣ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት ይዞታ ዐይተው እንዳላዩ የመሆን ዝንባሌ ነው የሚታይባቸው። A I ሌሎችም በመቀጠል ማድረግ የሚችሉት፤ ድምጻቸውን ከፍ አድረገው ማሰማት ፤ የሚያሳስቡ ሁኔታዎችን በሰነዶች ማሥፈር፤ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ የተጠቀሱትን መንግሥታትም፣ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የጋራ አቋም እንዲለውጡ በተደጋጋሚ መጠየቅ ነው። ጥያቄውን ይበልጥ ባነሣን ቁጥር ከመገናኛ ብዙኀን ጋር መነጋገር እንችላለን። ስለአሳሳቢ ጉዳዮች፣ ስለሰብአዊ መብት ጥሰት በማንሳት!

በእነዚህ አገሮች ያለው ህዝብ መጠየቅ ይጀምራል። መንግሥታቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በብሪታንያ፤ ህዝቡ፣ መንግሥታችን፤ በኢትዮጵያ ስላለው አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ይዞታ ፤አንዳች ጥያቄ ሳያነሳ፣ ሁኔታዎችን ችላ እያለ ለምንድን ነው፤ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ድጋፍ የሚሰጠው በማለት ሊጠይቅ ይችላል።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ