1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎንደሩ እና የደባርቁ ግጭት

Merga Yonas Bulaዓርብ፣ ሐምሌ 8 2008

በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ባሳለፍነዉ ማክሰኞ በአከባቢዉ ነዋሪዎችና በፌዴራል ፖሊስ መካከል በተቀሰቀሰዉ ግጭት የሰዉ ሕይወት ማለፉ እንዲሁም ንብረቶች መቃጠላቸዉ ተዘግበዋል።

https://p.dw.com/p/1JPfP
Karte Äthiopien englisch

[No title]

ለግጭቱ መንስኤ የሆነዉ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ መንግሥት ፍታዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩትን ግለሰቦች «በኤርትራ ከመሸጉ ፀረ- ሰላም ኃይሎች መመሪያ» ተቀብለዋል ብሎ «ስም ለጥፎ» በማሰሩ ምክንያት ግጭቱ መባባሱን የወጡ ዘገባዎቹ ያትታሉ። በዚህም ምክንያት ተቃዉሞዉ በትላንትናዉ ዕለት በሰሜን ምሥራቅ ጎንደር የምትገኘዉ ደባርቅ ከተማ እንደተስፋፋና በግጭቱም ምክንያት የ10 ሰዉ ሕይወት ማለፉ እየተዘገበ ይገኛል።


የፌደራል መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፍ አቶ ጌታዉ ረዳ በዛሬዉ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰሜን ጎንደር «የተፈጠረውን ኹከት የፀጥታ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን በሠሩት ሥራ መቆጣጠር ተችሏል» ሲሉ ተናግረዋል። በጎንደር ሁኔታዉ ተረጋግተዋል የሚሉት የአማራ ክልል የኮሙኒኬሸን ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እስከ አሁን በቁጥር 10 ሰዉ መሞታቸዉ ማረጋገጥ አልችልም ይላሉ።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪ የሆኑት አቶ ተሻገር ወልደ ሚካኤልን በከተማዋ ስላለዉ ወቅታ ሁኔታ ሲያስረዱን በከተማዋ አሁንም መንገድ ላይ የሚታየዉ መከላክያ ሠራዊት መትረየስ ጠምዶ እንደሚንቀሳቀስ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።


የታሠሩት የኮሚቴ አባላቶቹ በመንግሥት እዉቅና አግኝተዉ የማንነት ጥያቄያቸዉን ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸዉ እየታወቀ መንግሥት ለምን «ፀረ-ሰላም» ናቸዉ ሲል ስም ይሰጣል ብለዉ የሚጠይቁም አልጠፉም።


ይሄን ጉዳይ በተመለከተ ሰዎች አስተያየታቸዉን እንዲሰጡን በጠየቅነዉ መሠረት መንግሥት የሕገ-መንግስቱን ቃል ማክበር እንዳለበትና ነፃ ሆኖ ከማኅበረሰቡ ጋር መወያየት እንዳለበት ጠቁመዋል።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ