1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፋሽኑ ንጉስ፤ ካርል ላገርፌልድ

ሐሙስ፣ የካቲት 21 2011

በፋሽን ኢንዱስትሪዉ ዓለም ስሙ በገነነዉ በፓሪሱ የሻኔል ፋሽን ልብስ አቅራቢ ድርጅት በዋና አዘጋጅነት ለ 36 ዓመታት ያገለገለዉ፤ የፋሽን ንጉሱ አልያም የፋሽን አባቱ በሚል መጠርያ የሚታወቀዉ ጀርመናዉዊ ካርል ላገርፌልድ ከ 800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኃብት አለዉ ተብሎአል። ድመቱ 125 ሚሊዮን ዶላር ሳትወርስ እንዳልቀረችም ተዘግቦአል።

https://p.dw.com/p/3EGbw
Screenshot Youtube - Karl Lagerfeld mit Katze Choupette
ምስል Youtube/GRAZIA Deutschland

ከፋሽን ሌላ ፤ ጥሩ መጽሐፍን መግዛት ፎቶግራፍ ማንሳት ይወድ ነበር

እድሜህ ስንት ነዉ ተብሎ ሲጠየቅ የዓመታት ቁጥር  ዋጋ የለዉም «አሁንም ወጣት ሙሉ ጉልበት እና አቅም እንዳለኝ የዉስጥ ስሜቴ ይነግረኛል»  ሲል ይናገር እንደነበር  ቃለ መጠይቅ ያደረጉለት ጋዜጠኞች ጽፈዉለታል። ከ4 እና 5 አስርተ ዓመታቶች በላይ ወጣትነት ይሰማኛል ይል የነበረዉ እና በፋሽን ኢንዱስትሪዉ  ስሙ የገነነው ጀርመናዊዉ የዘመናዊ የልብስ ቅድ ባለሞያ «ዲዛይነር » ካርል ላገርፌልድ የካቲት 12፤  በ 85 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም ተለየ መባሉ በተለይ በተለይ በሚያዉቁት ዘንድ በፋሽኑ ዓለም ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮአል። በፋሽን ኢንዱስትሪዉ ዓለም ስሙ በገነነዉ በፓሪሱ የሻኔል ፋሽን ልብስ አቅራቢ ድርጅት በዋና አዘጋጅነት ያገለገለዉ ካር ላገርፌልድ ከጎርጎሮሳዊው 1983 ዓ.ም ጀምሮ በሚመራው በፓሪሱ የሻኔል የልብስ ፋሽን ትርዒት ላይ ከአንድ ወር ወዲህ መታየት ማቆሙ ጤናዉ ተስተጓጉሎ ይሆን? በሚል ብዙ ጥርጣሪዎችን አጭሮ ነበር። የእለቱ የመሰናዶ የታዋቂዉን ጀርመናዊ የሻኔል ፋሽን ልብስ ትርዒት አዘጋጅ የካርላ ላገርፈልድን ሥራና ሕይወት እየቃኘ በምዕራቡ ዓለም በፋሽን ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ተሰማርተዉ የሚገኙ አስተያየታቸዉን ያጋሩንን ኢትዮጵያዉያን ፈሻኞችን እናያለን። 

Kuba Karl Lagerfeld Modesschau in Havanna
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Espinosa

የዘመናዊ የልብስ ቅድ ባለሞያ ዲዛይነር ካርል ላገርፌልድ ባለፈዉ ሰሞን የካቲት 12 ፤ እለት ከዚህ ዓለም በሞት  ሲሰማ በምዕራቡ ዓለም በተለይም የፋሽን ኢንዱስትሪዉ ዓለም ታዋቂ የፊልም ባለሞያዎች ፖለቲከኞች «የፋሽኑ ኢንዱስትሪ ዓለም  ታላቁን የፋሽን ጥበብ ሊቅ አጣ ብለዉለታል»።  ላገርፌልድ ከጎርጎሮሳዊው 1983 ዓ.ም ጀምሮ በሚመራው በፓሪሱ የሻኔል የልብስ ፋሽን ትርዒት ላይ ከአንድ ወር ወዲህ መታየት አቁሞ ነበር። ከፈረንሳዩ ሻኔል በተጨማሪ ላገርፌልድ ለኢጣልያው ፌንዲም ይሰራ ነበር። የራሱንም ካርል ላገርፌልድ የተሰኘ የፋሽን መለያና በራሱ እጅ የተፈሸነ የጫማ የልብስ የሽቶ እና ቦርሳዎች መሸጫ እና ትርኢት ማሳያ ቦታ አለዉ። ላገርፌልድ ነጭ ቀለም የቀባዉን ረዘም ያለ ፀጉሩን በፖኒቴል በማስያዝ እና ከዓይኑ በማይለየው ጥቁር መነጽሩ ይታወሳል።

የፋሽን ንጉሱ የሚል መጠርያ የተሰጠዉ የሻኔል ልብስ ቅድ ዋና ተጠሪ ጀርመናዊዉ ካርል ላገርፌልድ በብሪታንያ ታዋቂ የሆነችዉን ዘፋኝ ሊሊ አለን በልብስ ትርኢት መድረኩ የፈሸናቸዉን ልብሶች አድርጋ እንድትታይ ጋብዞአት ያዉቃል። ሊሊ የካርል ላጋርፌልድን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ስትሰማ ካርል በሚፈሽናቸዉ ልብሶች ልዕልት አድርጎኝ ነበር። ስትል ነበር የገለፀችዉ።

«ካር ላጋርፌልድ በጣም በሚገርም መልኩ ለሁሉም ሰዉ የጥሩ ወደጅ ፀባይ ያለዉና ደግ ሰዉ ነዉ። በጣም ብዙ ፋሽን ልብሶችን እና ቦርሳዎችን ልኮልኝ ልብሶቹን አድርጌ ልክ ልዕልት እንደሆንኩ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎ ነበር። » 

Karl Lagerfeld und Claudia Schiffer
ምስል picture-alliance/dpa/R. Ochlik

ጀርመናዊዉ እዉቅ የፋሽን ልብስ ስራ አዋቂ ካርል ላገርፌልድ 85 ዓመቱን የደፈነዉ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያኑ መስከረም 10 እለት ነበር፤ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ እንኳን ለልደትህ በዓልህ አደረሰሕ ብለዉ ምኞታቸዉን ይግለፁለት እንጂ ካርል ላጋርፌልድ 80 አልያም 70 ወይም ደግሞ 85 ዓመት ይሙላዉ አይሙላዉ እርግጡን ተናግሮ አያዉቅም።  ምክናንያቱ ደግሞ ለሱ እድሜ መቁጠሩ ዋጋ የለዉም። በካርል ላገርፌልድ የፋሽን ልብስ ትርኢት ላይ ተሳታፊ ሆና የምታዉቀዉ ታዋቂዋ የብሪታንያ ዘፋኝ ሊሊ አለን ካርል እጅግ ተሰጥኦ እንደነበረዉም ተናግራለች። 

« በጣም የሚገርም ተሰጥኦ ያለዉ ሰዉ ነዉ። የሚወደዉን ነገር በተለያዩ ምዕተ ዓመታት ለረጅም ጊዜ ሲሰራ ቆይቶአል። እጅግ የሚደነቅ ሰዉ ነዉ። ይኼንን ነገር ሰራ ብዬ ላወጣዉ የምችለዉ አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን በጣም ብዙ ብዙ ነገሮች አሉት። ግን ሳልናገር ማለፍ የማልፈልገዉ ነገር የሻኔል ፋሽን ልብስ ትርኢት እድምተና ብቻ ሳሳልሆን ተካፋይም እንድሆን ጠይቆኝ ፤ የፈሸነዉን ልብስ አድርጌ እድምተኛ ወደሚጠብቅበት መድረክ ሲወጣ የኔን ሙዚቃ ያዜም ነበር። ይህ ከኔ የማይጠፋ ከካርል ላገርፌልድ ጋር ያለኝ ድንቅ ተሞክሮ ነዉ። »

ከወተት የሚገኙ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርት ድርጅት ከነበራቸዉና  በዝያን ዘመን ትልቅና የተከበሩ የተማሩ ከተባሉ ቤተሰቦች ጋር ያደገዉ ካርል ላገርፌልድ በሰሜናዊ ጀርመን የወደብ ከተማ ሃምቡርግ ሃንቡርግ ከተማ ተወለደ።  ካርላ ላገርፌልድ ከአንድ እህቱ እና ከወላጆቹ ጋር በሃንቡርግ ከተማ ሲኖር በጎርጎረሳዉያኑ 1944 ዓ.ም ከተማዋ በቦንብ መደብደብዋን ተከትሎ የካርል ወላጆቻቸዉን ይዘዉ መኖርያቸዉን በመቀየር ወደ ሌላኛዋ ሰሜናዊ ጀርመን ግዛት ሽሊዝቪግ  ሆልሽታይን ኑሮዋቸዉን ይመሰርታሉ። ካርል ላገር ፊልድ ቤተሰቦቹ ልጆቻዉን ይዘዉ ቦታ ቀይረዉ በመጡበት ከተማ ፤ ቀለል እና ተመጣጣኝ ኑሮ ከሚኖሩ የገበሪ ልጆች ጋር ነበር ያደገዉ። ካርል ላገርፌልድ ከሕጻንነቱ ጀምሮ የተለየ ተሰጥኦ እንደነበረዉ ይነገርለታል። ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት አፉን ከፈታበት ከጀርመንኛ ቋንቋ ሌላ በገዛ ራሱ ፍላጎት እንጊሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋን ተምሮ በቋንቋዉ መግባባት ብሎም መፃፍ ማንበብን ጠንቅቆ ያዉቅ ነበር። ስዕል ባገኘዉ ነገር ሁሉ ላይ እየሳለ ይለማመድ እንደነበርም ይነገርለታል። ካርል ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ የአንድ ፈረንሳዊ ሰዓሊ ጥበብ ሥራዎችን ወደ ሚታይበት ቤተ-መዘክር መሄድንም ይመርጥ ነበር።    

ካርል በጎርጎረሳዉያኑ 2014 ዓ.ም ስለሱ በተሰራዉ ዘጋቢ ፊልም ላይ እንደተናገረዉ፤ « የምወደዉ ነገር ሁሉ የፈረንሳይን ነገር ነበር። ያንን እፈልገዉ ነበር፤ ለዝያም ነዉ ከልጅነቴ ፈረንሳይኛ ቋንቋን የተማርኩት ፤ ፈረንሳይኛ ቋንቋን ባልችል ኖሮ፤ በፈረንሳይ ትምህርት ቤት መግባት አልችልም ነበር። »  ብሎአል።  

Kuba Karl Lagerfeld Modesschau in Havanna
ምስል picture-alliance/dpa/A. Ernesto

ካርል እያደገ እየጎለመሰ ሲመጣ ወደ ፈረንሳይ የመሄድ ምኞቱ እየጠነከረ መጣ። ላገር ፊልድ በጎርጎረሳዉያኑ 1950 ዓ.ም የሽቶ የቦርሳና ሌሎች ፋሽን ቁሳቆሱችን የሚያቀርበዉ «ክርስትያን ዲዮር » የተሰኘዉ ድርጅት በጀርመንዋ በሃምቡርግ ከተማ የዘረጋዉን ዓዉደ ርዕይ ከጎበኘ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ፈረንሳይ የመሄድ ምኞቱን በጎርጎረሳዉያኑ  በ1953 ዓ.ም አሳካ።  ላገርፌልድ ከእናቱ ጋር ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ መኖር ከጀመረ በኋላ በሃያ ዓመቱ ፈረንሳይ ላይ በተካሄደ አንድ የካፖርት ፋሽን ዲዛይን ዉድድር ላይ ተሳትፎ የመጀመርያዉን የፋሽን ንድፍ ሥራን አሸነፈ።  ካርል የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የልብስ ቅድ ሞያን ብቻ ነዉ የተማረዉ።  በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በፋሽን ስራዎች ከዘጠኝ ዓመት በላይ በመስራት ላይ የሚገኘዉና ድርጅቱ ማርክ ስታይል በሚል የሚታወቀዉ ወጣት በካርል ሞት ዓለም የፋሽን ፈጣሪ ንጉስን አጥቶአል ሲል ተናግሮአል። 

ካርል በመጀመርያ የተወዳደረበትን የካፖርት ንድፍ ካሸነፈ በኋላ፤ በተለያዩ የፋሽን ድርጅትቶች ዉስጥ ተቀጥሮ ሰርቶአል ። በ 1963 ዓ.ም ካርል ላገርፌልድ ለመጀመርያ ጊዜ አንድ የጥበብ ማኅበርን በዳይሬክተርነት ማገልገል ጀመረ።  በርካታ የሥራ ባልደረቦቹ እንዲሁም የድርጅቱ የፋሽን አድናቂዎች ካርል በነበረዉ ታታሪ የሥራ ሥነ-ምግባርና በጥንካሪዉ በመንፈስ ጽኑነቱ አድናቆትን እያተረፈ መጣ። ላገርፌልድ ፀጉሩን በፖኒቴል ማስያዝ እና መነፅርን የጀመረዉ ጎልማሳነት ዘመኑ ነበር።

ካርል ለሆሊዉዱ ለፓሪሱ ለበርሊኑ የፋሽን መድረክ አዳዲስ የፋሽን ንድፍን በወረቀጥ ላይ የማስቀመጥ ስራ ካልጠመደዉ፤ በፓሪስ ታዋቂ ቡና ቤቶች ጥሩ ቡና መጠጣትን፤ እንዲሁም ጥሩ የተባሉ መጽሐፍትን ለመግዛት በተለያዩ መጽሐፍ ቤቶች መዘዋወርን ያዘወትር እንደነበር ይነገርለታል። እንደዉም ከንድፍ ስራ በተጨማሪ መጽሐፍ የመሰብሰብ ፍቅሩ የግል ቤተ መጽሐፍት እንዲከፍ እንዳስገደደዉ  ይታወቃል። ካርል ላገርፌልድ የታሪክ  የስዕል ፎቶግራፍ ጥራዝና ፤ የተለያዩ የፋሽን መድረክ ፎቶግራፎች ጥራዝን ያካተተ ከ 300 ሺህ በላይ መጽሐፍት እንዳሉት የታሪክ መዝገቡ ያሳያሉ።   

Modedesigner Karl Lagerfeld
ምስል picture-alliance/dpa/Je. Kalaene

« ጥሩ ወይም መልካም የሳምንት መጨረሻ ጊዜ ነበረኝ ማለት የምችለዉ ፤ በሳምንቱ መጨረሻ የገዛኋቸዉን መጽሐፎች ማገላበጥ እና ማየት የቻልኩ ጊዜ ነዉ። መጽሐፎቼን ሳይ ጋደም ብዬ ሳነብ በመሃል እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርገኝ እንደገና ትንሽ ሳነብ ፤ ትንሽ ማስታወሳ ቢጤ ስጽፍ እንደገናሸለብ ሲያደርገኝ እና ሰዓት ስንት ሆነ ብዬ ሰዓት ሰዓት ሳላይ ከዋልኩ ለኔ ጥሩ ጊዜ ነዉ ሲል ተናግሮአል። »  በዩናይትድ ስቴትስ በተለያዩ የፋሽን መድረኮች ባህላዊ የኢትዮጵያን አልባሳት በተለያዩ ስፌቶች በማቅረብዋ የምትታወቀዉ ሌላዋ የፋሽን ልብስ ቅድ ባለሞያዋ ሰሎሜ በታዋቂዉ ጀርመናዊ የፋሽን ልብስ ባለሞያ ስራዎችን አድናቂ መሆንዋን ተናግራለች። 

ካርላ ላጋር ፌልድ ከጎርጎሮሳዊው 1983 ዓ.ም ጀምሮ በፓሪሱ የሚገኘዉን ሻኔል የተሰኘዉን የፋሽን ልብስ ሽቶ ጫማ ቦርሳና የመሳሰሉትን ፋሽን የመቸረሻ ፋሽን የተባሉ ቁሳቁሶች አቅራቢ ድርጅት የንድፍ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ መስራት ጀመረ። ላገርፌልድ ከፋሽን ንድፍ ሥራና መጽሐፍ ከመሰብሰብ ባሻገር ፎቶግራፍ የማንሳት ፍቅርም የነበረዉ ድንቅ የተባሉ ልዩ ጥበብን የተላበሱ በርካታ ፎቶግራፎችን ማንሳቱንና በፋሽን ልብስ ትርኢት መድረኩ ያቀርብም ነበር። ካርል ላጋርፌልድ በ 1989 ዓ.ም የሚወደዉና አብሮት የሚኖረዉ ጓደኛዉ በኢድስ ቫይረስ በሞት ከተለየዉ በኋላ ራሱን በስራ ጠምዶ ለብቻዉ መኖሩ ይነገራል። ሞላ ያለ ቁመና የነበረዉ ላገርፌልድ በ ጎርጎረሳዉያኑ 2000 ዓ.ም ላይ በ 13 ወራት ጊዜ ዉስጥ 42 ኪሎ ቀንሶ ጥሩ ቆመና ይዞ በመድረክ መታየቱ አብዛኞች ተመልካቾቹን አስደምሞም ነበር። ከዚህ ሌላ ካር ላገር ፌል አያጤስም አልኮል መጠጥም እንደማይጠጣ ተዘግቦታል።  

Corsa Karl und Choupette
ምስል Adam Opel AG

ያልተመቸዉ ነገር ሲኖር በግልፅ ትችት በማቅረቡ የሚታወቀዉ ካርል ላገርፌልድ በጎርጎረሳዉያን 2017 ዓመት በአንድ የፈረንሳይ ቴሌቭዝን ጣብያ ላይ በሰጠዉ ቃለ-ምልልስ የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ፖለቲካን በግልፅ መተቸቱ የአንድ ሰሞን ወሬ ሆኖም ቆይቶ ነበር። እንደ ካር ላገርፌልድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዶች በተጨፈጨፉበት ሃገር ጀርመን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሙስሊሞች ጥገኝነት መሰጠት ተቀባይነት የሌለዉ ሲል ተናግሮ ነበር።

በፋሽን ኢንዱስትሪዉ ዓለም ስሙ በገነነዉ በፓሪሱ የሻኔል ፋሽን ልብስ አቅራቢ ድርጅት በዋና አዘጋጅነት ከጎርጎረሳዉያኑ 1984 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለትም ይህችን ዓለም በሞት እስከተለየባት ቀን ድረስ ለ 36 ዓመታት ያገለገለዉ ካር ላገርፌልድ ከ 800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኃብት አለዉም ተብሎአል። ካርል ላጋርፌልድ ባለፉት ዓመታት በፋሽን ትርኢት መድረኩ ሲቀርብ በእቅፉ ይዝዋት ወደ መድረክ የሚወጣዉ የተባዘተ ንድፍ ጥጥ አይነት መልክ ያላት «ሻፔት » የሚል ስምን የሰጣት ባለ ጠጉራም ድመቱ ከ 800 ሚሊዮን ዶላር ኃብቱ ላይ ወደ 125 ሚሊዮን ዶላር ዉርስ ማግኘትዋ ተነግሮላታል። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ