1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀ/ጥበቃ ም/ቤት እና ፀረ ሽብርተኝነት ውሳኔው

ሐሙስ፣ መስከረም 15 2007

የተመድ አባል ሀገራት ፅንፈኞችን ለመቆጣጠር ጠንካራ ርምጃ እንዲወስዱ የየተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ትናንት ባሳለፈው ውሳኔ አሳሰበ። ሽብርተኝነትን ለማሸነፍ አባል ሀገራት ባጋራ መስራት እንዳለባቸው የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙን ተማፀነዋል።

https://p.dw.com/p/1DLCr
UN Sicherheitsrat 24.09.2014
ምስል Reuters/Brendan McDermid

«ሽብርተኝነትን የማጥፋቱ ጥረት ዓለም አቀፍ ትብብርን እና የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠይቃል። ልንጠቀምባቸው ከሚገቡት የተለያዩ ዘዴዎች መካከል አንዱ፣ ፅንፈኛ ቡድኖችን ስር እንዲሰዱ እና እንዲስፋፉ ያስቻሉዋቸውን ሁኔታዎች ለማጥፋት ጠንክሮ መስራት ነው። »ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆንበት ድርጊት በኢራቅ እና በሶርያ ያሉት የሚነቀሳቀሱት «የአይ ኤስ»ን የመሳሰሉ አክራሪ ቡድኖች የሚቀላቀሉዋቸው ደጋፊዎች እና ተዋጊዎች እንዳያገኙ ያከላክላል። አሳሪ የሆነው ይኸው ውሳኔ የ15 ቱን የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ስምምነት አግኘቶ ነው የፀደቀው። ፅንፈኞቹ ቡድኖች ተዋጊዎች የሚመለምሉበት እና የቡድናቱ ደጋፊዎችም ወደተባሉት ሀገራት የሚጓዙበት ድርጊት መከልከል እንደሚኖርበት በውሳኔው ተጠቅሶዋል። በጠበብት ጥናት መሠረት፣ እስካሁን ወደ 12,000 የሚጠጉ የ70 ሀገራት ዜጎች ፅንፈኛ ቡድኖችን ለመቀላቀል ወደ ሶርያ እና ኢራቅ ተጉዘዋል። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱን ስብሰባ የመሩት የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ «አይ ኤስ» መደምሰስ እንዳለበት በኒው ዮርክ አስረድተዋል።

« አሁን ያፀደቅነው ይኸው ታሪካዊ ውሳኔ የገጠመንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም ያለንን ፅኑ ቁርጠኝነት ያረጋግጣል። አሳሪም ነው። መንግሥታት ማሟላት የሚኖርባቸውንም አዳዲስ ኃላፊነቶችን አስቀምጦዋል። ይህ ውሳኔ በመንግሥታት መካከል ያለውን ትብብር ያጠናክራል፣ ይህም፣ የውጭ ዜጎች የሆኑ የአሸባሪ ተዋጊዎችን ዝውውር እና እንቅስቃሴን የሚመለከቱ ተጨማሪ መረጃዎችን መለዋወጥንም ያጠቃልላል። »

አርያም ተክሌ