1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጭልጋ ተመላሾች መጪው ጊዜ ያሳስባቸዋል

ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2011

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቤት የተቃጠለባቸውን ሰዎች ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል። ወደቦታቸው በመመለስ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች ቀለብ እተሰፈረልን አንኖርም የእርሻ መሳሪያዎችና በሬዎች ይሟሉልን ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3IiHi
Äthiopien Vertriebene aus Chilga
ምስል DW/A. Mekonnen

የጭልጋ ተመላሾች መጪው ጊዜ ያሳስባቸዋል

ሰሞኑን የጋዜጠኞች ቡድን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ያለውን ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም የስራ ሁኔታ በመጎብኘት ላይ ነው። ትናንት በዚሁ ዞን ጭልጋ ቁጥር 2 ላዛ በተባለው ቦታ እንደተመለከትነው የተቃጠሉ ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ሥራ መቀጠሉን ለማየት ችለናል።

Äthiopien Vertriebene aus Chilga
ምስል DW/A. Mekonnen

የላዛ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ስመኘው ጥሩነህ የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው። በአማራና ቅማንት ማህበረሰቦች መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት የደረሰባቸውን ሁኔታ ለዶይቼ ቬለ DW እንደተገሩት ቤት ንብረታቸውና ሀብታቸው ወድሟል። 

አርሶ አደሩ አያይዘውም የተደረገላቸውን ድጋፍና ስጋታቸውን እንዳብራሩት ወቅቱ የዘር ወቅት በመሆኑ አስፈላጊው የግብርና መሳሪና በሬዎች ሊዘጋጁላቸው ይገባል ካልሆነ ግን ቀጣዩን ዓመት ለመኖር አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ የጭልጋአርሶ አደር ቀለብ በጣሳ ተሰፍሮለት ህይወቱን አይመራም ነው ያሉት። መንግስት ወደ ቦታቸው እንዲመልሳቸው ማድረጉንና መኖሪያ ቤታቸው እንዲሰራ ማድረጉ መልካም ነገር እንደሆነም አመልክተዋል።

ሌላዋ የዚህ ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ አያል ክብረት ናቸው። አራት ህጻናትን ያለ አባት ያሳድጋሉ፣ በግጭቱ ወቅት የነበራቸውን ሁሉ አጥተዋል። መንግስት ቤት እንዲገነቡ ሁኔታውን እንዳመቻቸላቸው አስረድተዋል።

አቶ ሚካኤል ንብረት የጭልጋ ቁጥር 2 ላዛ ቀበሌ ቤት ግንባታ አስተባባሪ ናቸው። በአካባቢው 210 ቤቶች መቃጠላቸውን ጠቁመው አሁን ከግማሽበላይ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ሁሉም ቤቶች ተገንብተው ይጠናቀቃሉ እንደ አቶ ሚካኤል።

Äthiopien Vertriebene aus Chilga
ምስል DW/A. Mekonnen

ተመላሾቹ የሚያነሷቸውን የእርሻ ቁሳቁስ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አማረ ክንዴ እንዳሉት የግብርና ግብዓቶችን ለማቅረብ ጥናቶች እተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡

ከሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደነበሩበት ለመመለስ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ደግሞ የቤት ግንባታውን በቦታው ተገኝተው ሲጎበኙ ያገኘናቸው የአማራ ክልል ምክርቤት የህግ ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ ተናግረዋል፡፡

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በአጠቃላይ 1097 ቤቶች የተገነቡ ሲሆን 36 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን የአደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን አመልክቷል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ