1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፋሉጃዉ ዉጊያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2008

የኢራቅ ጦር ሥልታዊቱን የአል-አምባር ግዛት ርዕሠ-ከተማ ፋሉጃሕን፤ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ ከሚጠራዉ ቡድን እጅ ለማስለቀቅ የጀመረዉን መጠነ-ሠፊ ጥቃት እንደቀጠለ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1J3x6
Syrien Falludscha Hashd Shaabi Kämpfer
ምስል picture-alliance/Xinhua/K. Dawood

[No title]

ባንድ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶች እና የጦር አማካሪዎች፤ በሌላ በኩል በኢራን ወታደራዊ አማካሪዎችና ሚሊሻዎች የሚታገዘዉ የኢራቅ ጦር ጥቃቱን ከከፈተ ከሁለት ሳምንት በልጦታል።

የኢራቅ ጦር ሥልታዊቱን የአል-አምባር ግዛት ርዕሠ-ከተማ ፋሉጃሕን፤ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ ከሚጠራዉ ቡድን እጅ ለማስለቀቅ የጀመረዉን መጠነ-ሠፊ ጥቃት እንደቀጠለ ነዉ።ባንድ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶች እና የጦር አማካሪዎች፤ በሌላ በኩል በኢራን ወታደራዊ አማካሪዎችና ሚሊሻዎች የሚታገዘዉ የኢራቅ ጦር ጥቃቱን ከከፈተ ከሁለት ሳምንት በልጦታል።እስካሁን ግን ከተማይቱን ከአማፂያኑ እጅ ማስለቀቅ አልቻለም።አማፂያኑ ባንፃሩ የከተማይቱን ነዋሪ እንደ ሰብአዊ ጋሻ ይጠቀሙበታል ይባላል።ከሪስተን ክኒፕ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን እስከወረረበት እስከ 2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊዉ አቆጣጠር ነዉ) ድረስ ከታሪካዊቱ ሐገር ታሪካዊ፤ደማቅ፤ ዉብ ከተሞች አንዷ ነበረች።ፋሉጃሕ።አሁን ግን የፍርስራሽ፤ ክሳይ፤ ቁሻሻዋ ክምር፤ ከሕንፃ፤ ቤት፤ መሳጂዶችዋ ጋር ፉክክር ገጥመዉባታል።
ከ326 ሺሕ በላይ ሕዝብ ነበረባት።የአሜሪካ ጦር፤ የኢራቅ ጦር፤ የአል-ቃኢዳ ሸማቂዎች፤ የአይሲስ ተዋጊዎች ሲፈራረቁባት ያለቀዉ አልቆ፤የተሰደደዉ ተሰድዶ አሁን የቀረዉ ሐምሳ ሺሕ ይገመታል።የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ከተማይቱን ከተቆጣጠረበት ከ2014 ጀምሮ የፋሉጃሕ ነዋሪዎችን መግደል፤ ማሰቃየት፤ ማንገላታቱ ይነገራል።የተረፉት ከከተማ እንዳይወጡ ታግደዋል።
የኢራቅ መንግሥት እንደሚለዉ ከከተማይቱ ነዋሪ ISISን የሚደግፉት አንድ በመቶ ቢሆኑ ነዉ።ይሁንና ፋሉጃሕ ምዕራባዉያን እና በምዕራባዉያን የሚደገፉ መንግሥታትን የሚቃወሙ አማፂያን መፍለቂያ፤ መደራጂያና መሸሸጊያ የሆነችዉ ከ1991 ጀምሮ ነዉ።
ያኔ፤ አሜሪካ መራሹ ጦር ኩዌትን ከኢራቅ ወረራ ነፃ ለማዉጣት በሚል ሰበብ ኢራቅን ሲደበድብ አንድ የብሪታንያ የጦር ጄት የከተማይቱን እዉቅ የገበያ ሥፍራ አጋየዉ።150 ሰላማዊ ሰዉ ፈጀ።ሁለተኛ ጄት፤ ሁለተኛ ቦምብ። 50 ተጨማሪ ሰዉ ገደለ። ከዚያች ቀን ጀምሮ ፋሉጃሆች ምዕራባዉያን እና ታማኞቻቸዉን «ሐራም» አሉ።የእነ አቡ ሙሳብ አል ዘርቃዊ ደጋፊ፤ከለላ ሰጪ፤ ተባባሪም ሆኑ።
ኢራቅ ዉስጥ በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች የተገደሉት ሲጠብ ፋሉጃሕ፤ ሲሰፋ አል-አምባር ግዛት ነዉ።አሜሪካ በ2004 ከተማይቱን ለመቆጣጠር 6500 ባሕር ወለድ፤ 1500 እግረኛ እና 2000 የኢራቅ እግረኛ ጦር ማዝመት ነበረባት።
በአስራ-ሁለተኛ ዓመቱ ዘንድሮ በጣም ቢበዛ አንድ ሺሕ የሚገመቱ የISIS ተዋጊዎችን ለመደምሰስ በአስር ሺሕ የሚቆጠር የኢራቅ ጦር፤ የኢራቅና የኢራን ሚሊሺያ፤ ኮማንዶና ፖሊስ ዘምቷል።ሥለዉጊያዉ የሚዘግበዉ ጋዜጠኛ መሐመድ ዓሊ ማሙሪ እንደሚለዉ ወታደራዊዉ ዉጊያ ፈጠነም ዘገየ በመንግሥት ሐይል የበላይነት መጠናቀቁ አይቀርም።የከተማይቱን ሕዝብ ልብ ለመግዛት ግን መንግሥት ብዙ መሥራት፤ ብዙ መጣር፤ ከተማይቱን መልሶ መገንባት ግድ አለበት።
በበርሊን የሳይንስና የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ፎልከር ፔርቴስ እንደሚሉት ደግሞ ኢራቅን ባጠቃላይ ከአደገኛ ሐገርነት ለማዉጣት ብዙ ጥረት ይጠይቃል።
«ችግሩ በሙሉ እንዳለ ሆኖ (ኢራቅ) ሙሉ በሙሉ የጨገፈ መንግስት ናት ማለቱን አልፈልግም።እርግጥ ISIS በሚቆጣጠራቸዉ ግዛቶች መጨንገፉ በግልፅ ይታያል።ባጠቃላይም አደገኛ ሐገር መሆንዋ ግልፅ ነዉ።»
ISIS ኢራቅ ዉስጥ ፋሉጃሕን በመሳሰሉ ግዛቶች ከተመታ፤ ሶሪያ ዉስጥም እየተዳከመ በመሆኑ ዳግም የሚደራጅበት ጠንካራ መሠረት አያገኝም የሚሉ ተንታኞች አሉ። የማይንስ ዩኒቨርስቲዉ ፕሮፌሰር ጉተር ሜየር ግን ሊቢያ «አለችለት» ባይ ናቸዉ።
«በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የISIS ተዋጊዎች ከሶሪያ ወደ ሊቢያ ተዛዉረዋል።ሊቢያ መንግሥት አልባ ሐገር ናት።ISIS እዚያ ለወደፊቱ እየተደራጀ ነዉ።ምናልባት ሶሪያና ኢራቅ ዉስጥ ወታደራዊ ሽንፈት ቢገጥመዉ እንኳ የቡድኑ ፍፃሜ ነዉ ማለት አይደለም።»
ሜየር እንደሚሉት የሽብር ጥቃቱም ሙሉ በሙሉ ይወገዳል ብሎ ማሰብ አይቻልም።ወደ አዉሮጳ የሚመለሱ ወይም ሰርገዉ የሚገቡ የቡድኑ አባላት በየሐገራቸዉ አጥፍተዉ ላለማጥፋታቸዉ ምንም ዋስትና የለም።

Irak Falludscha Zivilisten versuchen die Stadt zu verlassen
ምስል picture alliance/AP Photo/ K. Mohammed
Irak Falludscha Regierungssoldaten vor der Stadt
ምስል picture alliance/AP Photo/O. Sami

ኬርስተን ክኒፕ/ነጋሽ መሀመድ

ሂሩት መለሰ