1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦር መሳሪያ ሽያጭ ዉል

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 2004

ከተለያዩ ሀገሮች የተዉጣጡ ልዑካን ከትናንት ሰኞ አንስተዉ ኒዉዮርክ በተመድ ጽሕፈት ቤት ተሰባስበዋል። የስብሰባዉ ዋና ዓላማም የመጀመሪያ የሆነዉን የጦር መሣሪያ ሽያጭን የሚቆጣጠር ዉል ተደራድረዉ ለማርቀቅ ነዉ። በዓለማችን የሚካሄደዉ

https://p.dw.com/p/15QiA
ምስል picture-alliance/Runesson Hansscanpix Sweden

የጦርመሣሪያ ሽያጭ ከ60 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ነዉ። ጀርመን ለአንድ ወር የሚቆየዉ ይህ ጉባኤ ትናንሽ የጦር መሣሪያዎችና ጥይት ጭምር ቁጥጥር እንዲደርግባቸዉ አሳስባለች። ጀርመንን ጨምሮ ብሪታንያ፤ ፈረንሳይና ስዊድን በጋራ የመንግስታቱ ድርጅት በሰብዓዊነት ላይ እየተባባሰ የሄደዉን ስጋት የሚቀንስ አጠቃላይ ዉል እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል።

ኒዮርክ ላይ የተጀመረዉ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ቁጥጥር ላይ የሚነጋገረዉ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ የሶርያ ግጭትና አፍሪቃ ዉስጥ የሚሰርገዉን የጦር መሳሪያ እንደማሳያ ተመልክቷል። የጦር መሳሪያ ሽያጭ ቁጥጥር እንዲደረግበት የሚያሳስበዉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ኮሚቴ የበላይ ብሬይን ዉድ ከፍተኛ ጥቃትና የመብት ጥሰት እንደሚፈፀምበት እየታወቀ ሩሲያ ለሶርያ መሣሪያ መላኳ ሃላፊነት የጎደለዉ ተግባር ነዉ ብለዋል። የጦር መሣሪያ ዝዉዉር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚያሳስቡት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ በእያንዳንዷ ደቂቃ የአንድ ሰዉ ህይወት በጥይት እንደሚያልፍ ይገልፃሉ።

Waffenhandel im Irak blüht
ምስል AP

ከምንም በላይ ቀዉስና ግጭት በተባባሰባቸዉ አካባቢዎች፤ እንዲሁም የመብት ጥሰት ለሚፈፀምባቸዉ ሀገሮች መሳሪያ እንዳይላክም ያሳስባሉ። እንደእነሱ አስተያየትም «ወርቃማ» የሚሰኘዉ መመሪያ የጦር መሣሪያ ዝዉዉሩን ቢቆጣጠር ይበጃል። ወርቃማ የተሰኘዉ መመሪያ ሌሎችን አለመጉዳት፤ ለሌሎች የማሰብና የመሳሰሉትን መልካም ስነምግባሮች ያካትታል። በጀርመን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተጠሪ ካተሪና ሽፒስ ይህ መመሪያ ከሻጭም ከገዢዉም ወገን ሊታይ እንደሚገባ ያሳስባሉ፤

«የወርቃማዉ መመሪያ ተግባራዊነት በእያንዳንዱ ሀገር ከግምት ሊገባ ይገባል። ያም ማለት በሻጩ እና ገዢዉ ሀገሮች፤ እንዲሁም በመሳሪያዉ ሽያጭ ሂደት የሚሸጋገርበት ሀገር ካለ ያም ጭምር ማለት ነዉ።»

በጦር መሳሪያ ሽያጭ ከፍተኛዉን ደረጃ የያዘችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከገበያዉ 40 በመቶዉን ትሸፍናለች። ከሷ ቀጥሎ ብሪታንያ፤ ቻይና፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመንና ሩሲያ እንደአጠራራቸዉ ይከተላሉ። እናም ዲፕሎማቶች እንደጠቆሙት እነዚህ ዋነኛ የጦር መሣሪያ አቅራቢ ሀገሮች የትኛዉንም የቁጥጥር ዉል በቀላሉ የሚቀበሉት አይመስልም። በየዓመቱ ስድስት ቢሊዮን ጥይት የምታመርተዉ አሜሪካ የጥይት ሽያጭ ነገር ከዉሉ እንዲካተት አትፈልግም። ቻይና በበኩሏ በማደግ ላይ ላሉት ሀገሮች በገፍ የምትሸጠዉ የአነስተኛ የጦር መሳሪያ ሽያጭ በዉል እንዲታሰር አትሻም። ጀርመን ሄሰን ዉስጥ የሚገኘዉ ሰላምና ግጭትን የሚያጠናዉ ተቋም ሊቀመንበር ዶክተር ዚሞነ ቪዝቶስኪ ይህ ጉዳይ በድርድሩ ሂደት ብዙ ሊያከራክር እንደሚችል አስቀድመዉ ጠቁመዋል፤

Waffenhandel in Mogadischu
ምስል dpa

«ዉዝግቡ ለምሳሌ የአነስተኛ ቀላይ መሳሪያ እንዲሁም የጥይት ሽያጭ ጉዳይ በዉሉ ይካከት አይካተት የሚለዉ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ሁለትዮሽ ጥቅም ያለዉ መሣሪያም እንዲሁ ሊያነጋግር ይችላል።»

አነስተኛ የጦር መሣሪያዎች በየቀኑ የሁለት ሺህ ሰዎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ ተገልጿል። የአዉሮጳ ሀገሮች የሚረቀቀዉ ስምምነት የጦር መሣሪያ ንግዱ ዓለም ዓቀፍ ግልፅነት የተላበሰ እንዲሆን ጠይቀዋል። ቻይና፤ ሩሲያና የአረብ ሀገሮች በፊናቸዉ የስምምነቱ ቅድመ ሁኔታዎች በፖለቲካ የተቃኙ ናቸዉ የሚል ቅሬታቸዉ ከወዲሁ እያሰሙ ነዉ። ከ193ሀገሮች የተዉጣጡት የተመድ አባል ሀገገሮች ለአንድ ወር በሚዘልቀዉ ድርድር የዉል ስምምነት እንደሚያረቁ ይጠበቃል። ሆኖም አብዛኞቹ ዲፕሎማቶች እና ታዛቢዎች ከዚህ መድረሱ አስቸጋሪ እንደሚሆን ነዉ የጠቆሙት።

ማርያም ጌርከ

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ